በቀበሌ መዝናኛ ውስጥ

12 Oct 2017

 

መዝናኛ ከተባለ መዝናኛ ነው፡፡ መዝናናት ከተባለም መዝናናት ነው፡፡ እንዲያውም እኮ ድንቃድንቅ የመዝናኛ ዜናዎችን የሚያቀርቡ መገናኛ ብዙኃንን ብትሰሙ ሰዎች የሚዝናኑባቸው በርካታ አስገራሚ ነገሮች እንዳሉ ትገነዘባላችሁ፡፡ እናም ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ የእኔ የመዝናኛ ምርጫዬ ቀበሌ ነው፡፡ ይህን ጊዜ ታዋቂ ሰው ብሆን ኖሮ ይህን አመሌን ከልጅ እስከ አዋቂ ያውቁልኝ ነበር፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም እንደልማዳቸው «ቀበሌ ብቻ የሚዝናናው ዝነኛ ሰው» እያሉ ያወሩልኝ ነበር፡፡ ቆይ ግዴለም ታዋቂ የምሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም!

ወደ ተቀመጥኩበት ሀሳብ ስመለስ (አልተነሳሁም ብዬ ነው) ዛሬ ይዣችሁ የምገባው ቀበሌ መዝናኛ ውስጥ ነው፡፡ ቆይ ግን ስለቀበሌ መዝናኛዎች ብዙ የማይወራው ለምንድነው? ሰው ግን ችግር አለበት፡፡ ቀለል ያለ ዋጋ ያለበት ቦታ ይጠቀምና ስለ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ያወራል፡፡ እኔ ግን ውለታዬን አልረሳም፡፡ ቆይ ግን ከዚያ በፊት አንድ ችግሬን ልናገር፡፡ የቀበሌ መዝናኛ ውስጥ የምገባው በአካባቢው ኢንተርናሽናል ሆቴል እንዳለ አረጋግጬ ነው፡፡ ቀበሌ ምግብ እበላና ውጭ ወጥቼ የሚያውቀኝ ሰው በዚያ እስከሚያልፍ እጠብቃለሁ፡፡ ሰውየው ሲመጣ ኮከብ ሆቴሉ በራፍ ላይ እሆንና እጄንና አፌን እጠራርጋለሁ፡፡ አሁን እኔን እዚያ በልቶ ነው ብሎ ማን እንዲገምት ነው?

አሁን ቀበሌው መዝናኛ ውስጥ ገብተናል፡፡ ቀበሌ ውስጥ ልብ ብለህ ካየህ ብዙ የሚያዝናኑ ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚገኙት በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በቀበሌ መዝናኛ ውስጥ ቆነጃጅት አገኛለሁ ማለት የዋህነት ነው፡፡ ሴቶች ግን ሐብታም ናቸው ማለት ነው? ትልልቅ ሆቴሎች እና ካፌዎች ውስጥ እንጂ የቀበሌ መዝናኛ ውስጥ ዘናጭ ሴት አይቼ አላውቅም፡፡ አይ! የምን ያለ አግባብ ማመስገን ነው ከወቀሳውም ጨመር ላድርግ፡፡ ሴቶች ቀበሌ መዝናኛ የማይገቡት ከወንድ በላይ ሐብታም ሆነው ብቻ ሳይሆን እንደተባለውም እነሱ ስለማይከፍሉ ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ ወንድ የሚወዳትን ሴት የትም ውሰደኝ ብትለው ይወስዳታል፡፡ ስለዚህ ቀበሌ አልገባም ካለችው ያው እንደፈረደበት ወደ ሆቴል ወይም ወደ ካፌ ነው፡፡

አሁን ወደ ወንዶች ተመልሻለሁ፡፡ እንዳልኳችሁ ከወንዶች እንኳን በዕድሜ ገፋ ያሉት ይበዛሉ፡፡ ዳሩ ግን እዚያ ውስጥ እንደ አዋቂ ሆነው አይደለም የሚታዩት፡፡ ያን ያህል የጎላ ባይሆንም አብዛኞቹ ሞቅ ብሏቸው ነው የሚታዩት፡፡ ደግነቱ ግን ቀበሌ ውስጥ ያለ ሞቅታና ሌላ ቦታ የሚታየው የሚለያይ ይመስለኛል። ሌላ ቦታ ሰዎች ሞቅ ሲላቸው እርስበርስ ሲሰዳደቡና ሌላ ሰው ሲረብሹ ነው የማየው፡፡ ቀበሌ ውስጥ ያለ ሞቅታ ግን ከራስ ጋር ብቻ የሚያስወራ ነው፡፡ አንዳንዱ ድምጹን ከፍ አድርጎ የሆድ የሆዱን ያወራል(ለማን እንደ ሚያወራው ባይታወቅም)፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ድምጹ አይሰማም እንጂ አካላዊ እንቅስቃሴው ሌክቸረር የሚሰጥ ነው የሚመስለው፡፡ ሌላው ብቻውን ይነሳና ውዝዋዜውን ያስነካዋል፡፡ ይህኔ እሱ ከሚዝናናው ይልቅ ሌላውን የሚያዝናናው ይበልጣ(እያዝናኑ መዝናናት እንዲህ ነው)፡፡

እስኪ አሁን ደግሞ ወደ መስተንግዶው እንሂድ፡፡ በቀበሌ ውስጥ ለመስተናገድ የገባ ሰው አንዱ ችግር የሚሆንበት ነገር እጁ እስከሚላጥ ማጨብጨቡ ነው፡፡ ሌላ ቦታ ገና ገብተህ ቁጭ ከማለትህ አስተናጋጇ መጥታ «ምን ልታዘዝትልሃለች፡፡ ቀበሌ ውስጥ ግን የቆየ ይሁን አይሁን የመጣ ይሁን፣ ቀኑ አልመሽለት ብሎ የገባ ይሁን ስለማይታወቅ ነው መሰለኝ ካልተጣራህ ማንም ዞር ብሎ አያይህም፡፡ በዚያ ላይ መቀመጫ ማግኘት ራሱ ከባድ ነው፡፡ ጠረጴዛ ካለበት ቦታ ሄደህ ተደርበህ መቀመጥ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የመጣ ይሁን የቆየ አያስታውቅም ማለት ነው፡፡

ቀበሌ ለምን ሰው ይበዛበታል? ዋናው ጥያቄ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ለነገሩ መልሱም ግልጽ ነው፤ ያው ክፍያው ቀላል ስለሆነ ነዋ፡፡ ሌላ ምክንያትማ በፍጹም አይኖረውም፡፡ እዚህ ላይ እንግዲህ ምሳሌ የማደርገው ራሴን ነው፡፡ የደመወዝ ሰሞን ለተወሰኑ ቀናት ወደ ካፌዎች ጎራ ካልኩ በኋላ ወደ ቀበሌዬ መለስ ነው፡፡ ያው እንደነገርኳችሁ «ድሃ ነው እንዴ ቀበሌ የሚጠቀመው» እንዳልባል ኢንተርናሽናል ሆቴል አካባቢ መርጬ ነው፤ ሌላኛው ዘዴዬ ደግሞ ጨለማን ተገን አድርጎ መሄድ ነው፡፡ ችግሩ የቀበሌ መዝናኛዎች ከሁለትና ሦስት ሰዓት በኋላ ዝግ ናቸው፡፡ ቆይ ግን እንዲህ ተደብቄ ገብቼ እዚያ የማውቀው ሰው ቢገኝስ? ምን አገባኝ እሱም እንደኔው ሊጠቀም ነው የገባው፡፡

በቀበሌ መዝናኛ ውስጥ የሚመሰገኑ ነገሮችም አሉ(እስካሁንም እኮ እያማረርኩ አይደለም)፡፡ ያዘዝከው ነገር ምንም ሳይዛባ ቶሎ ነው የሚመጣው፡፡ በዚያ ላይ ክፍያው ቅድሚያ ስለሆነ በሒሳብ መጨቃጨቅ አያጋጥምም፡፡ የምትፈልገውን ነገር ቀድመህ ትከፍላለህ፡፡ ከተስማማህ ይሆናል፤ ካልተስማማህ ለመተው ያመቻል፡፡ በተለይም ሞቅ ለሚላቸው ሰዎች ይሄ ነገር ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም በኋላ ቢሆን ይምታታባቸው ነበር፡፡ ኧረ ይሄ ነገር አንድ ልብ ያልተባለ ጥቅም አለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምን ያህል ብር እንዳላቸው እንኳን አያውቁም፡፡ ተጠቅመው ሲያበቁ ኪሳቸውን ዳበስ ዳበስ አርገው «እዚያኛው ሱሪዬ ውስጥ እረስቼው» የሚሉም አሉ፡፡ በእርግጥ መርሳት በትክክል የሚያጋጥምበት ጊዜም ይኖራል፡፡ ለዚህ ለዚህ እንግዲህ ቅድሚያ ከሆነ ግልግል ነው፡፡

ሌላው የማመሰግናቸው ነገር በቀበሌ ውስጥ የሚከፈተው ቴሌቪዥን የአገር ውስጥ ጣቢያ መሆኑ ነው፡፡ ሌላ ቦታ እኮ ማንም አይስማው እንጂ የሚከፈተው የውጭ ነው፡፡ ቀበሌ ውስጥ በዜና ሰዓት ገብተህ ዜና መስማት፣ ፕሮግራም መከታተል መቻሉ መልካም ነው፡፡

በሉ እንግዲህ ሐብታም የሆናችሁ ሰዎች ቀበሌ ምን እንደሆነ አስተዋወቅኳችሁ፡፡ ሐብታም ሳትሆኑም እንዲያው ለመግደርደር «ቀበሌ መዝናኛ አልገባም» ለምትሉ በኋላ «ብር አበድረኝ» ስትሉ እንዳልሰማ፡፡ በያላችሁበት መልካም መዝናኛ!

 

ዋለልኝ አየለ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።