ደብዳቤው 3

06 Dec 2017

 

ይድረስ ለተከበርከው ለታፈስከው… ማነው ለታፈርከው ወዳጄ አያ ሻረው፡፡ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ጣጣ በቅጡ እንኳ ሰላምታ እንዳላቀረብልህ አረገኝ፡፡ የዚህ አገር ምንገድ አያልቅምና እንደ ጉንዳን በየኸድኩበት ስሰለፍ እናእጁን መዋጥ አስመስሎ እየተጋፋ ከሚበረብር ወሮ በላ ኪሴን ስከላከል እውልለሀለሁ፡፡ ደሞ እኮ የተሰለፍኩትን ያህል በሰዓቱ ኸፈለግሁበት ብደርስ ምን አለበት?

እየውልህ እዚህ አገር መሂናውን የሚነዳው የትራፈሪክ ባርኔጣው ሳይሆን አይቀርም፡፡ አዳሜ መዘወሪያ ፍቃዱን ሲያዎጣ ‹‹ከራስ በላይ ነፋስ›› ብለው ያስረገሙት… ማነው ያስመረቁት ይመስል የትራፈሪክ መብራት መሀል ያንዱ መኂና ባንዱ ምንገድ ላይ ይሸነቆርልህና እርስ በርስ ጡሩምባውን እየነፋ ማለፍ የለ ማሳለፍ ዝም ብሎ መፋጠጥ ብቻ፡፡ በዚህ መሀል ሰርቶ አደር እኔ ቢጤ ምንገዱን ወይ እግዚሀር መጥቶ አያስለቅቅ ወይ ኸታክሲው ወርደን በእግራችን አንወዘወዝ… የስራው ሰዓት አለፈ-አላለፈ ስንንቦጀጀቦጅ አንድ ባለ ነጭ ባርኔጣ ይመጣና ይገላግለናል፡፡

በክብር እለፍ ላሳልፍህ ተባብሎ መዘወር የተሳነው ዘዋሪ ሁላ ባርኔጣውን ሲያይ ጥንቁቅ የስነ ምግባርና ትህትና ባለሟል፤ ተርብ የህጉ ተቆርቋሪ ሆኖ መዘወር ይጀምራል፡፡ ያው እኔና የኔ ብጤ ወደ ስራችን አረፋፍደን መግባት አለቆቻችንም ከደመዎዛችን ላይ መቆንደድ የዘወትር እጣፋንታችን ሆኗል፡፡

ከሁሉ ይባስ ብሎ ግን ተስድስት ወር በፊት ግምበኛ የሆንኩበት (ሙያተኛ ሆኘልሀለሁ)ወደ ሰማይ ጭምቡል ያለ ህንጣ ላይ የሚያሰራን አለቃ እኛ ስናረፍድ ከደመወዛችን ላይ ለመቆነጣጠር የማያመነታውን ያህል ደመወዝ እንደልቡ ሲያዘገይብን ትንሽ እኳ አይከነክነውም፡፡ ኧረ ማዘግየት ብቻም አይደል ተያ የባሰ ግፍ ይሰራብናል፡፡ የዛሬ ወር የሆነውን ላጫውትህ፡፡

ስራ አፈር ድሜ በልተን ጨርሰን ካስረከብን በኋላ ክፍያ ስንጠብቅ ሌላ ተጨማሪ ስራ ይኮናተርና ‹‹አዲሱን ስራ ጀምሩ ፤ የክፍያ ሂሳብ ሰረቸ ለዋናው አለቃ ልኬዋለሁ ዛሬ ወይ ነገ ይደርሳል›› ይለናል፡፡ እንግዲህ ምግብ በዱቤ እየበላንና እዳችን እየተቆለለ በዚያ ላይ የቤት ክራይ ምንከፍለው አጥተንና ቀኑ አልፎ ከአከራይ ጋር አዩኝ አላዩኝ ጠዋት ማታ በድብብቆሽ እየተሳቀቅን ግን አዲሱን ስራ እየሰራን በተስፋ ስንጠብቅ እሱም ዛሬ ነገ እያለ ሳምንታት ያጉላላናል፡፡

መጨረሻ ሲብስብን ስራ አቁመን ‹‹ደመወዛችንን ውለድ›› ብለን ስናፋጥጠው ‹‹ዋናው ተቋራጭ ገንዘብ አለቅልኝ ብሎ እኮ ነው፡፡ የናንተ ጉዳይ እኮ ሌት ተቀን ያስጨንቀኛል፡፡ ድርጅቱ ገንዘብ ባለመልቀቁ እኔም እንደእናንተው በችግር ነው ያለሁት፡፡›› ብሎ አንጀታችንን ሊበላ ይቃጣዋል፡፡

‹‹ስራ በውል መሰረት ተሰርቶ ካለቀ ድርጅቱ ምን አርጉ ብሎ ነው ገንዘብ የማይለቅ?›› ብለን ስንወጥረው ‹‹ዛሬን ብቻ ታገሱ፡፡ ስራ ግን መቆም የለበትም፡፡ ይኸን ስንጨርስ ለሁላችሁም ሸጋ ክፍያ ያለው አዲስ ስራ ተዋውያለሁ፡፡›› ይለናል፡፡

ይኸኛው ወጣት አሰሪያችን ደግሞ የእኛ መራብና መጠማት፣ ከተከራየነው ቤት ወደ ጎዳና መወርወራችን ሳይታየው <<ስራ ግን መቆም የለበትም>> ይለናል፡፡ ምን በልተን፣ በየትኛው ጉልበታችን ልንሰራለት?መቸም አንተ የአያ ዳርጌ ወፍጮ እንኳያለ ውሀ ሲንዶቀዶቅ አይተህ እንደማታውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አስትንፋስ ያለውን ሰው በባዶ ሆድህ ስራ ማለት እንግዲህ ምን የሚሉት ስልጣኔ እንደሆነ እንጃ፡፡

ታዲያልህ በነጋታው ስራ አቁመን የድርጅቱ ትልቁ ኃላፊ ዘንድ ኸደን ‹‹ደመወዝ ይከፈለን›› ብለን አቤቱታ አሰማን፡፡ ሰውየው አለባበሳቸው ሸጋ፤ ቁመናቸው ሎጋና ደልደል ያሉ ጎልማሳ፣ እንደ ጨ()ስ አደመ ሸጋ ግርማ ሞገስ ያላቸው ናቸው፡፡ በቀለም ትምህርት ብዙ የዘለቁና ዘመናዊ አኗኗር ያበሰላቸው እንደሆኑ ገና አይኔ እንዳረፈባቸው ነበር የገመትኩት፡፡ ግምት ብቻ ሆኖ ሊቀር፡፡

እሳቸው ወዳጀ….ገና የነተበና ላም አመንዥካ የተፋችው የሚመስል የስራ ልብሳችንን እንደለበስን ከፊታቸው ቆመን ሲያዩ ‹‹እናንተ ደሞ ምንድር ናችሁ? እዚህ ምን ትሰራላችሁ?›› ብለው ፊታቸውን ቋጥረው አንድባንድ ባይኖቻቸው ገላመጡን፡፡ ረሀብና ብሶት ናላውን ያዞረው ሰራተኛ ሁሉም አቤቱታውን ያለወረፋ ያንደቀድቅባቸው ጀመር፡፡ የሳቸው ጆሮ ሁለት የሚንጫጫው ምላስ መቶ ሆኖ ነገርየው ቅጡን ማጣት ሲጀምር ሰውየው በቁጣ ሁሉንም ጸጥ አደረጉት፡፡ አየህ… የተቋጠረ ገንዘብና የተቋጠረ ቂም ባዶውን ከተከማቸ ሰውና ህግ ሳይፈረጥሙ አይቀሩም፡፡

ለጥቀው በቁጣ እንደጋሉ ‹‹ይህ የስራ ቦታ እንጅ የማንም ወሮ በላ መፈንጫ አይደለም፡፡ ለመሆኑ ከድርጅቱ ጋር ቀጥተኛ የስራ ውል ያለው አለ?›› ብለው ጠየቁን፡፡ እኛም የኛን አሰሪ ጠቅሰን ለድርጅቱ የሰራነውን አስረዳናቸው፡፡

ታዲያ እሳቸውም ‹‹በእርግጥ ድርጅቱ ከልጁ ጋር ተዋውሏል፡፡ ስለዚህ ግንኙነታችሁ ከእሱ ጋር እንጂ ይህ ድርጅት እናንተን አያቃችሁም፡፡ ለተሰራው ስራ ደግሞ በውላችን መሰረት ተገቢውን ክፍያ ፈጽመናል፡፡ እናንተም ጉዳያችሁን ከሱ ጋር ጨርሱ፡፡ አለበለዚያ እዚህ የስራ ቦታውን እንረብሻለን ብትሉ ፖሊስ ጠርቸ እያንዳንድሽ ትታጎሪያታለሽ፡፡››

ልጁ በእለቱ ስራ ቦታ አልመጣም፡፡ ስልክ ስናቃጭልለትም አይመልስም፡፡ ይህን ለሰውየው ተናግረን ሚበላ ሚጠጣ እንዳልቀመስን፣ ከኪራይ ቤታችን ተወርውረን ጎዳና ልናድር እንደሆነ ብናስረዳና መላ እንዲፈልጉልን ብንማጠናቸውም ‹ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ› ሆኑብን፡፡

መጨረሻ ላይ አዝነን ስንባዝን አንድ ሰው የሰራተኛ ጉዳይ ሚባል መስሪያ ቤት አለ ብሎ ቦታውን ጠቁሞን ወደዚያው አቀናን፡፡ እዚያም በደላችንን ስናስረዳ አንድ ጠልጠል ያለ ወጣት የህግ ምሁር ወረቀትና እስክረቢቶውን መዥልጦ የስልጣን ማስታወቂያ ካርዱን በሰለሎ አንገቱ አጥልቆና ደረቱ ላይ አንጠልጥሎ ‹‹ኑ ተከተሉኝ›› አለን፡፡ እኛም ልባችን በተስፋ እየደለቀች ወደ ግምባታ ቦታው አጅበነው ተጓዝን፡፡ እጥር ግቢው ስንደርስ ጥበቃዎች እኛን እንዳያስገቡ ጥብቅ ትዛዝ እንደተሰጠነግረው አሰቆሙን፡፡ ወጣቱ የሰራተኛ ጉዳይ ባለሙያ ‹‹ሁለት ተወካይ ምረጡና እኔና ተወካዮቻችሁ ገብተን ጉዳዩን እንጨርሳለን፡፡›› አለ፡፡ እገሌ ተወካይ ይሁን አይ እሱ ንግግር አይችልም እገሌ ይሁን በሚል ስንጨቃጨቅ አንዱ ያንዱን ምርጫ እያጣጣለ የጋራ መከራችንን ተረስቶ በማይረባ ነገር ልንባላ ደረስን፡፡

የህግ ባለሙያው በሁኔታችን እየተቃጠለ ‹‹ብትስማሙ ተስማሙ! አለበለዚያ ጥያችሁ እሄዳለሁ፡፡ መስሪያ ቤቴ እንደናንተ አገልግሎቴን የሚጠብቁ ብዙ አሉ፡፡›› ሲል ገሰጠን፡፡ እኛም ምርጫ ስናጣ ሁለት ሰዎች እንደነገሩ መርጠን ላክን፡፡ አንዱ ተወካይ እኔ ነበርኩ፡፡

የድርጅቱ ኃላፊ ቢሮ ስንደርስ ጠሀፊያቸው ወጣቱን የህግ ሰው ሰላምታ ሰጥታ እኛን ገላምጣ ‹‹ሰውየው ስብሰባ ገብተዋል›› አለች፡፡ ባለሙያው እንደሚቆዩ ወይም እንደማይቆዩ ጠይቋት እሷም እንደማታውቅ ነገረችውና ተቀምጠን ለመጠበቅ ተወሰነ፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ ተጎለትን፡፡ ችጋር ያጎሳቆላቸው ሰርተው የላባቸውን የተነፈጉ ቢጤዎቼም በር ላይ ተኮልኩለው ይጠብቃሉ፡፡ ስንቱ ድሀ እንዲህ እየተጉላላ ቅማል የማይገድል ስብሰባቸው ላይ ተጥደው በሰው ብሶት የሚሳለቁ ስንት አሉ መሰለህ ወዳጄ አያ ሻረው፡፡

ሁለት ሰዓት የሚሆን ጠብቀን ሰውየው ሊያናግሩን መጡ፡፡ አሁንም በዚያ ጨካኝ አይናቸው እያዩን ‹‹የህግ ሰው ይዛችሁ መጣችሁ? እናንተ ሰዎች ገደባችሁን አታውቁም፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት የላችሁም ስላችሁ አትሰሙም? ከህግ ባለሙያው ጋር መነጋገር እንችላለን፡፡ እናንተ ግን ከቢሮየ ውጡ፡፡›› አሉን፡፡

የህግ ሰውየው ሊያግባባቸው ሞከረ፡፡ <ወይ ፍንክች> አሉ፡፡ ባለሙያውም ምርጫ ሲጠፋ ‹‹ግድ የለም በቃ እኔ አናግራቸዋለሁ፡፡ እናንተ ውጭ ጠብቁኝ አለን፡፡›› እየከፋን ወጣንላቸው፡፡ ትንሽ ቆይተው ባለሙያውና ሰውየው እየተሳሳቁ ወጡ፡፡ ‹‹አየህ ድርጅታችን የአሰሪና ሰራተኛ ህጉን ብቻ ነው ተከትሎ የሚሰራው፡፡›› እያሉ ይደሰኩሩለታል፡፡

ወደኛ ተጠግተው አሁንም በንቀትና ጭካኔ እየገላመጡን ‹‹ጉዳያችሁን ተነጋግረን አንድ ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡ አሰሪያችሁን ተደዋውለን ጠርተን ደመወዛችሁን እናስከፍላለን፡፡ እሱ ካልተገኘ ግን እኔ የድርጅቱ ስም በእንዲህ አይነት ነገር እንዳይነሳ ስለምፈልግና ይህን የህግ ሰው ላለማድከም ስል በድርጅቱ ኪሳራ እንዲከፈላችሁ አደርጋለሁ፡፡ እዚህ የምትመጡት የዛሬ ሳምንት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ድርሽ እንዳትሉ፡፡ አይሆንም ካላችሁ ግን የፈለጋችሁት ፍርድ ቤት ድረስ መክሰስ ትችላላችሁ፡፡›› አሉን፡፡

የህግ ባለሙያውም ‹‹እኔ ልረዳችሁ የምችለው እዚህ ድረስ ነው፡፡ ሳምንት መጠበቅ ካልቻላችሁ የጠፋውን አሰሪያችሁን በፍርድ ቤት መጠየቅ ነው ያላችሁ አማራጭ›› ብሎን ውልቅ አለ፡፡

እናም ይኸውልህ ወዳጀ አያ ሻረው ዛሬን ምንበላው፣ምንጠጣው፣ ምናድርበት አጥተን የላባችንን ጠብታ ይዞ ዱካውን ያጠፋ ግፈኛ አሰሪያችንን እየረገምን በድርጅቱ ኃላፊ ቸርነት የሚሰጠንን ክፍያ ሳምንት እስኪደርስ እንጠብቃለን፡፡

እኔ ግን <ስራ ስራ ነው፡፡ ያለስራ ወትም አይደረስም> የሚል ፈሊጥ አለኝ፡፡ ይህን ታላሰብኩ በስተርጅና እዚህ ምን ልሰራ መጣሁ? ገንዘብ ቢጠፋ ህልም ግን አይጠፋም፡፡ ህልም ታለ ደግሞ ወኔ አይጠፋም፡፡ ወኔ ታለ ስራ አለ፡፡ ስራ ታለ ልቅምቃሚም ቢሆን ገንዘብ አይጠፋም፡፡ ያ…ጉፍንት አሰሪያችን አጭበርብሮ ጠፋ ብየ እድሜ ልኬን አንገት ደፍቸ ሳለቅስ አልኖር፡፡ ፍርድ ቤት ከሶ ለመከራከርም አቅም ያስፈልጋል፡፡ ሰውየውን ለመክሰስ አንቀጥ ጠቅሶ የሚጥፍ ሰው እንኳ ወጪው ደመወዙን ለተነፈገ ሰው ቅዠት ነው፡፡

ታዲያ ሁሉንም ትቼ ሰልስትና ትራንስቦርት ሰልፉ ላይ ተገትሬ አዲሱ ስራየ በግዜ ገባሁ አልገባሁ እያልኩ መጨነቁና መንቆራጠጡ ሳያንሰኝ ወረንጦ እጁን ወደ ደረት ኪሴ አሹሎ እየቆሰቆሰ እንደ ልጅነት ወዳጅ ከኋላየ የሚተሻሸኝን ሰውየ አፈር ድሜ ላስበላው ዞር ስል የአያ ጓሉ መቁረጫ ልጅ ደንገለው ሆኖ አላገኘው መሰለህ፡፡ ያብማይቱን ‹‹የማናባቱ ልኩን የማያውቅ ብቅብቅ ውርጋጥ ነው?›› ብየ በያዝኩት አካፋ ላቆነዳው ዞር ስል ደንገለው፡፡

ዛድያ ደም ፍላቴ ሁላ ጥሎኝ ብን አለ፡፡ ‹‹ኧሮግ እታታ፡፡ አንተ ነህ እንዴ ደንገለው? እኔ ደግሞ የማን ወሮ በላ ነው ብየ፡፡ አንተ… ኸምኔው እንዲህ ጠበደልህ?›› ብለው ትንሽ አንኳ ሳይደነግጥ ‹‹ሰውየ ምንድር ነው ምታወራው?›› ብሎኝ እርፍ፡፡ እንዲያው እጢየ ነው ዱብ ያለው፡፡ ኸሱ በኋላ የተሰለፉት ሰዎች ‹‹ማይኮ ትተዋወቃላችሁ? ምንሽ ነው?›› ብለው ቢጠይቁት ‹‹አላውቀውም›› ብሎ ሸመጠጠ፡፡ ደንገለው እንደሆነ ጥርጣሬ ባይገባኝም በከተማ ስም ስለጠሩት ትንሽ ተደናገረኝ፡፡

ከደንገለው ወደ ማይኮ ግን ትንሽ መንገዱ አላጠረም? እያልኩ እራሴን ስሞግት ወዲያው ከፊት ከኋላየ የተሰለፈው ህዝብ ‹‹ሞላጫ… ሌባ….የሚያ ውቅህ መስሎ ሊያታልልህ… ሊሰርቅህ ነው፡፡ አውቀው የገጠር ሰው እየመሰሉና ገና ከክፍለ ሀገር መጣን እያሉ የሚያጭበረብሩ በዝተዋል፡፡ ተጠንቀቁ›› እየተባባሉ ያም ያም ሲገለማምጠኝ ቆሌየ እንደተገፈፈ ሰልፉን ጥየ በእግሬ ማዝገም ጀመርኩልህ፡፡

እውነት እልሀለሁ ይህ ከተማ የማያሳየው ጉድ የለም፡፡ ደንገለው ካች አምና ሳውቀው ምላስ ነበር የሚያክል፡፡ አሁን እንደሰንጋ ሻኛ አውጥቶ፣ እናት አባቱ ያወጡለትን ስም በሰልባጅ ቀይሮና ኮረኮሯ ላይዋ ላይ እንደኮቸረባት የጎፈየች በግ ጠጉሩን አጎፍሮ የሰው ኪስ ሲጎረጉር ይውልልሀል፡፡ እንዲያው በራሴ ላይ ባይደርስ አላምንም ነበር፡፡ ደሞ እሱ ብቻ እንዳይመስልህ ስሙን የቀየረው፡፡ ቀያቸውን በለጋነታቸው ለቀው የመጡ ሴት ጉብላሊቶቻችን እነ ታንጉት ሁሉ አጓጉል የመሸታ ስራ ላይ ባክነው መቅረታቸው ሳያንስ ስማቸውም ‹ዚጢጢ ፣ቢጢጢ፣…› እየተባባሉ ምናለፋህ የ‹ጢ› ቅራቅንቦ ሆነውልሀል፡፡

እና ቀለም የዘለቀውና ቀለም የነካካው ተመሀይሙ ጋር ተደባልቀው ስልጣኔያቸውም ድንቁርናቸውም አልገባኝ ብሎ እንዲሁ እንደዠበረርኩ ቀረሁልህ፡፡ ወይኔ ሰውየው? ተመልሸ እንዳልመጣ እጀ ሞፈር መጨበጥ ረስቷል፡፡ እዚሁ እንዳልቀር ከነፋሱ እኩል መንፈስ አልቻልኩም፡፡ እንዲያው ምክር ቢጤ ካለህ እጠብቃለሁ፡፡

ወዳጅህ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።