የእኔ ሰኞ እና ዓርብ

07 Dec 2017

እስኪ በምኞት ወደኋላ ተመለሱ (ለምኞትማ ማን ብሏችሁ)፡፡ ተማሪ እያላችሁ ምን ነበር የምትመኙት? ሥራ መያዝ ነበር አይደል? አሁን እያንዳንዱ ሰራተኛ «ከሥራና ከተማሪነትተብሎ ቢጠየቅ «ተማሪነትነው የሚለው፡፡ ተማሪ ሆኖ እኮ «መቼ ይሆን የምገላገለው» ሲል የነበረ ነው፡፡

የሰው ልጅ እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡ የሚመኘው አሁን ያለበትን ሳይሆን ያለፈውን ወይም ገና ለወደፊት መሆን አለበት የሚለውን ነው፡፡ ተማሪ ሆኖ የትምህርት ጸጋ አይታየውም፤ ሰራተኛ ሆኖ የሥራ ጸጋ አይታየውም፡፡ ወደኋላ ተመልሶ የተማሪነት ሕይወቱን ይናፍቃል፤ ያመሰግናል፡፡ ያኔ የነበሩ ነገሮች ሁሉ የተለዩ ይመስሉታል፡፡

ወደኋላ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ያለ ነገርም አሁን ካለበት በላይ ይናፍቀዋል፤ ለምሳሌ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለን የሚናፍቀን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ መሆን ነው፤ ከዚያም መሰናዶ፡፡ የመሰናዶ ተማሪ እያለን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ በጣም ይናፍቀናል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ሥራ ስለሆነ ሥራ ለመያዝ እንቸኩላለን፡፡ በተለያዬ አጋጣሚ በመስሪያ ቤት ውስጥ የምናያቸውን የአሰራር ውጣ ውረዶች በጣም መተቸት እንጀምራለን፡፡ በሰራተኞች መሰላቸት በጣም እንፈርዳለን፡፡ «እኔ ሥራ ብይዝ ሰርቼ አልጠግብም ነበር» የሚል አቋም ይኖረናል፡፡

እንዲህ ሲል የነበረን ሰው ሥራ ይዞ ነው ማየት፡፡ ያንን ሲተችና ሲወቅስ የነበረን ነገር ሁሉ ራሱ ይተገብረዋል፡፡ ይሰላቻል፤ ያረፍዳል፤ ከዚያም አልፎ ይቀራል፡፡ ትምህርት ጨርሶ ሥራ ፍለጋ ላይ እያለ በአንድ ነገር በጣም ይናደዳል፤ ሥራ ይዘው ሥራ ለመቀየር አብረው ስለሚወዳደሩ ሰዎች፡፡ እሱም ሥራ ከያዘ በኋላ ግን መስሪያ ቤት ሲቀያይር ይኖራል፡፡ በጋዜጦች ላይ ከሚወጡ አገራዊ ጉዳዮች ይልቅ የሚወጡት ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎች ቀልቡን ይስቡታል፡፡

ከብዙ መግቢያ በኋላ እንዴት ናችሁ? ታውቃላችሁ አይደል አንዳንዴ ነገር ነገር የሚለው ሰው? ከሰላምታ በፊት ነገር የሚያስቀድም፡፡ የሆነው ሆኖ እንዴት ናችሁ? ያለፈው ሰኞ እንዴት ነበር? የነገው ዓርብ እንዴት ነው?

ሰኞና ዓርብ በተማሪና በሰራተኛ ዘንድ ትልቅ ቦታ ነው ያላቸው፡፡ ምነው ለተማሪና ለሠራተኛ ብቻ? አይ! ለተማሪና ሰራተኛ ነው፡፡ የነጋዴ ልዩ ቀን ቅዳሜና እሁድ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የዕረፍት ቀናት ስለሆኑ ሰዎች የሚሸማምቱት ቅዳሜና እሁድ ይሆናል ብዬ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ይገርመኛል(መቼም አንዱን ይዤ አንዱን መልቀቅ ነው)፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች እሁድ እሁድ ሱቃቸውን ይዘጋሉ፡፡ ሰዎች ዕረፍት የሚኖራቸው ቅዳሜና እሁድ ስለሆነ በእነዚህ ቀናት አትዝጉ ለማለት ነው፡፡

ወደ ሰኞና ዓርብ እንመለስ፡፡ ቆይ ቆይ! ከዚያ በፊት የቅዳሜና እሁድ ነገር ይለቅ፡፡ ቅዳሜና እሁድ ለካ ለነጋዴ ብቻ ሳይሆን ለሰካራምም ልዩ ቀናት ናቸው ነው (እነርሱስ ለምን ይቅርባቸው?) ቅዳሜና እሁድ(በተለይ ቅዳሜ) የስካር ቤቶች የሚደምቁበት ነው፡፡

ወደ ሰኞና ዓርብ ልመለስ (ተመላለስኩ እንጂ!)፡፡ ሰኞና ዓርብ በተማሪና በሰራተኛ(በተለይም በመንግሥት ሰራተኛ) ልዩ ቀናት ናቸው፡፡ ሰኞ በጣም በመጠላት ዓርብ በጣም በመወደድ፡፡ እንዲያውም ሰኞን ፈረንጆች እንኳን ሳይቀር «Black Monday» ይሉታል እየተባለ ይታማል፡፡ ቆይ ግን እነርሱ ሥራ ይወዳሉ አልተባለም ነበር እንዴ? ታዲያ ለምን ሰኞን ጥቁር እያሉ ይጠሉታል? ለነገሩ መዝናናትስ የሚወዱ እነርሱ አይደሉ?

የእነርሱን ሀሜት እንተወውና በተጨባጭ ስለሚታየው የአገራችንን ነገር እናውራ፡፡ ሰኞ በተማሪም በሰራተኛም በጣም ይጠላል፤ ዓርብ ደግሞ በተማሪም በሰራተኛም በጣም ይወደዳል፡፡ ይህ ሁኔታ በተማሪም በሰራተኛም የስንፍና ምልክት ነው (እሺ! የግል አስተያየቴ ይሁን)፡፡ እንደኔ ይህ የለየለት ስንፍና ነው፡፡ ሰነፍ ተማሪ ሰኞ ሲመጣ በጣም ይጨንቀዋል፡፡ ምክንያቱም ዓርብ የተሰጠው የቤት ሥራ ይታያል፤ በዋናነት ደግሞ ሰኞ የሳምንቱ የትምህርት መጀመሪያ ነው፡፡ የቤት ሥራ፣ የክፍል ሥራ፣ ክፍል ውስጥ የመምህሩ ጥያቄ ይኖራል፡፡

በተቃራኒው ዓርብ ደግሞ ቅዳሜና እሁድን አስከትሎ ስለሚመጣ በጣም ይወደዳል፡፡ ሰነፍ ተማሪ ለሁለት ቀናትም ቢሆን ከትምህርት ይገላገላል(ያው ሲራገጥ ለመዋል ነው)፡፡

ወደ ሰራተኞች እንሂድ! በተመሳሳይ ሰራተኞችም ሰኞን ይጠሉታል፤ ዓርብን ይወዱታል፡፡ ይሄም የስንፍና ምልክት ነው፡፡ ሰኞ የሳምንቱ የሥራ መጀመሪያ ቀን ነው፡፡ ለተከታታይ አምስት ቀን በሥራ ላይ ይቆያል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰራተኞች ሰኞ ሲመጣ በጣም ይጨነቃሉ፡፡ አንዳንዱ ሥራ አጥቶ «ምነው 24 ሰዓት በሰራሁ» ይላል፤ አንዳንዱ ደግሞ ሥራ እየሰለቸው ያማርራል፡፡ ሰኞ ጠዋት እኮ የብዙ ሰው ፊት የጨፈገገ ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ዓርብ ደስታ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መጪው ቅዳሜና እሁድ የእረፍት ቀናት ስለሆነ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአንዳድ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ቅዳሜ እስከ ምሳ ሰዓት የሥራ ቀን መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ባንኮችማ ሙሉ ቀን መደበኛ የሥራ ቀናቸው አድርገውታል፡፡ ነገሩ ምን ያድርጉ? እነርሱማ መሥራት ያለባቸው ቅዳሜ እኮ ነው፡፡ ያ ዓርብን በጉጉት ሲጠብቅ የነበረ ሁሉ ሲያጠራቅም የከረመውን ወጣ አድርጎ ፈታ ለማለት ይመቸዋል፡፡

ነገሩ ዓርብ ከሰዓት ነው የሚጀምረው፡፡ እስኪ አንዳንድ መስሪያ ቤቶችን ልብ ብላችኋል? «ዓርብ ከዚህ ሰዓት በኋላ አገልግሎት አንሰጥም» የሚል ማስታወቂያ ለጥፈዋል፡፡ ዓርብ ከሰዓት አገልግሎት ለማግኘት ከሄዳችሁ፤ አቤት ያለ ግልምጫ (በእርግጥ ሌላ ቀንም የሚገላምጡ አሉ)፡፡ በተለይ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ለመውጣት ያለ መተራመስ፤ ጦርነት ለመሸሽ እንጂ ሥራን ለመሸሽ ሰው እንዴት ይሮጣል?

ለመሆኑ የኔ ሰኞና ዓርብ እንዴት ነው? በእውነት የኔ ሰኞና ዓርብ ይለያል፡፡ በቃ ከላይ ካልኳቸው ነገሮች በተቃራኒው ነው፡፡ ሰኞን በጣም እወደዋለሁ፤ ዓርብን በጣም እጠላዋለሁ(እስኪ «ጉረኛ» ለማለት አትቸኩሉ)፡፡ ይህ የሆነው ጎበዝ ተማሪና ታታሪ ሰራተኛ ሆኜ አይደለም፡፡ የራሱ ምክንያት አለው፡፡

ተማሪ እያለሁ ገነትን(ገጸ ባህሪ ናት ብያለሁ) በጣም እወዳት ነበር፡፡ እሷን የማየት ዕድል ያለኝ ትምህርት ቤት ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ አስቡት! በጣም የምትወዱትን ሰው አለማየት ምን ያህል እንደሚከብድ፡፡ ስለዚህ ዓርብ ሲመጣ በጣም ነበር የምጠላው፡፡ ለሁለት ቀን ያህል ገነትን አላያትም ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ የሰኞ ደስታ ደግሞ እሁድ ከሰዓት ይጀምረኛል፡፡ ሰኞን በደስታ ወደ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ፡፡

ትንሽ ጉራ ስጨምርበት ደግሞ ጎበዝ ተማሪም ነበርኩ፡፡ ዓርብ የተሰጠውን የቤት ሥራ በደንብ አድርጌ ከሰራሁ ሰኞ ክፍል ውስጥ የሚጨበጨብልኝ ይናፍቀኛል፡፡ ሁሉም ተማሪ ያቃተውን ጥያቄ ከሰራሁ የበላይነት ይሰማኛል፡፡ ክፍል ውስጥ ባለኝ ተሳትፎ ቲቸር ዘሪሁን(ይሄም ገጸ ባህሪ ነው) ስሜን እየጠራ ሲያደንቅ ገነት መስማቷ ደስ ይለኛል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሰኞ አዳዲስ ምዕራፍ ስለሚጀመር ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ምዕራፍ ጨርሰን ወደ አዲስ ልንገባ ስንል «ሰኞ ከዚህ ምዕራፍ እንጀምራለን» ይላል ቲቸር ዘሪሁን፡፡ የመማሪያ መጻሕፍቴን አንዳንድ ጊዜ ወደፊት ያሉ ምዕራፎችንም አየው ነበር፡፡ እናም ወደፊት የምንጀምረው ምዕራፍ በጣም ያጓጓኛል፡፡

ለመሆኑ አሁንስ በሥራ ላይ እያለሁስ ሰኞን ለምን ወደድኩት? ዓርብን ለምን ጠላሁት? ይሄም የራሱ ምክንያት አለው? ከመስሪያ ቤት ፍቅር ይዞኝ ይሆን? ቆይ በመሃል ሌላ ነገር እናውራ(ሃሃሃሃ ቀልብ አንጠልጣይ ፊልም አሉ)፡፡

ሥራ ላይ ሆኜ ሰኞን የወደድኩት ዓርብን የጠላሁት በሥራ ፍቅር አይደለም(በገነት ፍቅርም አይደለም)፡፡ ዓርብን በጣም የምጠላው ቤት ላለመቀመጥ ነው፡፡ ቆይ ግን ቤቴ ለምን አስጠላኝ? ለነገሩ ቤቴ ሳይሆን ያው የአከራዬ ቤት ማለት ነው፡፡ እናም ከቤት ስቀመጥ አከራዬ አንድ ነገር ማለቷ አይቀርም፡፡ «ቢያንስ ቢያንስ መብራት ለምን ታበራለህማለቷ አይቀርም፡፡ በዚያ ላይ እኔን «ድምጽ ከፍ ማድረግ ክልክል ነው» ቢሉኝም ከነሱ ቤት ግን ገደብ የሌለው ድምጽ ይለቀቃል፡፡ የሰዎችም፣ የሙዚቃውም፣ የቴሌቪዥኑም ድምጽ ሲረብሸኝ ይውላል፡፡ ታዲያ ቤቴ እንዲህ ካስጠላኝ ሌላ የት ልሄድ ነው? ስካር ቤቶችን ስለማልወዳቸው(የምር ይህን እንኳን ኮራ ብየ ነው የምናገር) ቅዳሜና እሁድ በጣም ይሰለቸኛል፡፡ ለዚህ ነው ዓርብን የምጠላው፤ ሰኞንም የምወደው!

እንግዲህ በዚህ አጋጣሚ በሥራ ገበታዬ ላይ ሁሌም ስለምገኝ በተዘዋዋሪ እመሰገንበታለሁ ማለት ነው፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።