ሳምንቱ በታሪክ Featured

05 Jan 2018

የ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ 93ኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ የተመሰረተው (ለሕትመት የበቃው) ከ93 ዓመታት በፊት፣  (ታኅሳሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም) ነበር፡፡

አንጋፋው ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም በንጉሥ ተፈሪ መኮንን (የኋላው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) መኖሪያ ግቢ ውስጥ ጨው ቤት በሚባለው ባለ ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ስራውን ጀመረ፡፡ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተባለውን ጋዜጣ ማተም ሲጀምር ስሙንም ከዚሁ ጋዜጣ ወረሰና ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› ተባለ፡፡ ይህም ማተሚያ ቤቱ ጋዜጦችን እንዲያትም (የማተም አገልግሎት እንዲሰጥ) አስቻለው፡፡ 

‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ  በ500 ቅጂዎች ያህል በሳምንት አንድ ጊዜ (ሐሙስ ዕለት) ይታተምና ይሰራጭ የነበረው በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ጋዜጣው ሲመሰረት (ከ1917) ጀምሮ እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ የጋዜጣው ዲሬክተር (ዋና አዘጋጅ) የነበሩት አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት የተባሉት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ በ1921 ዓ.ም አቶ ማኅተመወርቅ እሸቴ የጋዜጣው ዲሬክተር (ዋና አዘጋጅ) ሆኑ፡፡   

አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን ጊዜው ለኢትዮጵያ የብርሃንና የደስታ እንዲሆን በመመኘት (በማሰብ) የጋዜጣውን ስያሜ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ብለው እንደሰየሙት ይነገራል!

ብርሃንና ሰላም!      

ተፈስሒ ኢትዮጵያ ሀገረ ገነት፣ እስመ በጽሐ ብርሃንኪ ወራሲ መንግሥት

አንተነህ ቸሬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።