ጦርነትን ማስቆም የቻለ ታሪካዊ የገና በዓል Featured

13 Jan 2018

ያኔ ከዛሬ አንድ መቶ አራት ዓመታት በፊት፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1914 የገና ሰሞን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ የፈረንጆቹ 1914 በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሁሌም በክፉ የሚታወሰው አውሮፓ ውስጥ ጀምሮ መላ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍሎ እርስ በእርስ ያጫረሰው አስከፊ ጦርነት የጀመረበት ዓመት ነው፡፡ ሐምሌ 28 ቀን 1914 ልዑል አርክዱክ ፍራንሲስ ፈርዲናንድ የተባለ የአውስትሮ ሃንጋሪ መንግሥት ዙፋን አልጋ ወራሽ የሰርቢያ ዋና ከተማ ሳራይቮ ላይ በመገደሉ ምክንያት ይህ የበርካታ ሚሊዮኖችን ህይዎት በመቅጠፍ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትና በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳን ጥሎ ያለፈው አንደኛው የዓለም ጦርነት የጀመረበት ቀን ነው፡፡

ጦርነቱ ከተነሳበት ዕለት ጀምሮ በመጀመሪያዎቹ ሰላሳ ቀናት ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችና ሰላማዊ ዜጎች በማለቃቸው የፈረንጆች ገና ከመድረሱ በፊት ጦርነቱ እንደሚቆም የብዙዎች ተስፋ ነበር፡፡ ሆኖም ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ውጊያው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሁለቱም ጎራ ያሉ ጦር መሪዎች ለወታደሮቻቸው ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ጦርነቱ ተባብሶ ቀጠለ፡፡ በታነንበርግ፣ በማርንና በፐርስ የጦርነት ግንባሮች ታይቶ የማይታወቅ ዘግናኝ ዕልቂትን ያስከተለ ጦርነት ተካሄደ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታህሳስ 24 ቀን 1914 ዓ.ም በፈረንጆቹ የገና ዋዜማ ምሽት ላይ ግን ማንም ይሆናል ብሎ ያላሰበው፤ ይህንን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂ የሆነውን መጥፎ ጊዜ በበጎ እንዲታወስ የሚያደርግ ፈጽሞ ያልተጠበቀ፣ ግሩም ድንቅ ትዕይንት ተከሰተ፡፡ በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ሲጨፋጨፉ የዋሉ አንዳንድ የጀርመንና የብሪታኒያ ወታደሮች ጠብ-መንጃቸውን እየጣሉ ከየምሽጋቸው ወጥተው አንድ ላይ ተሰባስበው የገና መዝሙርን መዘመር ጀመሩ፡፡ ከሰዓታት በፊት በጠላትነት እርሳስ ሲለዋወጡ የነበሩ ወታደሮች ለጥይት መከላከያ የለበሱትን የብረት ቆብ እያወለቁ በወዳጅነት ስጦታ ተለዋወጡ (በገና ዋዜማ ስጦታ መለዋወጥ የአውሮፓውያኑ ልማድ ነበረና የሚሰጡት የስጦታ ዕቃ እንኳን ያልነበራቸው ምስኪን ወታደሮች ቆባቸውን በስጦታነት በማበርከት አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን ፍቅር ገለጹ)፡፡
ቀኑን ሙሉ ክፉኛ ሲገዳደሉ የዋሉ ባላንጣ ወታደሮች ማታ አንድ ላይ ተቀምጠው ኮቾሯቸውን እየበሉ፣ በፍቅር እየተጫወቱና እየጨፈሩ የ1914ቱን የገና በዓል አከበሩ፡፡ ይች የገና ዋዜማ ምሽትም በዚያ ሞት በነገሰበት አስከፊው የአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በበጎ የሚወሳ ደማቅ ታሪክ የተጻፈባት ልዩ ቀን ናት፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ታሪኩ የተፈጸመው አውሮፓ ውስጥ በአውሮፓውኑ የገና በዓል ዕለት ቢሆንም ፍቅር የሁሉም የሰው ልጆች ሃብት ነውና የጠላትነት ምሽግ በፍቅር ተደርምሶ፣ ጦርነት ቁሞ የዋለባትን ያችን ልዩ ቀን ሁሉም ያስባታል፡፡ የወገንና የጠላት ወታደሮች አንድ ላይ ሆነው ሲደሰቱ የዋሉባትን ያችን የፍቅር ቀን ይኸው እኛም ዛሬ በራሳችን የዘመን ቀመር ላይ ሆነን ገናን በምናከብርበት ዕለት አሰብናት፡፡
የዚህ አስደናቂ ታሪክ ተካፋይ ከነበሩ ወታደሮች መካከል አንዳንዶቹ ለጋዜጦችና ለፍቅረኞቻቸው በጻፏቸው ደብዳቤዎች ጦርነቱን አቁመው በዓሉን በጋራ ለማክበር የወሰኑባትን ያችን ልዩ የገና ዋዜማና የበዓሉን ውሎ እንደሚከተለው ገልጸዋታል፡፡
“የገና ዕለት ጓደኞቼ ከጀርመኖች ጋር ሆነው በምሽጎቻችን መካከል ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጠረንጴዛዎችን አስተካክለው በጋራ ተቀምጠው እየተጫወቱና በዓሉን የሚያስታውሱ ትንንሽ ስጦታዎችን እየተለዋወጡ ደስተኛ ጊዜያትን አሳልፈዋል” አንድ ብሪታኒያዊ ወታደር የፃፈው፡፡
“እጅግ በጣም የተለየ የገና በዓል ነው ያሳለፍኩት፤ እናም ለወደፊቱም ቢሆን ከምሽግ ወጥቼ በዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት ምርጥ ጊዜ የማሳልፍበት የገና በዓል ይኖረኛል ብየ የማላስብበት ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ” ሌላኛው የብሪታኒያ ወታደር ለፍቅረኛው የፃፈው ማስታወሻ፡፡
አንድ ሌላ ወታደር ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “ያን ቀን በዋዜማው ምሽት በዓሉን በጋራ ለማክበር ከተስማማን በኋላ፤ ወዲያውኑ በአምስት ደቂቃ ውስጥ በጠላት ጦር ምሽግ መካከል ያለው ክፍት ቦታ በብሪታኒያውያንና የጀርመን ወታደሮች ተሞላ፡፡ ወታደሮቹ ሲጋራና ሌሎች በርካታ ትንንሽ የስጦታ ዕወቃዎችን ይለዋወጡ ነበር”፡፡
የሁለቱም ወገን ወታደሮች ሰፍረውባቸው በነበሩ አንዳንድ የጦር ካምፖች አካባቢ ደግሞ ጓደኛሞች እርስበእርሳቸውና ከ“ጠላት” ጦር ወታደሮች ጋር እግር ኳስ እየተጫወቱ አሳልፈዋል፡፡ ጨዋታውን አስመልክቶ የብሪታኒያ የመኮንኖች ጦር የህክምና ክፍል ኃላፊ ለንደን ውስጥ ለሚኖር አንድ ወዳጁ በጻፈው ደብዳቤ፤ “ብርጌዳችን ከጀርመን ወታደሮች ጋር ጨዋታ አድርጎ ሦስት ለሁለት በሆ ውጤት አሸንፏል” ብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ የሁለቱም ወገን ወታደሮች በቤተ ክርስቲያናት እንደሚደረገው ዓይነት የጸሎትና የፍትሃት ሥርኣት በማከናወን የሚካሄደውን በጦርነቱ የሞቱባቸውን ጓደኞቻቸውን ቀብረዋል፡፡
በዚያች የ1914ቷ የገና ዋዜማ ምሽት የነበረውን ጦርነትን አቁመው ገናን በጋራ አክብረው የዋሉ ወታደሮችን አስደናቂ ትዕይንት ከሁሉም በላይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው አገላለጽ ግን ጥር 5 ቀን 1915 በወጣው የእንግሊዙ ካርልስል ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣው አንድ ብሪታኒያዊ ወታደር የላከው ደብዳቤ ነው፡፡ ደብዳቤው እንዲህ ይላል፤
“ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በመካከላችን ሰፍኖ እርስ በእርሳችን ሲያተላልቀን የቆየው ያ ሁሉ የጥላቻ መዓት የገና በዓል በፈጠረው ተዓምራዊ የፍቅር ኃይል በአንድ ጊዜ ጸጥ አለ፡፡ በሁለት ተቃራኒ ኃያላኖች ጎራ ተሰልፈው፣ ዘላለማዊ ጥላቻ ያላቸው ይመስል፤ በጠላትነት እየተያዩ በከፍተኛ ጥላቻና ቂም ተመርዘው፤ መራራ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀው፣ እርስ በእርስ ሲባሉ የነበሩ ባላንጣዎች በገና ዕለት ጥላቻቸውን በፍቅር ለውጠው የፍቅር ስጦታ እየተለዋወጡ፤ የፍቅር ዜማን እየዘመሩ አንድ ላይ መዋላቸው ለዓለማችን የወደፊት ሰላም ታላቅ ተስፋን ይዞ የሚመጣ ግሩም ድንቅ ትዕይንት የታየበት ቀን ነው” ፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ለቢዚነስ ኢንሳይደር ያካፈሉት የአንደኛው የዓለም ጦርነት መታሰቢያ ሙዚየም የትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሚስ ሎራ ቮግት በበኩላቸው፤ “ድርጊቱ ዛሬም ጦርነት ውስጥ ለሚገኙ አገሮችና እንደ ሰው ለሚያስቡ ሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ የሚያስተላልፈው ትልቅ የጋራ መልዕክት አለው” ይላሉ፡፡ “ሁሌም የገና በዓል በመጣ ቁጥር ለሰብዓዊነታችን ቅድሚያ ከሰጠን ጥላቻ ሊያሸንፈን እንደማይችልና በፈቃዳችን ከጦርነት ልንወጣ እንደምንችል እንድናስብ ለህሊናችን ያስታውሰናል”፡፡
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በተቃራኒ ጎራ የነበሩ ወታደሮች በዚህ ሁኔታ ለአንድ ቀንና ለአንድ ሌሊት ጦርነቱን አቁመው የ1914ቱን የገና በዓል አንድ ላይ ሆነው ካከበሩ በኋላም ከነ ጭራሹ ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ደም ያሰከራቸው የበላዮቻቸው ግን ጦርነቱ እንዲቆም ባለመፈለጋቸው የተቋረጠው ጦርነት እንደገና እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ የበላዮቻቸውን ትዕዛዝ አልቀበልም ብለው ጦርነቱን አልቀጥልም ያሉ ወታደሮችም ከነበሩበት ብርጌድ ወደ ሌላ ግንባር እንዲዛወሩ ተደርገዋል፡፡ ሌላ የተለያየ ቅጣትም እንዲቀጡ በመደረጋቸው በግዳጅ ጦርነቱን ቀጥለዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በወታደሮች ዘንድ አንድም ተመሳሳይ ጦርነትን የማቋረጥ ሙከራ ሳይደረግ ለአራት ዓመታት የዘለቀው የአንደኛው የዓለም ጦርነት ህዳር 11 ቀን 1918 ይፋዊ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
ያም ሆኖ ዕድሜ ለእነዚያ ልባቸው በጦር ሳይሆን በፍቅር ተማርኮ ጦርነት አቁመው አብረው ለዘመሩ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ወታደሮች ልብን በሚሰብረው የአንደኛው የዓለም ጦርነት ጥቁር ታሪክ ውስጥም የሰውነትን ዋጋ ከፍ የሚያደርግ ልብን በደስታ የሚሞላ ዛሬም ድረስ የማይረሳ ድንቅ ትውስታ ጥለውልን አልፈዋል፡፡ እናም ዛሬ ሁሌም በክፉ የሚወሳውን የአንደኛው የዓለም ጦርነትን የ1914ን የገናን ዜማን በደም ሳይሆን በፍቅር ባሳለፉት በእነዛ (የፍቅር ጣዖቶች ልንላቸው የሚቻለን) እንዲህ በበጎ አስታውሰነዋል፡፡
ፈጣሪ ፍቅርን ያብዛልን!

ይበል ካሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።