የ‹‹አይፎኑ›› ጣጣ Featured

13 Feb 2018

ብዙ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ከእጃችን አምልጠው መሬት ላይ ሲወድቁ የመሰበር እድል ቢገጥማቸ ውም ቢያንስ የማስጠገኑና ዳግም በእጃችን የማስገባቱ እድል ይኖረናል፡፡ ከእጃችን አምልጥው መፀዳጃ ቤት የሚገቡ ስልኮችን ግን ምን ልናደርግ እንችላለን?
ኦዲቲ ሴንትራል የተሠኘው ድረ ገፅ ባሳለፈነው አርብ ለንባብ ያወጣው ፅሁፍ እንደሚያሳየው የእርሶ ስልክ መፀዳጃ ቤት ቢገባ እንዴት ማውጣት እንደሚችሉ የሚመክር ሳይሆን እንደውም እጅዎን አጣጥፈው እንዲቀመጡ የሚያሳስብ ይመስላል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ታንግ የተሰኘው ቻይናዊ የጉዋንዚ ክልል ነዋሪ ከጓደኞቹ ጋር በአካባቢው በሚገኝ አነስተኛ ሆቴል ውስጥ መጠጥ እየጠጣ ባለበት ወቅት መፀዳጃ ቤት መሄድ ያስፈልገዋል:: ወደዛውም ያመራል፡፡ በመፃዳጃ ቤቱ ውስጥ እያለ ስልኩን ማየት ይፈልጋል:: ሰውየው ግን ትንሽ ሞቅ ብሎት ኖሮ ውዱ አዲሱ አይ ፎን ስልኩ ከእጁ አምልጦ መፃዳጃ ቤት ቀዳዳ ውስጥ ይገባል፡፡
ታንግ አይፎን 8 የተሰኘውን ስልኩን ገና በቅርቡ እንደገዛውና 8 ሺ ወይም ደግሞ 1 ሺ 300 የአሜሪካን ዶላር እንዳወጣበት ዘገባው ገልፆ፤ ስልኩ ወደ መጸዳጃ ቤቱ በገባበት ቅፅበት ጎንበስ በማለት እጁን ወደ መጸዳጃ ቤቱ ቀዳዳ ይሰዳል፡፡ ስልኩ ላይ መድረስ ባለመቻሉም እጁን እስከ ትከሻው ድረስ ወደ ውስጥ ይለቀዋል፡፡ታንግ ስልኩ ላይ በእጁ ለመድረስ እንዳልቻለና ይልቁንም እጁ እዛው የመፀዳጃ ቀዳዳ ውስጥ ተሰንቅሮ እንደቀረ ይረዳል፡፡
ሰዎች እርዳታ እንዲያደርጉለት ጥሪ ማድረጉ በጣም አሳፋሪ መሆኑን የተረዳው ታንግ፣ እጁን ከመፀዳጃ ቤቱ ቀዳዳ ለማላቀቅ 20 ደቂቃ ፈጅቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ እጁ የባሰ እየተጣበቀ በመሄዱ ከቀዳዳው ውስጥ ለመውጣት እርዳታ የግድ እንደሚያስፈልገው ይረዳል፡፡ ኩራቱንና እፍረቱን ወደጎን በመተውም የእርዳታ ጥሪ ማቅረብ ይጀምራል፡፡ ይህን የእርዳታ ጥሪ የሰማው የፅዳት ሰራተኛ ወደ መፀዳጃ ቤቱ በማምራት ታንግን ይመለከተዋል፡፡ ወዲያውም ለአካባቢው የድንገተኛ አደጋ ክፍል ስልክ ይደውላል፡፡
ዘገባው ሲቀጥልም የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች የታንግን እጅ ከመፀዳጃ ቤቱ ቀዳዳ ለማላቀቀ መቀመጫውን እስከ መፈንቀል ደርሰዋል ይላል ዘገባው፡፡ የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች የታንግን እጅ ከቀዳዳው ማላቀቅ የቻሉ ቢሆንም ውዱን አይ ፎን 8 ስልክ ግን ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ምስጋና ታንግ ለተዝናናበት ሆቴል ይግባና ሆቴሉ ታንግ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የሚከፍለው በመሆኑ ዳግም የአይፎን 8 ስልኩን ገዝቶ በእጁ ያስገባል ሲል ዘገባው አጠናቋል፡፡

 አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።