የደመወዝ ሰሞን Featured

11 Mar 2018

የሆነውስ ሆነና ዛሬ ቀን ስንት ነው? እኮ መጋቢት ከገባ ሁለት ቀን ሆነው? ሰሞነ ሁዳዴ ሊገባ ምን ቀረው ታዲያ? ሀብታም እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ በል! ሰሞነ ሁዳዴ የተባለው የያዝነው የሁዳዴ ጾም እንዳይመስልህ (ደግሞ እኮ መገጣጠሙ)፡፡ ሰሞነ ሁዳዴ የተባለው የደመወዝ ሰሞን ያልሆነው የወሩ አጋማሽ አካባቢ ነው፡፡ ‹‹ለመሆኑ የወሩ መጨረሻ አካባቢ ምን ይባላል?›› ካልከኝ ሰሞነ ፍስሃ፣ ሰሞነ ፋሲካ ይሉታል(ምን ይሉታል ነው እንለዋለን ልበል እንጂ)
ቆይ ግን ትክክለኛው የደመወዝ ቀን ከመቼ እስከ መቼ ያለው ነው? እንግዲህ ይሄ እንደየ መስሪያቤቱና እንደየአካባቢው ሁኔታ ይለያያል (ትልቅ ጉዳይ የምተነትን አስመሰልኩት አይደል?)፡፡ ለነገሩ ከዚህ በላይ ምን አለ?
አንዳንድ መስሪያ ቤት ከ23 እና 24 አካባቢ ጀምሮ ደመወዝ ይከፈላል፤ አንዳንድ መስሪያቤት ደግሞ ቀጣዩ ወር እስከሚገባ ሁሉ ሊዘገይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ስለ ሰሞነ ደመወዝ ብናወራ ጉዳዩ ወቅታዊ ነው ማለት ነው (ዛሬ የሚቀበልም ይኖራል)፡፡ እንዲያውም ዛሬ ደመወዝ ለምትቀበሉ ምክር ነገር አለችኝ፡፡ ይሄን ምክር ዝም ብየ ከሜዳ ተነስቼ የጻፍኩት አይደለም፡፡ ለዓመታት ያህል ደመወዝ በማባከን ያከበትኩትን ልምድ መነሻ በማድረግ ነው (ልብ በሉ በማባከንም ልምድ ማካፈል ይቻላል)፡፡ለማንኛውም ምክሩ ወደ መጨረሻ አካባቢ ነው (ደግሞ ዘላችሁ መጨረሻ ላይ እንዳትሄዱ)፡፡
ያዝ እንግዲህ! መቼስ የደመወዝ ሰሞን አይደል? አቤት እኮ የደመወዝ ሰሞን ያለ ግርግር፡፡ እኔ እኮ ግርም የሚለኝ የዚያን ሰሞን ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የ «ኤቲኤም» ማሽኖች ሁሉ ቀልባቸው መጥፋቱ ነው፡፡ አንዳንዴ ንግድ ባንክ ‹‹ብር ገብቶልሃል›› ብሎ የላከልህን መልዕክት «ኤቲኤም» ላይ ሄደህ ስታይ ‹‹ባክህ ውሸት ነው›› በማለት ተስፋህ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ይቸልስበታል፡፡ በኋላ ግን ነገሩ ሲጣራ ቅርጥፍ አድርጎ የዋሸው ራሱ ማሽኑ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ያስቀኛል፡፡ ብዙ ብር አውጥቼ እኮ ነው፤ ሌላ ቀን የቀረችዋን ለማውጣት ስጠይቀው ድሮ የነበረውን ጨምሮ ‹‹ይህን ያህል ብር አለህ›› ይለኛል፡፡ እንዴ! ማን ጨመረልኝ ብየ ለማውጣት ሳዝዘው ‹‹ባክህ ስቀልድ ነው›› ይለኛል፡፡
የንግድ ባንክ «ኤቲኤም» ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመራት የዜማ ግብዣ ተመችታኛለች፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ… ሁሌም ሁሌም… የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ›› ይላል፡፡ እንዴት ከኋላዬ ሰው ቆሞ እጨፍራለሁ ብዬ እንጂ ዜማዋን ግን እዚያው ቆሜ እየሰማሁ ወዝ ወዝ ማለት ያምረኝ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው የደመወዝ ሰሞን ነው፡፡ ሌላ ጊዜ መንገድ ላይ «ኤቲኤም» ሳገኝ የተኳረፍን ይመስል የጎሪጥ ነው የማየው፡፡ ያ የካርዱ ማስገቢያ ላይ ያለው አረንጓዴ መብራት ቦግ ቦግ ቦግ ሲል ሳየው እንዴት እንደምቀና፡፡ ብር ባይኖረኝ ራሱ የ«ኤቲኤም» ማሽኑ ተበላሽቶ ካየሁት ያናድደኛል፡፡
በነገራችን ላይ ባንኮች ግን ሀብታምና ድሃ ለይተው አያውቁም ማለት ነው? ደመወዝ ሲገባ በገባው ብር መጠን የሎቶ ቁጥር በስልኬ ይልኩልኛል፡፡ የባንክ ሠራተኞች እንደነገሩኝ ዕጣውን ለመጠበቅ ብሩ መውጣት የለበትም (እኔ እንደሆንኩ የገባ ዕለት ነው የምጀምረው)፡፡ ገና አንዴ እንዳወጣሁ ‹‹አንዱ የሎቶ ቁጥር ከሸፈ›› ይለኛል፡፡ አሁንም ሳወጣ ‹‹አሁንም ሌላኛው ከሸፈ›› ይለኛል፡፡ ቆይ ግን ምንም ብር ሳያወጣ ዓመት ሙሉ ይጠብቀኛል መስሎት ነበር? ‹‹እኔ የምሞት ዛሬ ማታ፤ ገብስ የሚደርሰው ለፍልሰታ›› አለች አሉ፡፡ ገና ለገና መኪና አገኛለሁ ብዬ እንዴት ልቆይ ነው?
እንዴት ነው የደመወዝ ሰሞን? ስልካችሁ የሚሴጅ ድምጽ ባሰማ ቁጥር አትደነግጡም? ውይ ይሄ በ80 ምናምን የሚጀምር ቁጥር እንዴት ደሜን እንደሚያፈላው! እኔ የCBE ሚሴጅ መስሎኝ ሰፍ ብዬ ሳይ ‹‹የፍቅር ጓደኛ ይፈልጋሉ? መኪና ይፈልጋሉ? ቤት ይፈልጋሉ? ምክር ይፈልጋሉ?...›› ኧረ ምን የማይባል ነገር አለ! CBE ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያበሳጨኝ ነው፡፡ ብር ሲገባልኝ ቶሎ መልዕክቱን አይልክልኝም (ኧረ ጭራሽ የሚተውበት ጊዜም አለ) ብር ሳወጣ ግን እዚያው ኤቲኤም ማሽኑ ሥር እያለሁ ነው ‹‹አውጥተሃል›› የሚለኝ፡፡ ይሄንማ ባይነግረኝስ እስተዋለሁ እንዴ!
ወይ የደመወዝ ሰሞን ብዙ አስወራን እኮ፡፡ በወሩ አጋማሽ ሰሞን ቢሆን እኮ ይህን ሁሉ አላወራም ነበር፡፡ የዚያን ሰሞንማ ምን አደርጋለሁ መሰላችሁ? ያለኝ ብር በ«ኤቲኤም» መውጣት ስለማይችል የባንክ ደብተር ይዤ ነው የምሄደው፡፡ አቤት እዚያ እንዴት እንደማፍር! ሰው እንዴት 50 ብር ለማውጣት ሠራተኞችን ሥራ ያስፈታል? እኔማ ‹‹ለዚህ ነው እንዴ ሥራ ያስፈታኸኝ?›› ይሉኛል እያልኩ አይን አይናቸውን ነው የማየው (ደግነቱ ብለውኝ አያውቁም)፡፡ ደግሞ እኮ የባንክ ሠራተኞች ምሥጢር ጠባቂነታቸው ደስ ሲል! ያቺን 50 ብር በደብተሩ ውስጥ አድርገው ነው የሚሰጡኝ፡፡ ማየት የለ፣ መቁጠር የለ፣ ተቀብዬ ዞር ነው፡፡
የምር ግን ባንክ ቤት ውስጥ ከሀብታም ጋር መሰለፍ እንዴት እንደሚሰለቸኝ! በዚያ ላይ ጣጣቸው አያልቅ፡፡ እኔ አንድ ወይም ሁለት መቶ ብር ለማውጣት ቦርሳ ሙሉ ብር እስከሚቆጠር ድረስ መቆም አለብኝ እንዴ? እሺ ብር ቆጠራውስ ይሁን፤ የባንክ ደብተራቸው ላይ የሚሞላው ነገርስ ምን ሆኖ ነው ያን ያህል የሚያቆየው?
የምክሯን ነገር ረሳኋት አይደል? ‹‹ምክርና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው›› አሉ፤ ለመሆኑ ይህን ምክር እኔ ተግባራዊ አድርጌው ይሆን? እዚህ ላይ አንድ ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ ሰውየው ‹‹ሚሊየነር ለመሆን የሚያግዙ ዘዴዎች›› የሚል መጽሐፍ ጻፈ አሉ፡፡ ከዚያማ ማሳተሚያ ገንዘብ አጥቶ ሳይታተም ቀረ፡፡ ለነገሩ ምክር እኮ የግድ መካሪው የተገበረው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የሲጋራን ጎጂነት ለማስተማር የማያጨስ ሰው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እንዲያውም ጉዳቱን በደንብ የሚያውቀው ተጠቃሚው ሲሆን ነው፡፡ ቆይ ግን ይህን ያህል ማግባቢያ የኔ ምክር ምን ሆኖ ይሆን? በአንድ ቃል ሲጠቃለል «አታባክን!»
የምር ግን የደመወዝ ሰሞን ሀብታም የሆንን የሚመስለን ለምንድነው? የማያልቅ የሚመስለን ለምንድነው? ኧረ ብሩም እኮ ችግር አለበት፡፡ የተገዛው ነገር ሳይታወቅ የብሩ ማለቅ ብቻ ነው የሚታወቀው፡፡ እንዲያው አናውቀው ብለን እንጂ እሱስ ሳይገዙበት አላለቀም፡፡ ዋናው ነገር ያ የተገዛው ነገር ምንድነው ነው?
በነገራችን ላይ እኔን ያስቸገረኝ ‹‹ደግሞ ለአሥር ብር፣ ደግሞ ለሃምሳ ብር፣ ደግሞ ለመቶ ብር›› የሚባል ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ልብስ ልገዛ አስቤ ‹‹እዚህ ቦታ የተሻለ ነው›› ሲሉኝ ‹‹ኤዲያ! ደግሞ ለመቶ ብር ብዬ፣ ደግሞ ለሁለት መቶ ብር ብዬ›› እያልኩ በቀላሉ የማገኘውን እገዛለሁ፡፡ አስቡት ስንፍና እንዴት እንደበደለኝ፡፡ መቶና ሁለት መቶ ብር አሁን ለኔ ቀላል ነበር?
ምግብ ቤት ስገባ ራሱ ያላሰብኩትን ነው በልቼ የምወጣው፡፡ መጀመሪያ የምገባው ሻይ በዳቦ ለመብላት ነው፡፡ ቀጥሎ ሀሳቤን ወደ ፍርፍር እቀይረዋለሁ፡፡ አሁንም የምግብ ዝርዝር ካየሁ በኋላ እንደገና ወደ ጥብስ ወይም ዱለት (በፍስክ ወቅት ማለቴ ነው) እቀይረዋለሁ፡፡ አስቡት እንግዲህ! በሁለትና በሦስት ብር የታሰበው ቁርስ በሀምሳና በስልሳ ብር ይጠናቀቃል፤ ኧረ ቆይ ገና ነው፡፡ ምግቡ ሲመጣ አስተናግጇ መጥታ ‹‹የሚጠጣ ነገር ምን ይምጣ?›› ትለኛለች፡፡ ሰው ምናለ አቅሙን አውቆ የብርጭቆ ውሃ ቢያዝዝ? ለነገሩ እዚህ ላይ እንኳን የምግብ ቤቶችም እጅ አለበት፡፡ ‹‹የቧንቧ ውሃ›› የለም ሊሉም ይችላሉ፡፡ መቼም ሰው ምግብ እየበላ የሚጠጣ ነገር ሳይዝ አይሆንም፡፡
ሆኖም ግን ጥፋቱን ሙሉ በሙሉ እነርሱ ላይ ብቻ አልዘፈዝፍም፤ የኔም እጅ አለበት፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የታሸገ ውሃ ማዘዝ አለብኝ፡፡ ይሄ ደግሞ ለጤናም ለኢኮኖሚም ጠቃሚ ነው፡፡ እንዲህ መሆን ሲገባው ግን ሚሪንዳ፣ ኮካ፣ ላዝዝ እችላለሁ፡፡ ኧረ አለፍ ካለ እነ ስም አይጠሬንም ላዝዝ እችላለሁ፡፡
ሌላ የደመወዝ ሰሞን ትዝታ አለ? ‹‹አንተው እንደጀምርክ ጨርሰው እንጂ!›› አላችሁኝ? ዋናውን አይደል እንዴ እንዲያውስ የተውነው፡፡ እስኪ ‹‹ደሞዝ ሲወጣ›› ብሎ ያልተበደረ አለ ይሆን? የዱቤ ዕቃ ያልገዛ አለ ይሆን? የጎረቤት ባለሱቅ ሸሽተህ መንገድ ቀይረህ አታውቅም? እዚህ ላይም ምክር አለኝ (ምነዋ እንደ ሽማግሌ ምክር አበዛሁ) ይሄም በአጭሩ ሲጠቃለል «የዱቤ ዕቃ አትግዛ!»
የብድሯ ነገርስ? ብድር እንዲያውም የዱቤ ዕቃ ከመግዛት የባሰ ነው፡፡ ዱቤ እኮ ቢያንስ በዕቃው ታስታውሰዋለህ፡፡ ብድር ግን ምኑም ሳይታወቅ የመመለሱ ጊዜ ነው የሚደብረው፡፡ እዚህም ላይ የራሴን ተሞክሮ ላካፍላችሁ፡፡ አልበዛም እንዴ ግን? ገንዘብ አባካኝ እኔ፣ የዱቤ ዕቃ ገዢ እኔ፣ ብድር ተበዳሪ እኔ፤ ይህን ያህል ምን ዕዳ አለብኝ? ትቸዋለሁ ከራስህ ተማር!

ዋለልኝ አየለ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።