ልመና ለሴቶች!

13 Mar 2018

የዚህ ጽሑፍ ርዕስ ‹‹ምክር ለሴቶች›› መባል ሲገባው ዳሩ ግን ነገሩ ከምክርነት ወደ ልመናነት የሚያደላ ስለሆነ ‹‹ልመና ለሴቶች›› ብየዋለሁ፡፡ ተለማኝ ሴቶች ናቸው፡፡ ለማኙስ ማነው? ለሚለው ጽሑፉን ማንበብ ነው (ማን ሊሆን ይችላል ደግሞ ወንዶች ነን እንጂ!) የምር ግን ለማኙ እኔ ነኝ፡፡
ዛሬ ሴቶችን ላደንቅ ነው የተነሳሁት፤ ቅር የሚለው ወንድ ካለ የሴቶችን ብቃት ይለማመድና በቀጣይ ደግሞ እሱን አደንቃለሁ፡፡ እውነቴን ነው ሴቶችን በጣም ላመሰግን ተነስቻለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሰሞኑ ድባብ እንዴት ነበር? የ‹‹ማርች ኤይት›› ድባብ ማለቴ ነው? ኧረ ቆይ አሁንም ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ቅሬታ አለኝ፡፡ (ዝም ብሎ አድናቆት ብቻ ይገኛል እንዴ?)
‹‹ማርች ኤይት›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል እንዴት አገራዊ ስያሜ አጣ? ቢያንስ ቢያንስ ‹‹መጋቢት ስምንት›› ብንለው እንኳን ምን ነበር? ወይም ደግሞ በዕለቱ በሚውለው የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መሰየም አይቻልም? ‹‹ማርች ኤይት›› ምን እንደሆነ የሚያውቁት የተማሩት ብቻ ናቸው፡፡ የሚገርመው እኮ ደግሞ የዚህ ቀን መከበር በዋናነት የትምህርት ዕድል ላላገኙና የጉልበት ብዝበዛ ለሚበዛባቸው ሴቶች ነበር፡፡ ቃሉን የሚያውቁትማ እኮ በዕኩልነት የሚያምኑ ናቸው፡፡ አሁን አንዲት የጉልበት ብዝበዛ የሚበዛባት የገጠር ሴት ‹‹ማርች ኤይት›› ምንድነው ብትባል ምን ትላለች?
ወደ ዋናው ጉዳይ ተመልሰናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ምን መሰላችሁ? ባሳለፍነው ሳምንት የሴቶች ቀን ተከብሮ ነበር፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ስለሴቶች ብዙ ነገርም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ (አይዟችሁ እነርሱ ያሉትን አልደግምም)፡፡ ታዲያ እኔስ ለምን የመሰለኝን አልልም? እንደማመጥ እንግዲህ ሴቶች፡፡
ሴቶች ወንድ ማድረግ የማይችለውን ብቃት አላቸው፡፡ የትኛውም የስነ ልቦና ባለሙያ፣ የህክምና ባለሙያ፣ የህግ ባለሙያም ሆነ የጦር ኃይል ማድረግ የማይችለውን ያደርጋሉ፡፡ ይሄ እሙን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ማድረግ የቻሉት ግን በሴቶች ጠንካራነት ብቻ ሳይሆን በወንዶች ደካማነትም ጭምር ይመስለኛል፡፡ (ማነህ እንዳትቆጣ)፡፡
ወደ ምክሬ (ልመና በሉት ካሻችሁ) ስገባ ሴቶች እባካችሁ ወንዶችን ልክ አስገቡልን የሚል ነው፡፡ በጣም እውነት ለመናገር ወንድን ልክ የምታስገባው ሴት ናት፡፡ በመሆኑም ወንዶችን ስነ ሥርዓት ለማስያዝ ወንዶች ላይ ከመስራት ይልቅ ሴቶች ላይ መሥራት የተሻለ ነው፡፡ ‹‹ሴት የላከው ጅብ አይፈራም›› የተባለው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ሴቶች በየመድረኩ የሚነገርባቸውን ጎጂ ምሳሌያዊ አነጋገር ሲያወግዙ ‹‹ሴት የላከው ጅብ አይፈራም›› የሚባለውን ግን ልብ አላሉትም፡፡ እነርሱ ደግሞ ችግራቸው ስለሴት እኩልነት ባወሩ ቁጥር ማውገዝ ላይና ሮሮ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ነው፡፡
እናም ‹‹ሴት የላከው ጅብ አይፈራም›› ወንድ ለሴት ልጅ በጣም ብዙ ነገር ይሆናል፡፡ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ምስቅልቅል (ለጊዜው ፖለቲካውን አይደለም) የተፈጠረው ሴቶች ያላቸውን ብቃት ስላልተጠቀሙበት ነው፡፡ የባለትዳሮች ወዲያውኑ መፋታት፣ የወንዶች አስረግዞ መክዳት፣ በኑሮ መጨቃጨቅ፣ እርስበርስ ለመጠፋፋት መሞካከር የተፈጠረው በወንዶች ሳይሆን በሴቶች ጥፋት ነው፡፡ ማለቴ ጥፋታቸው ችሎታቸውን አለመጠቀማቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ሴት እንኳን የትዳር ጓደኛዋን ሌላውን የማግባባትና ሰላም የማድረግ ችሎታ አላት፡፡ ይህ የሚሆነው ግን በዘዴ ነው፡፡
ቀለል ቀለል ያሉ ምሳሌዎች ላንሳ፡፡ ለብዙ የትዳር መፍረስ ምክንያቱ የወንዶች ጠጪነት፣ አጫሽነት፣ ቃሚነት… ነው፡፡ ይሄ ቀላል ችግር አይደለም፡፡ በቤት ውስጥ አለመስማማትን ያመጣል፤ የባህሪ መነጫነጭን ይፈጥራል፤ በጣም ሲከፋም ስንፈተ ወሲብ ይፈጥራል፣ የዘር መምከንን ያመጣል፡፡ ይሄ ሆኖ ደግሞ ትዳሩ ትዳር አይሆንም፡፡ ሌላው ሱስ ቀርቶ መጠጡ ብቻ ቢሆን እንኳን ከሌላ ሴት ጋር መማገጥን ያመጣል፡፡ ይህም መጠራጠርንና መጨቃጨቅን ይፈጥራል፡፡
ሴት ልጅ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማስቀረት ትችል ነበር፡፡ አንድ ወንድ የሚወዳት ሴት እንኳንስ ጫትና ሲጋራ ‹‹ምግብ ተው›› ብትለው ይተዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ የማውቀው ገጠመኝ አለኝ፡፡ (የሆነች ልጅ ናት የነገረችኝ፡፡) ልጁ በጣም ይወዳታል፡፡ በግንኙነታቸው ውስጥ ጫት እንደሚቅም ደረሰችበት፡፡ በጣም እንደምትወደውና ጫቱን ካልተወው ግን በፍጹም አብረው እንደማይሆኑና እንዲያውም ለሻይ ቡና እንኳን እንደማታገኘው ነገረችው፡፡ ለአፍታማ ሳያቅማማ ነው ጫቱን እርግፍ አድርጎ የተወው፡፡ ምንም እንኳን አሁን አብረው ባይሆኑም እንደ እህትና ወንድም ይተያያሉ፤ ዛሬ ድረስ ከልብ ያመሰግናታል፤ ያደንቃታልም፡፡ ልጅቷም አብረው እንደማይሆኑ እያወቀች ጫቱን ለማስተው የተጠቀመችው ዘዴ ነበር፡፡ ጎበዝ ሴት ማለት ለኔ እንዲህ ነው፡፡
እዚህ ላይ ይልቅ ትልቁ ችግር አንዳንድ ሴቶች ደግሞ አራዳ የሚባል ወንድ መውደዳቸው ነው፡፡ እነርሱ ‹‹አራዳ›› የሚሉት ደግሞ የሚቅምና የሚያጨስ ነው፡፡ አንድ ወንድ የሚወዳትን ለማግኘት የማያደርገው ነገር የለም፡፡ በአራዳነቴ ትወደኛለች ካለ እንኳንስ ጫት ሌላም ነገር ሊበላ ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ይሄ የብዙ ሴቶች ባህሪ አይደለም፤ እውነቱን እናውራ ከተባለ ግን የጀማሪ አራዳ ሴቶች ባህሪ ነው፡፡ በቃ ሱሪውን ዝቅ የሚያደርግ፣ ጸጉሩን የሚጎናጉን፣ የሚቅምና የሚያጨስ ወንድ ይወዳሉ፡፡ ስንቱ ወንድ እኮ የተበላሸው አራዳ የሆነ እየመሰለው ነው፡፡
አብዛኞቹን ሴቶች ካየን ግን መጠጥ፣ ጫትና ሲጋራ የሚጠሉ ናቸው፡፡ ይሄ ሆኖ ሳለ ግን ወንዶች ከዚህ እንዲላቀቁ ጥረት አላደረጉም፡፡ ‹‹ለምን እነርሱ የተለየ ዘመቻ ማድረግ አለባቸው?›› ከተባለ ማስቆም የሚችሉት እነርሱ ስለሆኑ ነው፡፡
በእውነት እስኪ ሴቶች የሚቅምና የሚያጨስን ወንድ ያግልሉና በአንድ ዓመት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ ቃሚና አጫሽ ባይጠፋ! አሥር ሳይንቲስት ‹‹ሲጋራ ገዳይ ነው!›› ከሚል ይልቅ አንዲት ሴት ‹‹ዞር በል አታጭስብኝ›› ብትለው እርግፍ አድርጎ ይተወዋል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ይባል ይሆናል፡፡ የሚያጨስንና የሚቅምን ሰው ‹‹ዞር በል፣ አታጭስብኝ›› ማለት ነውር ነው፤ ክብር ይነካል ይባል ይሆናል፡፡ ማጨስና መቃም እኮ የፈጣሪ ቁጣ አይደለም፤ ከላይ የወረደ መዓትም አይደለም፤ በራስ መተማመን በማጣት የመጣ ነው፡፡ እስኪ እነዚህ ታዋቂና ተወዳጅ ናቸው የሚባሉት ያውግዙትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ባይቆም!
ማንም ትሁን ማን ለምትቀርበው ወንድ ይህን ዘመቻ ብትጀምር ነገሩ ቀላል ነበር፡፡ ማንም ወንድ እንኳን የሚፈልጋትን ሴት የየትኛዋንም ሴት ወሬ ይወዳል፡፡ (አንወሻሽ ጎበዝ!)፡፡ ‹‹አንተ ይሄን ጭስ ይዘህ ሁለተኛ እንዳታናግረኝ›› ብትለው ያፍራል፤ ይተወዋል፡፡ ወንድ እንደዚህ ቢለው ግን ክንዱን ሰቅስቆ ነው ለድብድብ ነው የሚነሳው፡፡
ሴቶች ግን ልብ ብላችሁኛል? ‹‹ትችላላችሁና ወጣቱን ከሱስ አውጡት›› ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ በመጠጥ፣ በጫትና ሲጋራ እናንተ የተመሰገናችሁ ናችሁ፤ አትወዱም፡፡ (አጫሽና ቃሚ ሴቶች ቢኖሩም እንደ ወንዶች አይደለምና ብዙዎችን አይወክልም)፡፡ ይሄን ሥራ ሰራችሁ ማለት ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ትልቅ አገራዊ ሥራ ነው፡፡ ‹‹እንደ ጫትና ሲጋራን እንደ ትልቅ አጀንዳ ያወራል›› የሚል ካለ ተሳስቷል፡፡ ጫትና ሲጋራ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው፤ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ነው፤ ማህበራዊ ጉዳይ ነው፤ ከምንም በላይ ደግሞ የጤና ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን አስቀራችሁ ማለት እንግዲህ ምን ልበላችሁ! በቃ ሕይወት አዳናችሁ ማለት እኮ ነው፡፡ ተግባባን?
እናም እላለሁ! እባካችሁ ሴቶች ማድረግ ትችላላችሁና ይሄን ቅጠላ በላ ወንድ ልክ አስገቡልን!

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።