የደም ምርመራ በእራት ግብዣ ላይ Featured

15 May 2018

አሁን ያለንበት ወቅት የሰርግ እንዲሁም የተለያዩ ዝግጅቶች የሚከናወኑበት እንደመሆኑ እዚህም እዚያም «ጸበል ቅመሱ፤ የደስታችን ተካፋይ ይሁኑ» የሚሉ ግብዣዎች በርካታ ናቸው። ታዲያ በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ ሲኬድ ለድግሱ ድምቀት የተዘጋጁትን የተለያየ ይዘት ያላቸውን ምግቦች መቀማመስም አይቀረም። አንዳንዶቹ ለጤናችን የማይስማሙን ቢሆኑም እንኳን እንደው «ጠሪ አክባሪ» እያልን መውሰዳችን ግድ ይለናል።
ግብዣውን በሰላም አጠናቅቀን ወደ ቤታችን ከገባን በኋላ ስለሚገጥመን የጤና ችግር ግን የምናውቅም የማናወቅም እንኖር ይሆናል፤ ይህ በምን ይሉኝ የተተበተበው የእራት ፕሮግራምም ምናልባትም የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ አዳራችን አልያም ማምሻው በሆስፒታል አልጋ ላይ ሊሆንም የመቻሉ ሁኔታ እጅግ የሰፋ ነው። ይህ ይሉኝታ እኛ አገር ብቻ ያለ ይመስላል፤ በሌሎች አገራት ግን እንዲህ አይነቱ እምብዛም የሚታይ አይደለም፡፡ ምንም ዓይነት ግብዣዎች ሲከናወኑ በመጀመሪያ የብዙሀኑን የጤና ሁኔታ ያማከለ ብሎም የማይስማማ ነገርም ሲታይ ያለምንም ሀፍረት የሚተውበት ሰርዓትም ያዳበሩ በመሆናቸው እንደ እኛ ተጎጂ ላይሆኑ ይችላሉ።
ኦዲቲ ሴንትራልም ‹‹ይህንን መሰሉን ችግር የሚቀረፍ መላ ያመጡ አሉ›› ሲል ያስነበበውን እንዲህ አቅርበነዋል። ዘገባው፣ እነዚህ ማህበራዊ ዝግጅቶች ጤናማና ወዳጅ ዘመድም በነጻነት በልቶና ጠጥቶ እንዲሁም ተዝናንቶ ወደ ቤቱ ከሄደም በኋላ ባሳለፈው ቀን ተደሳች እንጂ ታማሚ እንዳይሆን የሚያደርግ መላም ከጤና እድገት መጎልበት ፓርቲዎች መዘጋጀቱን ያብራራል ።
ዘገባው፣ በመሰል ዝግጅቶች ላይ እየተገኙ የተጋባዦችን የደም ናሙና እየወሰዱና የሚስማማቸውን የምግብና የመጠጥ አይነት እየመረጡ በቀጣይ በጤናቸው ጉዳይ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያሳመኑ የሚሰሩት ስራም በተለይ በእንግሊዝ እየተወደደ መምጣቱን ያብራራል።
ምናልባት አንድ አስደሳች የእራት ግብዣ ላይ ‹‹ስለ ኮሌስትሮል መጠን፣ ስለ ካሎሪና ቫይታሚኖች ማውራት ምናልባትም ደባሪ ሊሆን ይችላል›› የሚሉት ፓርቲዎቹ፣ ሆኖም ስለ ጤናዎ በሚገባ የሚጨነቁ ከሆነ ይህንን ማድረግ ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም በማለትም አስፈላጊነቱን ያስረዳሉ።
ይህንን ተከትሎም በቅርቡ ለንደን ውስጥ በገበያ ቦታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጤና የተሻለ ማሻሻያ የሚያደርግ የፓርቲው አገልግሎት ተጀምሯል። በዚህም ለተዘጋጁት እሽግ ምግቦች እያንዳንዱ ሰው 250 ፓውንድ (337 ዶላር) የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ በዚህ ቦታ ላይም እስከ ስምንት እንግዶች ማስተናገድ ይቻላል። ልክ እንደ ቋሚ የምሽት ክብረ በዓላትም የሚካሄድ ሲሆን በተዘጋጀው ቤት ውስጥ በመሰባሰብና እራት ከመብላትና መጠጦችን ከመውሰድ በፊት ምናልባትም ለሁለት ሰዓት በዚህ በመቆየት የደም ናሙና መስጠት ያስፈልጋል ፤ ከዚያም ለኮሌስትሮል፣ ለታይሮይድ እክል፣ ለቫይታሚኖች እጥረት ምን ያህል የተጋለጡና የበሽታው ምልክቶች ምን ያህል ይታዩበታል የሚለውም ይታያል።
የእንግዶቹ ደም ከተሰበሰበ በኋላ መጨረሻ ላይ አንዳንድ መጠጦች እና ጥሩ ምግብ ይታዘዛሉ፤ የአመጋገብ ሳይንቲስቱ ቶታል ሻህ፣ ለእንግዶቹ እንደ ወቅታዊው ሁኔታ ብዙ ፕሮቲን እና ጤናማ እፅዋትን ያካተተ የምግብ አይነቶችን ያቀርባሉ። በተጨማሪም ስለ ሁሉም የአመጋገብ እና የግል ጤንነት እንዲሁም ስለ የተመጣጠኑ ምግቦች ይዘት ለሁሉም ሰው ንግግር ያደርጋሉ። በዚህ መካከልም ስለጤናማ አመጋገብ ብሎም ስለ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጥያቄዎች ያሏቸው ሰዎች እንዲጠይቁ በመጋበዝ ሰፊ ወይይቶችም እንደሚደረጉ ዘገባው አመላክቷል።
እነዚህ በምርመራው የተሳተፉ ሰዎች ወዲያው የሚስማማቸውን እራት እንዲመገቡ እንጂ ውጤታቸውን አንዲያውቁ አይደረግም። ምክንያቱም መጀመሪያ ውጤታቸውን ለማየትና ለመቀበል ዝግጁ መሆን ስላለባቸው ነው። ሆኖም ውጤቱ ተዘጋጅቶ ለሼፉ (ምግብ አዘጋጁ) በ30 ደቂቃ ውስጥ ይደርሳል። ፍቃደኛ ለሆኑትም ውጤታቸውን የመስጠትና ምን ዓይነት የኑሮ ዘዬን መከተል እንዳለባቸው በመምከረም ምሽቱ እንደሚጠናቀቅ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የ41 ዓመቷ ወይዘሮ ሻሀ በሰጡት አስተያየትም፤ ይህንን የጤና ፓርቲ በተለይም ከ 35 እስከ 50 ዓመት ያላቸው ሁሉ እጅጉን ይፈልጉታል ማለታቸወንም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

እፀገነት አክሊሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።