መተሳሰብ ለጋራ ኑሮ

15 May 2018

ድሮ ድሮ ሰዎች በተለይም በጉርብትና ሲኖሩ «አንቺ ትብሽ እኔ» ተባብለውና ተቻችለው ይኖሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ይህ መተሳሰብ በመጠኑም ቢሆን የተጓደለ ቢመሰልም ሙሉ በሙሉ ደግሞ የለምም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜም ቢሆን ጉርብትናቸው ማስተማሪያ ሊሆን የሚችልና በአርአያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰዎች ዛሬም ድረስ በመኖራቸው ነው።
ሆኖም በተለይም አሁን አኗኗራችን በጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) የሆንን ሰዎች ይህ ማህበራዊ መስተጋብር ሲጓደል እናስተውላለን፡፡ በተለይ ደግሞ አንዳንዱ ለሌላው መብትና ሰላም የማይጨነቅ ከመሆኑም በተጨማሪ በርካታ አዋኪ ነገሮችን ሲያደርግ መመልከት የተለመደ ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች ሲያጋጥሙ ግማሹ በሀይለ ቃል ወይም በጸብ፣ ሌላው ደግሞ ‹‹መቼስ ምን ይደረግ ጎረቤትም አይደሉ›› በማለት ሲተላለፉ ማየት የሚዘወተር ጉዳይ ነው፡፡
በጋራ መኖሪያ ቤቶች ከተከለከሉ ወሳኝ ነገሮች መካከል ሙዚቃን ከልክ በላይ በመክፈት ሌሎችን እንዲረበሽ ማድረጉና በቤት ውሰጥ ከሚከወኑ ተግባራት ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው አልያም የሚወቀጥ ነገር መስራት ይጠቀሳሉ። ሆኖም በአንዳንድ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቡናውም ይወቀጣል፤ ሙዚቃውም ይከፈታል፡፡ ኧረ ምኑ ቅጡ! ብቻ ‹‹ማስቻሉን ስጠኝ›› ብሎ መኖር ካልሆነ በቀር በርካታ አላስፈላጊ ነገሮች ይከወናሉ።
ኦዲቲ ሴንትራል እንዳስነበበው፤ ዩናይትድ ኪንግደም የምትኖረው የ48 ዓመቷ ሄዘር ዌብ ቢያንስ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በምትኖረው ህንፃ ውስጥ አስፈሪ የድመት ድምጽ አስመስላ በማውጣት ጎረቤቶቿን ጮክ ብላ አስፈራርታለች። እኤአ በ2014 ጎረቤቶቿ ፀረ-ማኅበራዊ ባህሪ ቅጾችን ሞልተው ወደ አካባቢያዊ ምክር ቤት ቢልኩም፤ ከፖሊስ የማኅበረሰብ ጥበቃ ማስጠንቀቂያ ብቻ መጥቶላት ታልፋለች።
እኤአ በ2016 ደግሞ ጎረቤቶች እንደገና ሴትየዋ ስትዘፍን ድምጿ ከፍተኛና አሰቃቂ መሆኑን ለጉባኤው ቅሬታ አቅርበዋል፤ ሆኖም በሴትየዋ ላይ ምንም እርምጃ አልተወሰደም። በመጨረሻም በታህሳስ ወር ዳኛ ዌቢን በአፓርታማዋ ውስጥ እንዳትዘፍን በሕግ የታገደች የወንጀለኛ ባህሪ ትዕዛዝ አውጥቶባታል ሲል ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።