ጠብ ሲል...

16 May 2018

ቀኑን ሙሉ ስታቃጥል የዋለችው ጸሀይ ወደ አመሻሹ ቀዝቀዝ ማለት ጀምራለች።እንዲህ ሲሆን ደግሞ አብዛኛው ሰው አዋዋሉን እያስታወሰ «እፎይ» ይላል። የቀኑን ሙቀትና ጭንቀትም እያነሳ በእጅጉ ይወያያል።ሁሌም ቢሆን እንዲህ መሆኑ ተለምዷል።የእኛ ነገር ዝናብ ሲሆን ማማረር፣ ሙቀቱም ሲመጣ ያው ማማረር ነው። ይህ ደግሞ ከየወቅቱ ለውጥ ጋር ይቀያየራልና ብርቅ አይደለም።
እንዳልኳችሁ ገና በማለዳው አምርራ ስታማርር ያረፈደችው ጸሀይ ማርፈጃዋን መለስ ቀለስ ስትል ውላ ፤ ሄዳለች ሲባል ርቃ ያለመራቋን ልታሳይ የብልጭታዋን ፈገግታ ለሁሉም አዳርሳለች። የፀሃይዋን መምጣትና መሄድ በወጉ ተረዳን ያሉቱ ቀለል ያለ ልብስ ለብሰዋል። ለወትሮም ዝናብ ካላጉረመረመ መያዝ የማያስቡትን ዣንጥላ ወዲያ ጥለውም ሌጣቸውን ናቸው።
መቼም ወዳጆቼ! እንዲህ በሆነ ሰሞን እግረኛ ሆኖ አለመገኘት ነው። በተለይማ ከአውላላው መንገድ፣ ከጥርጊያው ጎዳና ንፋስ ከዛፍ ጥላ ብርቅ ሲሆን ፤ ከእመት ጸሀይ ጋር ግብግብ መግጠሙ ቀላል አይሆንም። የሰላምታ ያህል በቅኝቷ ብትጎበኝዎ አናትዎን ማዞር አይደለም ያሉበትን ቦታ ሁሉ ሊያስረሳዎ ይችላል። በውስጥዎ የሚፈጠረው ግራ አጋቢ ስሜት ነጭናጫ ያደርግዎታል።
ምንም ይሁን ምን ግን እመት ጣይቱ ማምረር ካሰበች የሚያስቆማት የለም።ከአናት እስከ እግር ጥፍር በሚዘልቅ ኃያል ጉልበቷ ያሻትን ብታደርግ ማን ሊከለክላት። በዚህ ጊዜ ማንም ምንም ማድረግ አይቻለውም። ላቡን እያንጠፈጠፈ ድካሙን ከማስታመምና እንደተለመደው ከማማረር ሌላም ምርጫ ላይኖረው ይችላል። ለነገሩ በአውላላው የጎዳና ጉዞ በጸሀይ ጉልበት ከመሸነፍ ውጭ ምን ምርጫ ሊኖር ይችላል? ምንም።
አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ ሲያስጨንቅ የሚውለው ቀን በድንገት ባህርይውን ይቀይርና ደርሶ ግራ ያጋባል። ዳመናው በሰማይ ሳይታይ ከየት መጣ የማይሉት ዝናብ ዶፍ አስከትሎ ያጥለቀልቃል። ይሄኔ ታዲያ መንገደኛውም ይሁን ከቤት ያለው የሚይዝ የሚጨብጠውን ያጣል። ድንገቴው ዝናብ ቃጠሎውን አባሮ ሁሉን ማተራመስ ሲይዝ ድንግርግሩ አጀብ ያሰኛል።
በዚህን ጊዜ ከቤት የዋለው ከደጅ የተወውን ሊያስገባ፣ ከውጭ ያሰጣውን ሊሰበስብ ሩጫና ጥድፊያው ያይላል።በዚህ አጋጣሚ ሁሉም የኔ የሚለው አጣዳፊ ጉዳይ ይኖረዋልና ለሌላው እገዛ ላይደርስ ይችላል። ሌላውም ቢሆን ከዝናቡ ድንገቴ ጥፋት እንዲታደጉት የጎረቤቶቹን አስቸኳይ እርዳታ አይፈልግም።ያለ የሌለ ሀይሉን ተጠቅሞ በዝናብ የሚበላሹ ቁሶችን በጥድፊያ ይሰበስባል። ይህ የሚሆነው ግን ምንአልባት ዝናቡ የአፍታ ጊዜ ከሰጠውና የመታገስ ምልክት ካሳየው ብቻ ነው።
መቼም ይህኛው እውነት ድንገቴው አጋጣሚ የፈጠረው ክስተት ነው ይባል።እንዲህ ከሆነ አጋጣሚው የሚያስከትላቸው የተለመዱ ለውጦች ከተጠቃሚው እርምጃ ጋር ሊታዩ ይችላሉ። እኔ ግን ሁሌም ቢሆን ግርም የሚለኝ ሀይለኛ የሚባል ዝናብ ጥሏል በተባለ ቀን የሚከሰተው ችግር ብቻ አይደለም። ለእኔ አስገራሚውና አናዳጁ ጉዳይ ጥቂት ዝናብ ጠብ ሲል በከተማው የሚታየው የባህርይ ለውጥ ነው።
ወዳጆቼ! አበው ሲተርቱ «ክፉ ቀንን አያምጣ» ይላሉ። እነሱ እንዲህ ለማለታቸው የራሳቸው የሆነ ብዙ ምክንያት ይኖራቸዋል። እኛ የአባባሉን ስጋት እንገምት ከተባለ ደግሞ በርካታ እውነታዎችን ልንመዝ እንችላለን። እውነት እኮ ነው! እንዲህ አይነቱ ክፉ የሚባል ቀን ሲመጣ የሚሆነው አይታወቅም። ደግ የተባለው ክፉ፣ቀና የነበረው ጠማማ፣ነጩ ጥቁር፣ ሜዳውም በአንዴ ገደልና ሸለቆ ሊሆን ይችላል።
«ትንሽ ደግስና ወዳጅ ጠላትህን ለይ» እንዲሉ እንዲህ አይነቱ ቀን ሲያጋጥም ጥሬውን ከብስሉ ለመለየት ያመቻል። በዚህ ጊዜ ማን በጎ እንዳሰበ ፣ ማንስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሽንቁር እንዳሰፋ ለማወቅ ቀላል ነው።አያልፉት የለምና ይህ ቀን አልፎ በትውስታ ሲያወጉት ደግሞ የትዝብትና የምስጋናው ነገር መሳ ለመሳ ሆኖ በአንድ መወጋቱ አይቀሬ ነው።የዛኔ ታዲያ በክፉ ቀን ክፉ የሰራውን ሆኖ አለመገኘት ነው።
የከተማችን አንዳንድ ባለታክሲዎች ጉዳይም ልክ እንደዛው ማለት ነው።ዶፍም ይሁን ጠብታ ለአፍታ መጥቶ መመለሱ ላይቀር ፣ከበረዶም በኋላ ጸሀይ ደምቃ «አለሁ»ማለቷን ላትተው፣ በሰዎች ልቦና ክፉ ስማቸውን እንዳፃፉ ያልፋሉ፡፡ ሁሌም ትዝብትን አትርፈው ይጓዛሉ፡፡
ቀኑን ጸሀይ ውሎ ጥቂት ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ለእንዲህ አይነቶቹ ልማደኞች መልካም የሚባል አጋጣሚ ይሆናል። ሰበብ ፈላጊዎቹ ጠዋት እየለመኑ ሲያሳፍሩት የነበረውን ሰው እንደማያውቁት ሆነው በራቸውን ይዘጋሉ። የታክሲ ሾፌሮች ድርጊት ታክሲ ፈላጊው ሲንገላታና ሲሯሯጥ ማየትም በእጅጉ የሚያስደስታቸው ይመስላል። በዚህ ወቅት እነዚህ አሽከርካሪዎች ቢጠሯቸው አይሰሙም። የዝናቡ ጠብታ ለኪሳቸው ጥሩ ሲሳይ እንደሚያመጣ በማሰብ በነባሩ ታሪፍ ላይ በእጥፍ ጨምረው ይደራደራሉ። በዕለቱ ማንም ቢለምናቸው፣ ቢያለቅስና ቢያዝን ደንታቸው አይደለም። ባዶውን ታክሲ በኩራት እያሽከረከሩ ማለፍም የተለመደ ድርጊታቸው ሆኗል፡፡
አንዳንዶቹ በጉጉት አፍጥጦ በሚጠብቃቸው እግረኛ መሀል ሰንጥቀው ሲያልፉ የሚያሳዩት ያልተገባ ድርጊት ደግሞ ያስገርማል፣ያሳዝናል፤ያናድዳል። የመጡበትን ፍጥነት እንደማቀዝቀዝ አድርገው ቆም ለማለት ይሞክራሉ። ይህኔ ሊያሳፍሩን ይሆናል በሚል ጉጉት የሚሽቀዳደመው ተሳፋሪ የታክሲውን በር አንቆ አብሮ መሮጥ ይጀምራል። እንዲህ ሲሆን የእነሱ ትምክህት አብሮ ይጨምራል።በሩጫ እየተከተለ የከበባቸውን ሰው የኋሊት እያዩም «አንሄድም» ይላሉ።
አሁንም መሮጥና መጓጓት የማይደክመው የሩቅ ሰፈር ነዋሪ ከሩቅ ብቅ የሚለውን ታክሲ እየጠበቀ በሩን አንቆ ይሽቀዳደማል። አሁንም ግን ከተመሳሳይ ልፋትና ጉጉት በኋላ « አይሄድም» በሚል ምላሽ ይሸኛል። በዚህ ጊዜ የአንዳንድ ባለባጃጅ አሽከርካሪዎች ባህርይም በጣም የሚገርም ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲመላለሱበት የሚውሉበትን መንገድ በተለየ ሁኔታ ተመልክተው «ኮንትራት ካልሆነ አንሞክረውም» ይላሉ።
ወዳጆቼ! በጠራራ ጸሀይ ድንገት ጠብ የምትል ዝናብ ምንያህል ለውጥ ታመጣ መሰላችሁ? ግን እንደአበው ተረት ክፉ ቀን አያምጣ እንጂ ከዚህ የባሰ አጋጣሚ ቢፈጠር ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመቱ ቀላል ነው። ያም አለ ይህ ግን ዝናቡ ሲያልፍ ጸሀይ፣ ጨለማው ሲነጋም ብርሀን መተካቱ አይቀርምና ለሚያልፍ አጋጣሚ ክፋትን አንልመድ እላለሁ። ባህርያችን ከወቅት ጋር ሊቀያየር አይገባምና፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።