ሰኔ ግን 30 ቀን ብቻ ነው?

10 Jun 2018

እስኪ ስለሰኔ ሳይንሳዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተረታዊ ብያኔዎቹ እናውራ፡፡ እንዲያውም የሰኔን ተረታዊነት እናስቀድም፡፡ ከወራት ሁሉ ስማቸው ተደጋግሞ የሚጠሩ ወሮች መስከረምና ሰኔ ይመስሉኛል፡፡ በተረትና ምሳሌ እንዲያውም ሰኔ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ «ሰኔ መቃጠሪያ ህዳር መገናኛ»፣ «ሰኔ ነግ በኔ»፣ «ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ»፣ «ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል»፣ «በሰኔ ገመሻ በበጋ ጤፍ እርሻ…» የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገር ብቻ ሳይሆን ፈሊጣዊ አነጋገሮችም አሉት፡፡ ‹‹ሰኔና ሰኞ›› የሚለውን አታውቁትም? ይህንማ ማንም ያውቃል፡፡
ሰኔና ሰኞ ማለት እንደ ፈሊጣዊ አነጋገር ድንገተኛ አጋጣሚ ማለት ነው፡፡ ይሄውም ሰኔ አንድ ሰኞ ዕለት ሲውል ማለት ነው፡፡ አይ እኮ የልማድ ነገር፡፡ ሰኔ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ከዋለ አደጋ ይፈጠራል ተብሎ ይፈራል፡፡ ይሄ ለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ ከአፈ ታሪክ የዘለለ ተጨባጭ ነገር ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ምናልባት ግን እንዲህ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ዓመት ላይ ሰኔ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ይውላል፤ በአጋጣሚ በዚያን ዓመት የሆነ አስገራሚ ነገር ከተፈጠረ በዚያው ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሌላ አጋጣሚ ይጨመርብህ ካለው ደግሞ ከተወሰነ ዓመታት በኋላም ሰኔ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ውሎ ያጋጠመ ነገር ካለ በዚያው ይለመዳል፡፡
እስኪ አሁን ደግሞ ከተረታዊ የሰኔ ብያኔዎች ወደ ሳይንሳዊ እንሂድ (አንዳንዴ የሳይንስ ሊቅም ያደርገኛል)፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ የተማርኩት የሳይንስ ትምህርት የህልም ያህል ትንሽ ትንሽ ትዝ ይለኛል፡፡ እናም ከ6ኛ ክፍል ትምህርቴ አንፃር (ሻሼ ስታይል) ሰኔን ስተነትነው የክረምት ወር መጀመሪያ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ብዙ ተረትና ምሳሌዎች ከታታሪነት ጋር የተያያዙት፡፡ «ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል» የተባለው ገበሬ ጠንካራ መሆን ያለበት በሰኔ ስለሆነ ነው፡፡ «ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ» የተባለውም ሰኔ የክረምት ወር መጀመሪያ ስለሆነ በወቅቱ መሰራት አለበት ለማለት ነው፡፡ «ሰኔ መቃጠሪያ ህዳር መገናኛ» የተባለውስ ለምንድነው?
ይቺኛዋን ለማብራራት አሁን ካለንበት ዘመን ወደኋላ መለስ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ይህ የተባለው እንደ አሁኑ ድልድይና መኪና ባልነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ከሰኔ ጀምሮ ክረምቱን ሙሉ ወንዞች ስለሚሞሉ የወዲያ ማዶ ሰውና የወዲህ ማዶ ሰው የሚገናኘው የክረምት ወራት አልቆ ወንዞች ሲጎሉ ነው፡፡ ሰኔ ሲመጣ ወንዝ እንደሚሞላ ስለሚያውቁት ‹‹በሚቀጥለው ዓመት እንገናኝ›› ብለው ይቀጣጠራሉ ማለት ነው፡፡
ኢ-ሙያዊ ትንተናዬ ይቀጥላል፡፡ የሰኔ ወር ባህላዊ አንደምታም አለው፡፡ እንዴት? ማለት ጥሩ ነው፡፡ አሁን ቀጥ ብለን ወደ እኛ ቤት ፓርላማ እንገባለን! በነገራችን ላይ የእኛ ቤት በየዓመቱ ሰኔ ወር ላይ በጀት ያጸድቃል፡፡ እንዲያውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚያጸድቀው ይለያል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እኮ የሚያጸደቀው ብር ብቻ ነው፡፡ የእኛ ቤት ፓርላማ ግን የሚያጸደቀው ሽሮና በርበሬ ጭምር ነው፡፡ በየዓመቱ የሰኔ ወር ላይ እኮ ‹‹የእኛ ቤት ፓርላማ›› እያልኩ ነግሪያችሁ ነበር፤ ወይስ ትንሽ መገረብ ያስፈልጋችኋል? በነገራችን ላይ «መገረብ» ማለት አራድኛ ሲሆን መድገም ማለት ነው (እግረ መንገዳችንን አራድኛም እንማር ብየ ነው)፡፡
ወደ እኛ ቤት ፓርላማ እንመለስ፡፡ ፓርላማው የሚያቀርበው የሽሮና የበርበሬ በጀት በሙሉ ድምጽ ላይጸድቅ ይችላል፡፡ ድምጸ ታቅቦ የሚባል ነገር ግን የለም፤ ወይ መቃወም ነው ወይ መደገፍ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የፓርላማው አባላት(የቤተሰቡ አባላት በሚል መረዳት እኮ ነው) ወስነው ለክረምት የሚበቃ ሽሮና በርበሬ ይጸድቃል፡፡ የምር ግን እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር እናውራ፡፡
በገጠር አካባቢ የሰኔ ወር የተለየ ቦታ አለው፡፡ የክረምት ወር መጀመሪያ ስለሆነ ሁሉ ነገር መዘጋጀት አለበት፡፡ ምክንያቱም ዋናው ክረምት ከገባ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በሥራ የሚዋክቡበት ነው፡፡ ከዱር ያለው የግብርና ሥራ ላይ እንጂ ሽሮና በርበሬ ማዘጋጀት ላይ ሥራ መፍታት አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም ሽሮና በርበሬው ቀድሞ መዘጋጀት ይችላል፤ የእርሻ ሥራ ግን ወቅታዊ ነው፤ የዝናቡን መኖር ተከትሎ ብቻ የሚታረስ ነው፡፡ በተለይ የጤፍ እርሻ ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ወቅት ማንም ወለም ዘለም ማለት አይችልም፡፡
የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ መሆን አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን ፌዴራላዊ አንደምታም አለው፡፡ ለምሳሌ በሰኔ ወር ብዙ ነገሮች ይዘጋሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፣ አንዳንድ ተቋማት ይዘጋሉ(በተለይ በገጠር አካባቢ)፣ የመንግስት ዓመታዊ በጀት እንኳን የሚጸድቀው በሰኔ ወር ነው፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮው የ2011 በጀት ጸድቋል፡፡ የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ መሆኑ እንደ ልማድ ባይሆን ኖሮ የ2011 በጀት የሚጸድቅ መስከረም ወር ላይ ነበር፤ ምክንያቱም ሰኔ ማለት ገና 2010 ነው፡፡
የሰኔ ወር ብዙ ትዝታዎች አሉት፡፡ ለሰራተኛ ትዝታ አለው፣ ለተማሪ ትዝታ አለው፤ ለእረኛ ትዝታ አለው፡፡ ደግሞ የእረኛ ትዝታ ምንድነው የሚል ካለ የከተማ ልጅ ነውና ወደ እኔ ይምጣ፡፡
እረኛ ከሌሎች ወራት በተለየ ክረምት ጫና ይበዛበታል፡፡ ምክንያቱም በክረምት በየአካባቢው የሰብል ቡቃያ ነው፤ ያንን ደግሞ ከብቶች እንዳይበሉት መጠበቅ አለበት፡፡ በዚያ ላይ የክረምት ዝናብ በየሰዓቱ ድንገት እየመጣ ያወርደዋል፤ መጠለያ እንኳን አያገኙም ዝናቡ የሚያልቀው ከላያቸው ላይ ነው፡፡
ሌላውና ትልቁ ትዝታ ደግሞ የተማሪዎች ነው፡፡ ተማሪ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሰኔ ትዝታ አለበት፡፡ ከአንደኛ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት እያለ ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ስለሚላመድ የሰኔ ወር መለያየትን ይዞ ሲመጣ ቅር ይላል፡፡ በሌላ ምክንያት ደግሞ የሰኔ ወር የዓመቱ መውደቅና ማለፍ የሚታወቅበት ነው፡፡ በልጅነት አዕምሮ እኮ የሞት ፍርድ እንደመጠባበቅ በሉት፡፡ ለደረጃ የሚፎካከሩ ተማሪዎች ደግሞ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚባባሉበትና የሰኔ ወር ቁርጣቸውን የሚነግራቸው ነው፡፡
ስለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ትንሽ እንበል፡፡ ይሄ ነገር በተለይም ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችና ለተመራቂዎች የተለየ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ የሚለይበት ነው፡፡ እነዚህን ቤተሰቦቹን የሚያገኛቸው በሰኔ ወር ነው፡፡ እዚህ ጋ የቤተሰብ ናፍቆት አለ፤ እዚህ ጋ ደግሞ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍል ከተውጣጡ ጓደኞቹ ጋር ሌላ ሕይወት ጀምሮ ሌላ ትዝታ ፈጥሯል፤ ሰኔ ላይ እነዚህን ልጆች ይለያቸዋል፡፡ የሰኔ ወር ለዚህ ተማሪ የትዝታ ምስቅልቅሎሽ ያለው ነው፡፡
ወደባሰው ትዝታ እንምጣ(አይ ሰኔ ወር ስንቱን ነገር አስታወሰን እኮ)፡፡ የሰኔ ወር ለተመራቂ ተማሪዎች ከማንም በላይ ትዝታ አለው ብንል ትክክል ነን፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኘው የነበረውን ሙያ የሚያረጋግጠው በዚህ ወር ነው፡፡ እንደገና መወለድ ልንለው እንችላለን፡፡ ያ ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› የሚለው መዝሙር ሆድን የሚያላውሰው በዚህ ወር ነው፡፡ ይሄ ትዝታ ለተመረቅንበት ዓመት ብቻ ሳይሆን የሰኔ ወር በመጣ ቁጥር የቴሌቪዥን ዜና ላይ ስናየው በትዝታ ወደተመረቅንበት ዩኒቨርሲቲ የሚወስደን ነው፡፡
የሰኔ ትዝታ ለሰራተኛውስ? እዚች ላይማ አንድ ነገር ወረፍ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ‹‹የበጀት መዝጊያ›› የሚባል ነገር ታውቃላችሁ አይደል? እሷ ነገር ብዙ ጥሩ ያልሆነ አሰራር አላት አሉ፡፡ እንዲያው በአጭሩ ምን ለማለት ነው፤ የበጀት መዝጊያ ላይ ብር ላለመመለስ ተቋማት ያልሰሩትን ሥራ ሁሉ የሰሩ ለመምሰልና ለሪፖርት መሯሯጥ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ብሩ ላልታሰበለት ዓላማ ይውላል ማለት ነው፡፡ ኧረ እንዲያውም አሸሸ ገዳሜ ሁሉ ይኖራል፡፡ ቆይ ግን ይህን ሁሉ ሁነት የያዘው የሰኔ ወር እንደሌሎቹ 30 ቀን ብቻ ነው?
ሰራተኞች እንዴት ናችሁ?(ሰው እንዴት በመጨረሻ ሰላምታ ይጠይቃል?) ወድጄ አይደለም እኮ የዘንድሮ ክረምት የተገላበጠ መስሎኝ ነው፡፡ ቆይ ግን አዲስ አበባ ውስጥ ሐምሌና ግንቦት ቦታ ተቀያየሩ እንዴ? እኔማ ያ ሐምሌ ደርሶልኝ እስከማረጋግጥ ነው የቸኮልኩት! ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፤ ሐምሌም ግንቦትም ዝናብ ይሁኑ!
የዘንድሮ ግንቦት እኮ ወሩን ሙሉ ዝናብ በዝናብ አደረገን! ምን ዋጋ አለው በልግ የሚታረስበት ገጠር ውስጥ የለም አሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ግን አላስወጣ አላስገባ ብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ዝናብ የጠቀመው ነገር ቢኖር ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ማስተጓጎሉ ብቻ ነው፡፡ እኔማ እኮ ዝናብ በመጣ ቁጥር ድህነቴን ነው የሚያስታውሰኝ፡፡ አንድ ቢሉ ጫማየ ከሥር ውሃ እያስገባ ድህነቴን ያስታውሰኛል፡፡ ሌላኛው እንኳን ስቀብጥ ነው እንጂ በዚህ መበሳጨት አልነበረበኝም፡፡ ድንገተኛ ዝናብ በመጣ ቁጥር የምጠለለው ካፌ አካባቢ ነው፤ በር ላይ ሆኜ ወደ ውስጥ አያለሁ(መቼም ዓይኔ አያርፍ)፡፡ ከውስጥ ያሉ ሰዎች ኬክ፣ በርገር፣ ፒዛ እያማረጡ ሲበሉ እያየሁ ስለኑሮ ልዩነት ማሰብ እጀምራለሁ፤ በኋላ ራሴን በራሴ ለማጽናናት ‹‹ግደለም ደራሲ ለመሆን ይረዳኛል›› እላለሁ፡፡
በሉ ዝናቡ እንዳባራልኝ ልሄድ ነው፤ በሌላ ዝናብ እንገናኝ!

ዋለልኝ አየለ

 

የጠፋው ዕቃ የጠፋበት ቦታ

 

ከቤታቸው አይጠፉም የተባሉ ሰዎች ሁሉ ተጠሩ፤ ጠሪ ወይዘሮ የሻሽወርቅ ናቸው። ከተጠሩት መካከል እኔም ነበርኩበት። እንደው ጉዳዩን ታዘቢ ሲለኝ እንጂ ከአባቴ እኩዮች ኅብረት ጋር ለመቀላቀል እድሜዬ ደርሶ አይደለም። አብሬያቸው ስሆንና በጨዋታቸው መካከል የትውልድ ወቀሳ ከተነሳ የትውልድ ተወካይ ተወቃሽ እኔ ነኝ፤ ደግሞ በወጋቸው መካከል ለዚህ ትውልድ ሀዘኔታ ከተሰማቸው የሚያዝኑት ለእኔ ነው፤ ያልተወከልኩ ተወካይ።
የሻሽወርቅ ቤታቸው ለሻይ ቡና፣ ለጥየቃ፣ ለሰላምታ፣ ለብድር፣ ወሬ ለማቀበል፣ እግር ጥሎት፣ መርዶ ለማርዳት ወይም ደስታን ለማብሰር...ብቻ እግሩ ደጃቸውን የረገጠውን ሁሉ አስጠርተዋል። የተጠሩ ብዙዎች ቢሆኑም በስፍራው የተገኘነው ጥቂት ነበርን። ያለወትሮው ደግሞ ከተጠሩት መካከል እትዬ አደላሽ አልተገኙም፤ ለምን?
«ምነው በሰላም ነው?» አለች አንዷ ጎረቤታቸው፤ የእርሷ ቤታቸው መገኘት ወሬ በማቀበል ላይ የተመሰረተ ነው፤ «መቼም የአቶ አበራ ልጅ ዘንድሮ ሊመረቅ ሲጠበቅ ጉድ እንደረገን፤ እንደማይመረቅ ሰምተው አይደለም?» ብላ አስቀድማ ግምቷንና መረጃውን አቀበለች። «አይመረቅም እንዴ?» ሌላዋ ከቀደመችው አፍ ቀበል አድርጋ ጠየቀች።
«አዎን! እሱማ ሃሳቡ ጋውን ተከራይቶ እናትና አባቱን ሊያታልል ነበር። አይታወቅብኝም ብሎ ነውኮ! ምን ይሳነዋል የነዛ ምስኪን ወላጆቹ አምላክ አጋለጠዋ!» ወሬዋን ቀጠለች። የሻሽወርቅ እስከአሁን ዝም ማለታቸው አዲስ ነገር ሆነብኝ። ሰው ሲታማላቸው አይወዱም፤ ራሳቸው ስም ካላነሱ በቀር። ይህን አስቤ ብዙም ሳልቆይ የተጠራንበት ጉዳይ ይፋ ተደረገ። «አሁን እዚህ የጠራኋችሁ እንድትወያዩ አይደለም፤ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ ፈልጌ ነው» አሉ ፊታቸውን እንዳኮሳተሩ። «ባለፈው አሟቸዋል ያሉኝ ዘመድዎ ደኅና ናቸው? ችግር አለ እንዴ እማማ የሻሽ?» አለች ለቡና እና ሻይ ከቤታቸው የማትጠፋዋ ሌላዋ ሴት።
«ወዲያ! ምንድን ነው ክፋትን መጥራት፤ እኔ ችግር ገጠመኝ የሚል ቃል ከአፌ ወጥቷል? በቃ እንደው መርዶ ለመስማት ነው የምትጓጉት? ምን ያለ ጉድ ነው!» ቆጣም፣ ገልመጥም ብለው ተናጋሪዋን ተመለከቷት። መልስ አልሰጠችም፤ እርሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎቻችንም አስተያየት ከመስጠት ታቀብን። አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን አስተያየታችንንም አስተካከልን፤ መሬት መሬቱን ማየት ጀመርን። ምን ያህል እንደምናከብራቸው ተመልከቱልኝ!
«እንደው ከዚህ ቤት አትጠፉም፤ በዛ ላይ የሆድ የሆዴን ታውቃላችሁ። እንደውም ከእኔ የተሻለ ነገርንም ሆነ ቁምነገርን የሚያስታውስ ጭንቅላት አላችሁ ብዬ አስባለሁ። መቼ እለት እቁብ ወጥቶልኝ ነበር...» ንግግራቸውን ሳይጨርሱ በቤታቸው የነበርን ሁሉ የደስታ ድምጽ አሰማን። የደስታ ድምጽ ምን ዓይነት ነው? «እሰይ!»፣ «ውይ! እንኳን ደስ አሎት»፣ «ጎሽ!» ፣«ኧረ?» አልን፤ ማጨብጨብ ነው የቀረን። ለምን ደስ አለን የሚለው ጥያቄ ግን የታወቀ መልስ የለውም።
የኢትዮጵያዊነት ባህል ይሆን? ለቡና እና ለሻይ ብሎም ለቡና ቁርስ የሚበጀተው በጀት ከፍ ይላል ብለን ይሆን? ደግሰው ይጋብዙናል ብለን ይሆን? ራሳችንን በእርሳቸው ውስጥ አስቀምጠን አስበነው ይሆን? አልታወቀም።
«እስቲ ቀድማችሁ ስሙኝ፤ ታድያ የእቁቡን ብር ያስቀመጥኩበት ጠፋኝ፤ እና ቤቴ ስትመላለሱ አይታችሁ እንደሆነ ልጠይቃችሁ ነው» አሉ የሻሽወርቅ፤ ይሉኝታ አያውቃቸውም አያውቁትም። «አበስኩ ገበርኩ! የፈጣሪ ያለህ! ድንግል እናቴ ድረሽ! ቅዱስ ገብርኤል! የመልአኩ ያለህ! ብሩ ጠፋ?» ድንጋጤ በእነዚህ ተከሽኖ ቀረበ። የጎረቤቶቻቸው ድንጋጤ ግን እንደውም የሻሽወርቅን ጥርጣሬ አገዘፈው።
«ምን አስደነገጣችሁ! አይታችሁ እንደሆነ ጠየቅሁ እንጂ ሌባ አልኳችሁ? አላልኩም።» አሉ ሁላችንንም በተራ በተራ እያዩን። «ስንት ነው ገንዘቡ? ቆይ ቆይማ እንደውም አይንገሩን፤ የት ነበር ያስቀመጡት?» አለች ብዙ ጊዜ ለብድር ከቤታቸው የምትመጣዋ ሴት፤ መልስ አልሰጧትም።
«እስቲ ተማክራችሁም ቢሆን ንገሩኝ፤ ሰው እንዴት የገዛ ገንዘቡን ያስቀመጠበትን ያጣል?» ሁላችንንም እያዩ። ካለነው መካከል የተናቁ የመሰላቸው ፊታቸውን ጥለው የሚሆነውን ይጠባበቃሉ እንጂ አስተያየት አልሰጡም። የሻሽወርቅ ጭንቀት ይሁን ቁጣ አልያም ግራ መጋባት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆነ።
«እንደስልክ ብር ላይ አይደወል! ቆይማ አደላሽ የት ሄዱ? እርሳቸው ቢኖሩኮ መፍትሄ አይጠፋም» አለች የወሬ እናት፤ መረጃ አቀባይቷ ሴት። ይሄኔ የሻሽወርቅ ፊታቸው ነጭ ሆነ፤ የቀይ ዳማ መልካቸው በፍጥነት ሲቀየር የበለጠ ደግሞ እኛን አስደነገጡን። እውነትም እትዬ አደላሽ ቢኖሩ እንዴት ጥሩ ነበር፤ እትዬ አደላሽ ግን ለምን አልመጡም?
ይህን እያልን ሳለ እትዬ አደላሽ ብቅ አሉ፤ እድሜያቸው ረጅም ነው። የአደላሽ መምጣት እኛን ሲያስደስተንና ሲያስተነፍሰን እትዬ የሻሽን ግን አስጨነቃቸው፤ ፊታቸው ላይ ጭንቀታቸው በግልጽ ይታያል። የተጨነቁት ግን በገንዘባቸው መጥፋት እንጂ በአደላሽ መምጣት ላይሆን ይችላል፤ ነገሩ በኋላ እስኪገለጥ ድረስ።
«እንዴ! ቤተ-ሰፈሩ ተሰብስቦ የለም እንዴ? ደግሞስ የቆማችሁ ለምን ነው? የሻሽ...ተቀመጡ ማለት ቀረ?» እትዬ አደላሽ በፈገግታቸው ታጅበው ገቡ፤ እኛም ፈገግ ብለን የሰላምታ ቃል እያሰማን ተቀበልናቸው። «ምነው? ቡናም አልቀረበ...በሰላም ነው? አስጨነቃችሁኝኮ!» ነገሩን ለእትዬ አደላሽ ደፍሮ የሚያስረዳ ሰው ጠፋ።
ራሳቸው የሻሽወርቅ መናገር ጀመሩ «የደረሰኝን የእቁብ ብር ያስቀመጥኩበት ጠፋኝ ብዬ አገር ይያዝልኝ ልል ስል መጣሽ!» አሉ፤ «እና እነሱን ለምን አደከምሽ?» አሉ እትዬ አደላሽ በቀላሉ ቀበል አድርገው፤ እኛ የተጨነቅነውን ጭንቀት አያውቁ። «ብሩን ያስቀመጥኩበት ቦታ ጠፋኝ እንጂ ብሩ ጠፋኝኮ አላልኳቸውም፤ የት ላስቀምጥ እችላለሁ የሚለውን ስንመካከር ነበር።» አሉ፤ ይሉኝታ አይፈሩም አይደለ? ከይሉኝታ ይልቅ ጓደኛቸውን እትዬ አደላሽን ያከብራሉ። ይህ ሆነና እኛም በመገረም፤ አንዳንዱም «እኚህ ሴትዮ! እስከመቼ እንዲህ እንዘልቃለን!» ብሎ በለሆሳስ እያጉረመረመ ቤቱን ለቀን ወጣን።
ስወጣ ሞባይሌን ረስቼ ነበር፤ ምሥጢር ሰማሁ። «የሻሽወርቅ! ኧረ ተይ አስተውይ! አረጀሽ እንዴ? ቤቴ ብዙ ሰው ገባ ወጣ ስለሚል አንቺ ጋር ይሁንልኝ ብለሽኮ ለእኔ ብሩን ሰጥተሽኛል፤ ጎረቤቶችሽን በማያውቁት ነገር ማስጨነቅ ምን ማለት ነው?» አሉ እትዬ አደላሽ ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው፤ የምክር በሚመስል ድምጸት።
«አንቺ ደግሞ! ረሳሁታ...በዛ ላይ ገንዘብ ጠፋኝ ሳይሆን ያደረኩበት ጠፋኝ ነው ያልኳቸው። ከዛ ይኸው አንቺን አገኘሁ።» ብለው ሳቁ። በሩን መልሼ ሳንኳኳ ሁለቱም በፍጥነት ሳቃቸውን አቆሙ። «የዘንድሮ ልጆችኮ! ተደብቀሽ ስትሰሚ ነበር?» አሉኝ የሻሽ-ወርቅ፤ «ኧረ ምንም አልሰማሁም። ስልኬን ያስቀመጥኩበት ጠፍቶኝ ነበር፤ ትዝ ሲለኝ እዚህ ነበር ለካ!» ብዬ የረሳሁት ተንቀሳቃሽ ስልኬን ይዤ ሹልክ፤ የጠፋብንን ነገር ለማግኘት ያስቀመጥንበትን ቦታ መለየት ለካ ይቀድማል።

ሊድያ ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።