የክረምት ድምጾች

13 Jun 2018

የዘንድሮ ክረምት አመጣጥ ገና በጠዋቱ ሆነና ዝናቡ ያልታሰበ ሆኖ ሰነበተ። አያ ግንቦትም ጠንከር ላለው ዶፍና ጎርፍ እጁን ሰጥቶ በወጉ ከተሰናበተ ቀናት ተቆጠሩ። እንደቀድሞውማ ቢሆን ይህ ወቅት በፀሀዩ ሙቀት አግሎ መድረሻ ያሳጣን ነበር። ግን ደግሞ አንዳንዴ ወቅቶች እንዲህ ይቀያየሩና ያልታሰበው ይሆናል።
መቼም ቢሆን ክረምትና በጋ መፈራረቃቸው የሚያስገርም አይደለም። ከእነዚህ ወቅቶች ጋርም ብርድና ውሽንፍሩ ተደርቦ ቢመጣ አሁንም አያስገርምም። ጭቃና ድጡ፣ ዳመናውና የቀኑ ጨለማነትም ብርቅ አይደለም። ለእኔ ሁሌም ድንቅ የሚለኝ ነገር ቢኖር ክረምቱን ተከትለው የሚመጡ የአንዳንድ ድምጾች ጉዳይ ነው።
ወዳጆቼ! እነዚህ ድምጾች ምንአልባትም በየአመታቱ ከክረምቱ ጋር እኩል ሲራመዱ የኖሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ በመሆናቸውም ብዙዎች የእነሱን መኖር ከቁብ ሳይቆጥሩ ከጆሯቸው አላምደው የተዋቸውም ይሆናሉ። ለእኔ ግን ሁሌም የሚረብሹኝ እልፍ ሲልም የሚያበሳጩኝ ናቸው ብዬ ስናገር ደግሞ ያናድደኛል።
እንደው በሞቴ አትሳቁብኝና እናንተ የቢንቢዎች(ትንኝ) ድምጽ አናዷችሁ አያውቅም? ለእኔ ግን በእጅጉ ያበሽቀኛል። ቢንቢ ማለት እኮ ለአይን በወጉ የማትታይ፣ ልያዛት ቢሉም በቀላሉ የማትገኝ ሚጢጥዬ ነፍሳት ነች። ቢንቢ እንዲህ በቀላሉ ብትገለጽም ሰዎች ዘንድ ቀረብ ስትል የምትፈጥረው ድርጊት ከቃላትም በላይ ሊሆን ይችላል።
ክረምቱ አይሎ አካባቢው በሳርና በቅጠል ሲሸፈን ደግሞ እሷን ላለማየትና የክፉ ድርጊቷ ሰለባ ላለመሆንም መጠንቀቅ ነው። በትክክልም ይህ ጊዜ ለዚህች ፍጥረት ሰርግና መልሷ ይሆናል። በእነዚህ ቦታዎቿ ዘር ማንዘሯን አሰባሰባና በአቅም ተደራጅታ ምሽቱን «ቤቶች»እያለች ብቅ ያለች እንደሆን ውይይይ! ...እመት ቢንቢ ውይይይይ!..
የእሷ ክፋት እኮ የሰዎችን ደም መጦና ያገኙትን ሁሉ ቀማምሶ ማለፍ ብቻ አይሆንም። በእንቅልፍ የደከመና የተረታውን ሁሉ ከያለበት ለመቀስቀስ በአንድ ትንፋሽ ጥዝዝዝዝዝ..ካለች በቃ!ብሽቀትን ጭራ ብስጭትን ታራባለች።ይህኔ በስንት መከራ ዕንቅልፍ ያሸለበው ካለም ጥቂት ከራቀበት የህልም አለም ተመልሶ የእሷ ሰለባ ላለመሆኑ ፊትና መላ አካሉን ዳብሶ ያረጋግጣል። እኔ የምለው? ምንአለበት እንደው አንዳንዴ እንኳን ድምጿን አጥፍታ የምትፈልገውን አድርጋ ብትሄድ? ክፉ! እውነት በጣም ክፉ ሚጢጢ ነፍሳት ናት።
ወዳጆቼ! መቼም ሰሞኑን ከክረምቱ መግቢያ ጋር እየተጓዝን ነውና ብዙ ድምጾችን እየሰማን ስለመሆኑ አምናለሁ። አሁንም የሌሎችን ስሜት ባላውቅም ከዚህ ጊዜ ጋር ተያይዞ በጣም የሚያስገርመኝን አንድ ጉዳይ ላንሳ። እንቁራሪቶችንና ጆሮ የሚበሳ ድምጻቸውን። እንዲህ አይነቱ ደማቅ ድምጽ እንኳን ክረምቱ በወጉ ገብቶ ይቅርና ፣ጥቂት ዝናብም ቢርከፈከፍ ፈጥኖ መደመጥ የሚችል ድምጽ በመሆኑ ሁሌም ያስደንቀኛል።
እኔ ክረምትን ሳስብ እንቁራሪቶችና አካባቢውን የሚያውከው ድምጻቸው ጭምር ትውስ ይለኛል። በጣም የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህ ፍጥረቶች ደረቅ ሆኖ የከረመው ሜዳ በድንገቴው ውሃ መላበስ ሲጀምር በማህበር ተደራጅተው ለመገናኘት ያላቸው ፍጥነት ነው። እርስዎ ጠዋት ረግጠው ያለፉት የአፈር መንገድ ማታ ሲመለሱ ውሃ ተኝቶበት ሊደርሱ ይችላሉ።
ይህም ብቻ አይደለም ከየት መጡ የማይባሉ ምድረ እንቁራሪቶች ጉሮሯቸው እስኪላቀቅ በሚያወጡት የቅብብሎሽ ድምጽ የምሽቱን ሰላምዎን ጭምር ይነጥቆዎታል፡፡ እነዚህ አንቋራሪዎች በረጅሙ በሚለቁት የማያቋርጥ ድምጽ ምሽቱን አልፈው እስከ ንጋቱ ሊያደነቁርዎትም ይችላሉ። ለነገሩ ምን ማድረግ ይቻላል? አይደለም ለእነዚህ ሚጥጢዬዎች ለእኛ ለሰው ልጆችም እኮ የድምጽ ብክለት ምናንም እየተባለ የሚወጣው ህግ የሚገዛን አልሆነም።
እናንተዬ የሚያውክ ድምጽን ካነሳን አይቀር የክረምት ውሾችን ጉዳይም በቀላሉ አንዘንጋው።ልብ ብላችሁ ከሆነ በርከት የሚሉ ተልከስካሾች በየመንደሩ እየዞሩ በጨኸት ሰላማችንን የሚነሱን ወቅቱን ሰበብ አድርገው ነው። ከየት መጡ የማይባሉት እነዚህ መንጋ ውሾች ለጠብና ለተፈጥሯዊ ጉዳዮቻቸው ጭምር ቀጠሮ የሚይዙት እኮ በየአጥሮቻችን ስር ሆኗል።ይህን ማድረጋቸው ባልከፋ ፣ግን ምን በወጣን ነው? በእነሱ ድብድብና የከፋ ጨኸት ሳቢያ ሰላማችንን የምናጣው?
አንዳንዴ ደግሞ ከበድ ያለ ዝናብ ሊጥል ሲያምረው አስቀድሞ በጉርምርምታ ድንጋጤውን ይለቅብናል። ሲለው አጨልሞ ሲያሻው አደምኖ «መጣሁ» የሚለው የክረምት ዝናብ በቅድሚያ የሚሰጠው የቃል ማስጠንቀቂያ የዋዛ አይደለም። ከሰማይ ወገብ ወደ ምድር የሚለቀው ደማቅ ብልጭታ በአስደንጋጭ ድምጽና በአስፈሪ ሀይል ሲታጀብም የሚኖረው ማብረክረክ ፍጹም ማንነትን ያዝላል። ምንም እንኳን ጉዳዩ የተፈጥሮ ሆኖ የተለመደ ነው ቢባልም አንዳንዴ ይህን ያስረሳና ድንገተኛ የሚሳይል ጥቃት የደረሰ ያህል ድንጋጤን ያጭራል። እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚሆነው በዚሁ አይቀሬው የክረምት ወቅት ላይ ነው።
መቼም ክረምትና ጨለማ ተደጋግፈው ሲመጡ ለደህንነትም ማስፈራታቸው አይቀርም። እንዲህ በሆነ ጊዜ ቀኑ በዳመና ሊታጀብ ግድ ቢሆንም፤ ከምሽቱ ጋር ተደርቦ የሚጥለው ዝናብ ደግሞ ላልተገቡ ድርጊቶች ሁሉ ተባባሪ ሆኖ ሊዘልቅ ይችላል። በዚህ ወቅት አንዳንዶች ለክፉ ድርጊታቸው ይተጋሉ። ጨለማና ዝናብን ተገን አድርገውም ለዝርፊያና ለድብደባ ይዘጋጃሉ።
ብዙ ጊዜ መንገደኞች አምሽተው የሚንቀሳቀሱና ወደ መኖሪያቸው በብቸኝነት የሚዘልቁ ከሆነ፣ ክረምትና ጨለማ ከዘራፊዎች ጋር አብረው ሊያጠቋቸው ይችላሉ። በዝናብ በረከት የለመለሙ ቅጠላ ቅጠሎችም እነዚህን ክፉ አሳቢዎች ሸሽገው የድርጊታቸው አካል መሆናቸው አይቀሬ ይሆናል። ምንግዜም ወንጀል ሲፈጸምና በደል ሲያጋጥም ለመጮህ የሚበረቱ አንደበቶች ታዲያ የክረምቱን አየር ሰንጥቀው በኡኡታ አገር ምድሩን ቢያቀልጡት የሚያስገርም አይደለም። ለምን ከተባለ ደግሞ በክረምት እንዲህ አይነት ድምጾች ተለምደዋልና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።