የባቢሎን ግንብ አፍራሽ

10 Jul 2018

«ሁለት ጉዳዮችን አትርሳ፤ የማይደርስ ነገር የለም፤ የማያልፍም እንዲሁ» ይህ ጥቅስ በሌላ ሰው ቤት ተሰቅሎ ስለመኖሩ እንጃ፤ እርሱ ግን በየዕለቱ ማለዳ ከእንቅልፉ ሲነቃ እንዲያየው ከራስጌው ትይዩ ከፍ አድርጎ ሰቅሎታል። በትምህርት ቤት ቆይታውም በመተኛ ክፍሉ ለጥፎት ዓመታት አልፈዋል።
ጥቅሱን ከዓመታት በፊት ነው የጻፈው። ከየት እንደሰማው ግን አያውቅም። «የማይደርስ ነገር የለም፤ የማያልፍም እንዲሁ።» የማይደርስ ማለት? ጊዜ ይወስዳል እንጂ የፈለጉት ሁሉ ይደርሳል ማለት ነው? ወይስ እኛ እየደረስንበት ግን በትህትና ይደርሳል እያልን እየጠበቅን ነው? ምን እየጠበቅሁ ነው? እስኪያልፍ? በቃ! ጥቅሱ ዛሬ አልገባህ አለው፤ እስከዛሬ እንደሚያበረታው አልሆነም።
ከእንቅልፉ በደንብ ነቅቷል፤ መሃሉ ከረገበው የሽቦ አልጋው ላይ ሰውነቱን አንጠራርቶ ተነሳና ለጥቅሱ ጎኑን ሰጠው። ከፊት ለፊቱ ካለው ባለ ሶስት እግር ወንበር ላይ የተቀመጠውን ጥቁር ጋዋን ተመለከተ። የዓመታት ድካሙ፣ ጥረቱ፣ እንቅልፍ ማጣቱ ታወሰው። ሲማር የኖረው ለማወቅ ነበር ወይስ ላለመውደቅ?
ውጪዋ በቆርቆሮ፣ ውስጧ በማዳበሪያ የተጌጠው የክፍሉ አንድያ በር ተንኳኳች፤ «ተስፉ? ተስፉ...አልነቃህም እንዴ?» እትዬ አደላሽ ናቸው። በትምህርት ዓመታት ቆይታው ሰበብ እንዳያበዛ እንቅፋት የሆኑበት ስለሚመስለው ለእርሳቸው ያለውን ስሜት ለይቶ አያውቀውም። ከቤተሰቤ ርቄ እንዳይል እንደእናቱ፣ አልባሽ አጉራሽ የለኝም እንዳይል እንደዘመድ ሆነውታል። የሚሰንፍበትን እድል ሁሉ ነጥቀውታል። የአደራ ልጄ ሲሉት ይሰማል፤ ሸክም የሆነባቸው መስሎ እንዳይሰማው የማያደርጉት ነገር እንደሌለም ሁሌ ያስተውላል።
«ተነስቻለሁ ማዘር...ደኅና አደሩ?» አለ፤ ወፈር ባለና ባልጠራ ድምጽ፡፡ «ይመስገን...ሄደህ ከተመራቂ ጋር አበባ ባትቀበልም መጥተህ ቁርስ ብላ...» አሉት። መነሳት ባይፈልግም «መጣሁ ...» አለ።
ከአልጋው የመንፏቀቅ ያህል ቀስ ብሎ ተነስቶ ቆመ። ባለ ሶስት እግር ወንበሩ ላይ የተቀመጠውን ጥቁሩን ጋዋን አንስቶ ተመለከተው፤ በልጅነቱ ምርቃቱ እንዴት ቢሆን እንደሚመኝ አስቦ አያውቅም ነበር። የሚያስበው ቤተሰቦቹን ስለሚያገኝበት መንገድ ነበር። ሲያድግ እናቱ ጋር የሚወስድ መንገድ የሚሠራ ኢንጅነር የመሆን ህልም ግን ነበረው። ኢንጅነር ሆኗል፤ ወደእናቱ የሚወስደውን መንገድ እንዴት መሥራት እንደሚችል ግን ያስተማረው አልነበረም።
የማይደርስ ነገር የለም፤ ግን አደራረስም ዓይነት አለው። ዝም ብሎ «ደረሰ» ማለት ብቻ ምን ዋጋ አለው። ውድ ጊዜ የተከፈለበት፣ ብዙ ዋጋ የወጣበት ከሆነ፤ ከ«ደረሰ» በላይ ቋንቋ ያስፈልገዋል። ተመርቄአለሁ...ምርቃቴ ዛሬ ነው፤ ግን ምን ጨመረ? አንዲት ከእናቴ ጋር የምታገናኝ መንገድ መዘርጋት እንኳ የሚያስችል ምን አገኘሁ? ግን በቃ ያልፋል፤ እንደቀላል ነገር ያልፋል።
ጥቁሩን የመመረቂያ ጋዋን መልሶ ካነሳበት ወንበር ላይ ወርውሮ አስቀመጠውና ትንሿን በሩን በእርጋታ ከፈታት፤ ከውጪ ያለው ብርሃን እኩለ ቀን ይመስላል። የአንድ ክፍል ቤቱ ጨለማ ውጪ ስላለው ብርሃን እንዳያስብ ጋርዶት ነበር? በሚከፈት አንድ በር ብቻ፤ ሙሉ ቤት በብርሃን ይሞላል? የፀሐይዋ ብርሃን ዓይኑን ሙሉ በሙሉ ሊያስገልጠው ባይችልም ተስፋን ሰጠው፤ ከምንም የሚገኝ ደስታን አገኘ።
«አንተ ልጅ! ተመርቄአለሁና አልታዘዝም ብለህ ነው? ና ስልህ ቶሎ የማትመጣው?» አሉ እትዬ አደላሽ ከቤታቸው በረንዳ ላይ አሻግረው ድርቡን እያዩ። ፈገግ አለ፤ ፀሐይዋ የሰጠችው ብርታት ሳይሆን አይቀርም ፈገግታው ለእርሳቸውም ተጋባ «ኧረ ማዘር ምን አገኘሁ ብዬ? ተጣጥቤ መጣሁ» ከበሩ አፍ ላይ የተቀመጠውን አፍንጫው የተሰበረ የውሃ ጆግ አንስቶ ወደቧንቧው አመራ።
**** **** ***** **** ****
እትዬ አደላሽ ተስፉ የሚያደርገውን በጥሞና ይመለከቱ ጀመር። ከነፍሳቸው ይወዱታል፤ ባህር ማዶ ሄደው ከተለይዋቸው ልጆቻቸው አብልጠው ያዝኑለታል። እናቱ ወዳጃቸው ስለነበረች? የልጅነት ዘመን ተድላውን ስለሚያስታውሱ? የእናቱን አደራ ስለተቀበሉ? ሰው ስለሆኑ? ብቻ የውስጡን ጥያቄ እንደማይመልሱትና ውስጣዊ እረፍት እንደማይሰጡት ቢያውቁም አንዳች እንዲጎድልበት አድርገው አያውቁም።
«አቤት ማዘር...» የበረንዳውን ሁለት ደረጃዎች ወጥቶ በሃሳብ ከተዋጡት እትዬ አደላሽ አጠገብ ተገኘ። ደነገጡ፤ «ታያለህ የአሮጊት ነገር? በሃሳብ ሄጃለሁኮ! አሃ! የት አለ ያ ጥቁሩ ካባህ የኔ ልጅ? ኧረ ተው ሥራ በማግኛህ ጊዜ አታስቀይመኝ። በል ሂድና ቶሎ ለብሰህ ና» አሉት። ይታዘዛቸዋል፤ እንደሚወዱት ያውቃላ! ቢያናድዱትም ይወዳቸዋል፤ ያለ እርሳቸውስ ማን አለው?
በሯ ያልተዘጋው ክፍሉ ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ጋውኑን በፍጥነት አነሳውና ወጣ። ጋውኑን የመልበሱ ጥቅም አልታየውም፤ ግን ለእትዬ አደላሸ መታዘዙ ዋጋ እንዳለው ያምናል። ጋውኑን ታድያ እንደነገሩ ጣል አድርጎ እትዬ አደላሽ መኖሪያ ዋናው ቤት ዘው ብሎ ገባ። ባዶ ቤት አልጠበቀውም፤ «እንዴት ሆነልህ?...ጎሽ» እያሉ የሚያበረታቱት የአደላሽ ጎረቤቶች ቤቱን ሞልተውት ነበር።
እልል አሉ፣ አጨበጨቡ፣ ተቀባብለው ጉንጩን ሳሙት፣ እንባቸውን እየጠረጉ ፈጣሪን «ምን ይሳንሃል?» ብለው አመሰገኑ። ሁሉም ሲረጋጋ ነው ተስፉ ማሰብ የጀመረው። ደስ ብሎታል? ደንግጧል? ተነስቶ አመስግኖ መውጣት ፈልጓል? ተቀምጦ የጋገሩትን ዳቦ መቅመስ፣ ያቀረቡትን እህል መቃመስና ጨዋታቸውን መካፈል ፈልጓል? የተሰማውን ስሜት መለየት አልቻለም። «ከዚህ በላይ ምን ትጠይቃለህ?» አለችው ህሊናው፤ ይሄኑ በእርሱ ደስ ስላላቸው በዙሪያው ስላሉ ሰዎች ሲል ፈገግ አለ።
ተበላ...ተጠጣ...«መቼም ጠላታችሁ ወገቡ ስብር ይበልና ሰበር ወሬ በየሰዓቱ ነው የምንሰማ። እስቲ ማነሽ? ወሬውን ተይና ቲቪውን ብትከፍቺው» አሉ አንድ ተለቅ ያሉ የእትዬ አደላሽ የቅርብ ጓደኛና የዝግጅቱ እንግዳ። «አዎን! እውነት ነው። ይሄ ጎረምሳ ሄዶ ዝግጅቱን መሳተፍ ባይችልም ይመልከተው። እንደሚመረቅ ካወቀ በኋላኮ ያው መመረቂያ ካባውን ሊያመጣ አንዴ ነው የሄደ። እስቲ ጓደኞቹን ይመልከታቸው» አሉ እትዬ አደላሽ በዓይናቸው ተስፉን ገርመም እያደረጉ።
«አንቺን እንዳያስቸግር ብሎ እንጂ ቢሄድ የሚጠላ አይመስለኝም። አንቺ እንደሆነ ያው ተከትዬው ካልሄድኩ ነው የምትይ! አይደለም እንዴ ልጅ ተስፉ» አሉት አስቀድሞ የተናገሩት የእትዬ አደላሸ ጓደኛ። የተከፋበትን ስሜት ሁሉ የደበቀው ተስፉ ፈገግ አለ። «ማዘርዬማ ለእኔ ብለው ነውኮ! ያለእርሳቸው ማን አለኝ?» አለ።
ከየት እንደመጣ የማያውቀው እንባ ተናነቀው። ብሶቱ ሁሉ በዚህ ንግግሩ ቀዳዳ ሾልኮ ማምለጥ የፈለገ መሰለ። ሁሉም የጎረቤት እንግዳ ከንፈሩን መጠጠ። «ተው ይህን አንቱታና ማዘር ስልህ ይኸው ስንት ዘመን ሆነ? ተምረህ ጨርሰህ ተመረቅህ። እንዳይከፋህ ብዬ እንጂ በዚህች ማማሰያ አንጎራድድህ ነበር» አሉት ሳቅ ለመፍጠር ያህል፤ ይባስ እንባውን መቆጣጠር አቃተው፤ ተነስቶ ወጣ።
**** **** ** **** ****
«ተስፉ ...ና ቶሎ በል እባክህ» ከቤቱ በር አፍ ላይ ተክዞ የተቀመጠው ተስፉ የሰማው ድምጽ የሰላም ስላልመሰለው በፍጥነት ደረጃውን ወጥቶ አደላሽ አጠገብ ተገኘ። ማንም ምን ሳይነግረው በቴሌቭዥኑ ላይ ያረፈው ዓይኑ ግን የሆነውን ነገረው።
ሁለት ሰዎች ተያይዘው ይሳሳቃሉ፤ በሳቃቸው ውስጥ እንደህልም ትዝ የምትለውን እናቱን አየ፤ በሳቃቸው ውስጥ ማረፊያ ሲያገኝ ታወቀው፣ በሳቃቸው ውስጥ መመረቁ ትርጉም ሰጠው። እርሱ ያልሠራው መንገድ በሌላ ሰው ተሠርቶለት ሲያይ የእርሱ ታሪክ አልመስልህ አለው፤ ፊልም መሰለው።
በቤቱ ያለው ሰው ሁሉ ቲቪውን በጥሞና ይከታተላል። አደላሽ ግን ተሻግረው ሄዱ። እልል ከሚሉት የአስመራ እናቶች መካከል የተስፉን እናት የሚያገኙ መሰላቸው። ከዓመታት በፊት የኤርትራ ተወላጆች ከየቤቱ እንዲወጡና ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ሲታዘዝ፤ የተስፉ እናት ትገባበት ጨነቃት። እዛም ብትሄድ ለክፉ ቀን ብላ ያስቀመጠችው ነገር አልነበረም፤ ከዚህ ትታው የምትሄደው የበዛ ሀብት ኖሯት አይደለም። ልጇን ግን በእንግልት ውስጥ ማሳለፍን ፈራች፤ እንድትጨክን ተገደደች። ወደጎረቤቷ አደላሽ ተጠግታ ልጇን ሰጠች። «ልቤ ሁሌም ከዚህ ይሆናል» አለቻቸው።
ይህን ሲያስታውሱ እንባቸው በተሸበሸበ ቀይ ጉንጫቸው ላይ ከብለል ብሎ ወረደ። «ልጄ እንግዲህ መመረቅህ አሁን የበለጠ ዋጋ አለው። መንገዱን ታሰማምራለህ» አሉት በደስታ ሲቃ የያዘውን ተስፉን እያዩ። ተስፉ በክፍሉ ያለውን ጥቅስ እያሰበ ነበር፤ «የማይደርስ የለም ብለን አንጠብቅም፤ እንደርስበታለን እንጂ።» እርግጥም «በዚህ ጉዞ የማንደርስበት የለም፤ ይህም ሁሉ ቢሆን ደግሞ ያልፋል።»

ሊድያ ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።