የምትሠሩትን አታውቁምና...

12 Jul 2018

«እንደው ይህን የመሰለ ሰው...እስከዛሬ የት ነበር?» አሉ አንድ እናት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አብቅቶ የሬዲዮን ፕሮግራሙ ዝግጅት አስተባባሪ ድምጽ ሲከተል፤ ዞር ዞር ብለን በፈገግታ ተመለከትናቸው። «ይኸው ራዲዮና እና ያንን ቴሌቭዥን ተከታታይ አድርጎኝ አረፈው» ብለው እየሳቁ ነጠላቸውን አራግፈው ከተቀመጡበት ተነሱ።
«እድሜዬን በሙሉ ስፈልግሽ ኖሬ
ጊዜው ደረሰና አገኘሁሽ ዛሬ» አለ ያ ዘፋኝ! መኪና ላይ ተኝቶ፤ ልክ ሴትየዋ በአጠገቤ እልፍ ሲሉ ሙዚቃው ብልጭ አለብኝ። ምርጥና በጣም አስፈላጊ ብሎም ተፈላጊ ሰው የት እየሄደ ነው ሲጠሩት ሳይሰማ ግን በድንገት ከች የሚለው? ምርጥ ነገሮች ብዙ ጊዜ ትንቢትን ይፈልጋሉ መሰለኝ፤ «ይመጣልና ታገሱ!» ተብሎ ካልተነገረለትና በተስፋ ካልተጠበቀ ዝም ብሎ አይከሰትም።
በሬዲዮን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከሰማሁበት «ኑ ቡና ጠጡ» ሻይ እና ቡና ቤት ወጥቼ መንገድ ስጀምር ገራሚ የሆኑ ሰዎች እንዲህ በዘመናት መካከል እልፍ እልፍ እያሉ የሚታዩበት ምክንያት ምን እንደሆነ እያሰብኩ ነበር። አንድ ምርጥ ሰው ለመሥራት ስንት ዘመን ይፈጃል? ስንት ተላላዎችን አልፎ ነው አንድ ብልህ የሚወጣው? ከስንት ኪሎ ድንጋይ ውስጥ ነው አንድ ግራም ወርቅ የሚገኘው?
«በዛ በኩል ሂጂ...በዚህ ጋር አያስኬድሽም» የሚል ድምፅ ወደመጣሁበት መንገድ ፊቴን እንድመልስ አስገደደኝ። «ስለተቆፋፈረ...» አለኝ ተናጋሪው እንደማፈር እያደረገውና ጫማዬን እየተመለከተ፤ የተጋነነ ከፍታ ያለው ጫማ ያደረግኩ ስላልመሰለኝ በጥርጣሬ ጫማዬን ተመለከትኩ። ቢሆንም አጎንብሰው ደኅና የሚመስል የመንገድ ንጣፍ ድንጋይ ከሚፈነቅሉ ሰዎች መካከል የሆነው፤ የመንገድ ንጣፍ ሥራ ባለሙያ እንደሆነ ሁኔታው የነገረኝ ሰው ከእኔ የተሻለ መረጃ ስለሚኖረው ብዬ መንገዴን ቀየርኩ።
የተሻለ መንገድ መቼ ነው ተሠርቶ የሚያልቀው? አዲስ ሥራ እስኪፈጠር ድረስ ነው መሰል፤ ደንጊያ ሲያነጥፉ፤ መልሰው ሲነቅሉና ሲያፈርሱ...ደግሞ ሲሠሩ፤ መልሳችሁ አፍርሱ ሲባሉ፤ የሚሠራውን (ጠበቅ አድርጋችሁ አንብቧትማ!) የሚያውቁ ቢኖሩም፤ እነዚህ ባለሙያዎች ግን የሚሠሩት የተነገራቸው አይመስለኝም። የሠሩትን የሚያውቁት መንገዱ አልቆ ዳግም አይቆፈርም የሚባልበት ቀን ሲደርስ ነው።
ግን እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ሁላችን የምንሠራውን የምናውቅ አይመስለኝም። «የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው...» ይል የለ ቅዱሱ መጽሐፍ ታሪክን ጠቅሶ? ለምሳሌ ሰውን እንደምንሠራ እናውቃለን? በእግራችን ስር ውር ውር የሚሉ ህጻናትን እየገነባንና እየሠራናቸው ያለነው እኛ እንደሆንን እናውቃለን? ዛሬ ከላያችን ላይ ሆነው ዘረፉን ሰረቁን የምንላቸውንስ የሠራቸው ማን ነውና?
እውነት! የምንሠራውንኮ አናውቅም። በመሰዳደብ እና በመጠላላት ውስጥ ምን ዓይነት መልካም ፍሬ ይጸድቃል? እንደውም ስታስቡት የጠቅላይ ሚኒስትራችንን በቀናነት የታሸ ብልህ መሪነት አይተን የምንደነቀው በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ ሰው ይኖራል ብለን ስለማናስብ ነውኮ! እንደዛ ዓይነት ሰው አልሠራንማ።
ግን ደግሞ በሌላም አቅጣጫ ማየት ይቻላል። ከተናቀ አፈር ውስጥ ወርቅ እንደሚወጣው በብዙ ፈተና ያለፉ ናቸው የበለጠውን ስኬት የሚያመጡት ወይም በብዙ ጠላት መካከል ነው ብርቱ ወታደር የሚገኘው። በጣም ጥላቻና ትክክል ያልሆነ ነገር በበዛበት ጊዜ ያንን ለማተካከል ያሰበ ሰው ድንገት ብቅ ይላል። ህሊናውን የሚሰማ፣ እውነትን የሚያዳምጥ።
የት ነበርክ? የት ነበርሽ? ብላችሁ ብትጠይቁ እነዚህ ሰዎች ሲሠሩ ነበር። እዚህ አረፍተ ነገር ላይ እንደው ተቸገሩና «ሲሠሩ» የምትለዋን ቃል አጥብቃችሁ አንብቡልኝ። አዎን! እነዚህ ሰዎች ሲሠሩ ነበር። ሠሪው ቤተሰብ ነው፣ ሠሪው ማኅበረሰብ ነው፣ ሠሪው ሕዝብ ነው። ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሕዝብ ታዲያ የሚሠሩትን አያውቁም። ግን ውጤታቸው በፊታቸው ይታያል። ወይ ወደ አዘቅት ይጨምራቸዋል አልያም አሁን እየሆነ እንዳለው ጤና አዳም ይሆናቸዋል።
ከዚህ በኋላ የምንሠራውን ማወቃችንን እንጃ፤ ግን በጎ ያልነውን ሁሉ ልንሠራ መርጠናል ብዬ አምናለሁ። ፍቅርን ማጠናከር፣ አንድነትን ማበረታት፣ እንደው አደባባይ ላይ ብቻ ሳይሆን በጓዳና በቤትም ውስጥ መተጋገዝ፤ በድምሩ መደመር የመሳሰሉትን ይዘን እንቀጥላለን። ቂምና ጥላቻ መወራረስ እዚህ ላይ አበቃ ማለት ነው። በዚህ የበለጠ ቀና ትውልድ፣ በፍቅርና በይቅርታ የሚያምን፣ የሚለፈፍለት ሳይሆን ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊነትን የሚኖር ሰው ይመጣል።
በተጓዳኝ ዓይኑ የሚቀላም ይኖራል። «እሺ! ደግሞ ፍቅር ፍቅር ማለት ጀመራችሁ? ቆይ!» የሚል አይጠፋም። በቃ እንዲህ ነው! በጎ ያልነውን ብናደርግ እንኳ የምንሠራውን አናውቅም። ግን...እንደ ቱርክ ፊልም፤ ምን ችግርና ፈተናው ቢረዝም፣ አክተሮቹ ሁሉ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ፣ ከአሁን አሁን አለቀ ቢባል፤ በጥቅሉ የመጣው ቢመጣ የሄደው ቢሄድ፤ አሸናፊው አሁን የያዝነው መንገድ ነው።
ልክ መንገዴን እንዳስቀየረኝ የመንገድ ዝርጋታ ሠራተኛ «እየሄዳችሁ ያላችሁበት መንገድ ከማንነታችሁ ከፍታ ጋር ስለማይሄድ መንገድ መቀየር ያስፈልጋል» ያለ መሪ ከች ብሏላ! ለልማትም ብለው ይሁን ለጥፋት፤ መንገዳችንን የሚቆፋፍሩ ካሉ...ድልድይ እንዴት እንደሚዘረጋም አይተናል።
ውይ! ብቻዬን ስሆን እንደ ፈላስፋ የሚያደርገኝ ይመስለኛል መሰል። ግን «እንደ ፈላስፋ አደረገኝ» ማለት ራሱ መልሶ ያሳፍረኛል። ለብቻ ሲሆኑ ግን ከቀኝ ጎን መማከር ነው ጥሩ፤ ይሄኔ ክፋትም ቢሆንኮ ስንቱን ክፉ ክፉ ነገር የማሰብ እድል አለኝ ማለት ነው? በቀኝ አውለኝ...ቀኙን አሳስበኝ ማለት ነው!
መንገድ ቀይሬ መንገዴን ከቀጠልኩ ቆየሁ። በምንም በኩል ሂድ፤ ትክክለኛው መንገድ ይሁን እንጂ መድረሻህ ጋር በትክክል ከደረስክ አልተሳሳትክም፤ የሚል አባባል ሰምቻለሁ ልበል? እያስፈራራ ያለውን ዝናብ ዘመን አመጣሿ ትንሿ ስስታም ጥላዬ እንደማታስጥለኝ ሳስታውስ ፈጠን እያልኩ መራመድ ጀመርኩ። ነገሩ ብዙም ሳልርቅ ነው የዘነበው፤ ከአንዱ ልብስ ቤት ዘልዬ ገባሁ። የምንሠራውን አናውቅምና በቦርሳ ለመያዝ ትመቻለች ብለን የያዝናት ትንሽዬ ጥላ ለራሳችንም እያነሰችን ነው መሰል። ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።