‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው! ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከንጉሥም በላይ ነው!›› ከልባችን ነው ?

24 Jul 2015

 

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመዝናኛ ዓምድ አዘጋጅ ሰኔ 13 ቀን 2007 .ም ‹‹ደንበኛ ንጉሥ አይደለም›› በሚል ርዕስ ለጻፉት ጽሑፍ አያሌው ንጉሤ የተባሉ ፀሐፊ ሰኔ 27 ቀን 2007 .ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዚያው በመዝናኛ ዓምድ ‹‹ ደንበኛ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከንጉሥም በላይ ነው ! ›› በሚል ርዕስ የመልስ ምት የሚመስል እና ‹‹ ለደንበኛ ንጉሥነት ›› የወገነ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ እኔ የሁለቱንም ፀሐፊዎች ሃሳብ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በአክብሮት እየተቀበልኩ ነገር ግን ከሁለቱም ሃሳብ ውስጥ የማልስማማባቸውን ሃሳቦች እያነሳሁ ፍልሚያው ውስጥ እገባለሁ - ራሴን ችዬ ፡፡

በመነሻ ሃሳቤ በእኔ ውስጥ የሚመላለሰውን ‹‹ የደንበኛ ንጉሥነትን ›› ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ ልበል በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ በሚኖረውና በሚፈጠረው ግንኙነት የማገልገልና የመገልገል፤ አገልግሎት የመስጠትና አገልግሎት የመቀበል ቅብብሎሽ አለ፡፡ በዚህ ቅብብሎሽ ውስጥ በሁለቱም አቅጣጫ ‹‹ተጠቃሚነት ›› የሚባል ጉዳይ ይነሳል። ‹‹ተጠቃሚነትን›› ላብራራው አንድ ዓይነት አገልግሎትን የሚያበረክት አካል አገልግሎት በመስጠቱ የሚያገኘው አንዳች ትርፍ ወይም ጥቅም አለ፤ አገልግሎት ተቀባዩ እንዲሁ ሲገለገል ወይም አገልግሎት ሲያገኝ ተጠቃሚና አትራፊ ነው፡፡ ሁለቱም አካሎች ተጠቃሚዎች እስከሆኑ ድረስ በእንደዚህ ዓይነት ዓውድ ውስጥ አንዱ ምንዝር አንዱ አለቃ ፤ አንዱ አንጋሽ ሌላው ነጋሽ፤ የሚሆኑበት የዘውዳዊ ሥርዓት ተምሳሌት አባባልና ይዘተ ነገር መነሳት ያለበት አይመስለኝም ብዬ አሰብኩ፡፡ እና ለእኔ ካስፈለገ ሁለቱም ንጉሦች ናቸው፤ ሁለቱም አሸናፊዎች ፤ ሁለቱም ተጠቃሚዎች ናቸው ነው የምለው -ደንበኛም የደንበኛውም አስተናጋጅ፡፡

‹‹እህል ያለው ፈርዛዛ ፤ወርቅ ያለው ቀበዝባዛ›› ወይም ‹‹ወርቅ ያለው ፈርዛዛ፤ እህል ያለው ቀበዝባዛ›› ብለን ልንል፤ ይህንን አባባል በዚህ ሁኔታ ላይ ልንጠቅስ የምንችልበት ሁኔታ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ሻጭም ገዢም እኩል ናቸው የሚል ነው የኔ መረዳት፡፡ በሌላ በኩል በአክብሮት ማስተናገድ ከተነሳ እኔ የዚህ ሃሳብ ተጋሪ ነኝ፡፡ ደጋፊም፡፡

አገልጋይም ሆነ ተገልጋይ አንዱ ለሌላው የሚሰጠው አክብሮትና የሚያሳየው መልካም ፊት ለሚኖራቸው ግንኙነትና የሁለትዮሽ ቅብብል ምቹ መደላደል ይፈጥራልና!! ሌላውን ማክበር ራስን ማክበር ነውና ! አሁን እንደገና ወደዚያው ወደ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› አንኳር ሃሳብ ልመለስና ነገሬን ልቀጥል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ‹‹የተራበ ዳቦ ፈላጊና ገዢ›› ‹‹ዳቦ ለሚሸጥ ሰው›› ፤ እንደምን ነው ንጉሡ የሚሆነው? ብዬ እጠይቅና መልሱ «አልመጣልህ» ሲለኝ ጥያቄዬን ጥያቄ አድርጌ እተወዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ንጉሥ እንኳን ቢሆን ንጉሥ መሆን ያለበት ባለዳቦው ነው ብዬ ስለማስብ፡፡ ‹‹ ለእኔ የንጉሥነት ነገር ብዙም ወደ ውስጤ አይገባም፤ ይልቅስ ዳቦ ሻጩም ዳቦ ገዢውም በእኩል ደረጃ የሚፈላለጉ ሁለት ክስተቶች ናቸው ›› አለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳብ ያካፈልኩት ወዳጄ፡፡ የዚህን ጊዜ ጌታቸው ሠናይ ‹‹ ደንበኛ ንጉሥ አይደለም ›› ብለው ባቀረቡት ጽሑፋቸው ‹‹ ሁሉም ለጥቅሙ ነው የሚፈላለገው›› ያሉት ሃሳብም ትዝ አለኝ፡፡ በዳቦ ፈላጊውና በሻጩ መሀል የጋራ የሆነ ጥቅም አለና !! ዳቦ ሻጩ ዳቦ ሸጦ፤ ጨው ይገዛል፤ ‹‹ሰው በእህል ብቻ አይኖርም›› የሚለውን ሃሳብ እያከበርኩ፤ዳቦ ገዢውም ዳቦ ገዝቶ፤ ርሀቡን አስታግሶ በሕይወት ይኖራል እላለሁ፡፡

ሌላው ነገር ደግሞ ከዚሁ ደንበኛ ንጉሥ ነው ከሚለው ሃሳብ ጋር አብሮ የሚነሳው ጉዳይ ደንበኛ ንጉሥ ከሆነ በሁሉም ሥፍራ፤ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሁሉ ‹‹ንጉሥነቱ›› መታየትና መገለጥ፤ ለ‹‹ንጉሥነት›› የሚገባውን አክብሮትና ደረጃ ማግኘት አለበት፤ ይሁንና ይህ ሂደት የማይታይበት ድርጊትና ሁኔታ ብዙ ነው፡፡

ለምሳሌ ተኮልኩለው የታክሲ አገልግሎት የሚጠብቁ ተገልጋዮች በአንዳንድ ባለታክሲዎች የሚደርስባቸው እንግልትና ‹‹ትፈልጋለህ እዚህ ጋ ቁጭ በል ፤ አትፈልግም ውረድ፤ አልጭንም ትጭነኛለህ ንትርክ፤ ጠጋ በል ፤አትጨቃጨቅ፤ የገዛኸው መኪና አይደለም አትንቀባረር ፤በዚህ አቅጣጫ አልሄድም፤ በእዚያኛው ነው ማለት ወዘተ›› አፍ እላፊ ንግግሮች ‹‹የደንበኛን ንጉሥነት›› ጥያቄ ውስጥ አይከቱብንም ? በዚህ ዓይነት ነው ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው እንዲያውም ንጉሥ ብቻ አይደለም ከንጉሥም በላይ ነው ›› የምንለው ?

‹‹ስኳር ፤ ዘይት ፤ቅቤ፤ ምስር ፤ ጤፍ ወዘተ ለሚሸጡልን ነጋዴዎች፤ ለእንትናና ለእንትና መሥሪያ ቤቶች ፤ እኛ ደንበኞች ንጉሦች ነን ? ›› ብለውኛል- ደንበኛ ንጉሥ ነው ያልኳቸውና ሃሳቡን መቀበል ያቃታቸው ሰዎች፡፡ ‹‹ ጽድቁ ቀርቶብኝ፤ በወጉ በኮነነኝ ›› የሚለውንም አባባል አክለውልኛል፡፡ ወግ ያለው ኩነኔ ምን እንደሆነ ባይገባኝም፡፡ ኩነኔ ኩነኔ ነዋ!

ታዲያ ‹‹ ደንበኛ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከንጉሥም በላይ ነው! ›› የሚለው የፀሐፊው አያሌው ንጉሤ ሃሳብ በምሳሌነት የቀረቡትን ሃሳቦች ምን ያህል ፉርሽ ሊያደርግ እንደሚችል ብረዳ እኔም የአቶ አያሌውን ሃሳብ ይዤ አቀነቅን ነበር፤ ሰው መቼም አንድ ነገር በደንብ ሲረዳና ሲገባው አይደል ደቀመዝሙር ወይም ተከታይ የሚሆነው ?

‹‹ ደንበኛ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከንጉሥም በላይ ነው!›› ሲሉ ፀሐፊው አያሌው ንጉሤ በቃለ አጋኖ ምልክት አጅበው ያቀረቡት ርዕሱ ራሱ ባስበው፤ ባስበው ትርጉሙ አልመጣልህ ብሎኝ እርሳቸው የሚያብራሩና የሚተረጉሙልኝ ቢሆን ብዬ ያልገባኝን ይህን ርዕስ በጥያቄ መልክ ለማንሳት ወደድሁ እና ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከንጉሥም በላይ ነው!›› ብሎ ማለት ምን ማለት ነው ? ‹‹ ከንጉሥ›› በላይ ያለው ማን ነው ? ከ ‹‹ ንጉሥ ›› በላይ የሆነ ማዕረግስ ምንድን ነው ? ‹‹ከንጉሥም በላይ ነው›› ሲባል ‹‹ ፈጣሪ ነው ? ›› ለማለት ነው ? ይሄ ደግሞ የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ትርጉሙን ማወቅ ከብዶኛል፡፡

ደንበኛን ይህን ያህል ከምረነው፤ ማለት ከንጉሥም በላይ ያለውን ነገር ( ይህ ከንጉሥ በላይ የሆነው ነገር እስከአሁን ባለውቀውም) አድርገነው ከንጉሥ በላይም ስም ሰጥተነው እዚያ ላይ ስንሰቅለው ‹‹በነገሠበት›› አገልግሎት ሰጪ ላይ ትልቅ ጫና አይፈጠር ይሆን ? አንዱን ወገን ክበን፤ ክበን ሌላውን ወደታች ከዳጨነው ዴሞክራሲያዊ የእኩልነት መርህን የሚፃረር ሃሳብ ገኖ አይወጣብንም ትላላችሁ?

ሌላው በዚሁ በአቶ አያሌው ጽሑፍ ውስጥ የተነሳው ሃሳብ ‹‹የታማኝ ደንበኛ ›› ጉዳይ ነው ‹‹ታማኝ ደምበኞች ለሥራው አስፈላጊ ናቸው! ይህ ማለት ታማኝ ደምበኞች በሽያጭና በአገልግሎት ዘርፍ ብዙም ጉዳት አያስከትሉም። ስለዚህ ገንዘብን ያድናሉ ›› የሚል ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ ከዚሁ ጋርም ‹‹ሁሉም ደምበኞች እኩል ዋጋ የላቸውም ! ይህ ማለት ደምበኞች ለአገልግሎት ሰጪያቸው ድርጅት በሚያስገኙት የላቀ ጠቀሜታ ተለይተው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል›› ብለዋል፡፡ በጠቀስኳቸው በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ውስጥ ያሰመርኩባቸውን ሁለት ሃሳቦችን ከ ‹‹ ደንበኛ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከንጉሥም በላይ ነው›› ዋና ርዕሰ ሃሳብ ጋር እያስተያየን እንፈትሻቸው፤ በመጀመሪያ ‹‹ንጉሥ›› እና ከ ‹‹ንጉሥም›› በላይ ነው የተባለ ደምበኛ እንደምን ነው ‹‹ ታማኝ የሆነ ››፤ ‹‹ታማኝ ያልሆነ›› ብሎ ማለት ? ደምበኛ በደምበኝነቱ በእኩል ሚዛንና እይታ ነው መስተናገድ ያለበት ብዬ አስባለሁ። «የሚታመን፣ የማይታመን» ብለን የምንከፋፍልና የምንለያይ ከሆነ ደግሞ በጅምላ ደምበኛ ‹‹ንጉሥ›› ነው ለማለት የምንችል አይመስለኝም ፡፡

ከዚሁ ጋር ደግሞ ለእኔ እንደሚገባኝ የአምስት ብር ዕቃም ይግዛ፣ የ100 ብር፣ ደምበኛ ለዕቃው ሻጭ እኩል ዋጋ ያለው ሰው ነው፡፡ ሻጩ ሱቁን ከፍቶ ቀኑን ሙሉ ደምበኞችን ለማስተናገድ ሲጠብቅ የአምስት ብር ብቻ ሽያጭ ካከናወነ በኋላ ጀንበር ጠልቃ ሱቁን ዘግቶ ወደ ቤቱ ሊመለስ ይችላል፡፡ እና ታዲያ እንደምን ነው ‹‹ሁሉም ደምበኞች እኩል ዋጋ የላቸውም›› ማለት የሚቻለው ? ለእኔ ደምበኛ ሁሉ እኩል ዋጋ አለው የሚለው ሃሳብ ነው የሚጥመኝ፡፡

ብዙ ልጆች ያሏቸው እናቶች ልጆቻቸውን እኩል እንደሚያዩ እና ልዩነት እንደማያደርጉ ሲናገሩ ‹‹የልጅ አመሳሶ የለውም ›› ይላሉ፤ ሁሉም እኩል ነው ለማለት፡፡ ‹‹አጭሩም ረጅሙም›› ‹‹ቆንጆዋም ፉንጋዋም›› ለእናት ሁሉም ልጆቿ እኩል ናቸው፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ማንነትና ተፈላጊነት አላቸው፡፡ ስለዚህ ‹‹ከፍተኛ ዋጋ ያለው ደምበኛ›› ‹‹ አነስተኛ ዋጋ ያለው ደምበኛ ›› ብሎ የደምበኛ ታላቅና ታናሽ መደብ መፍጠር ለእኔ ግራ አጋብቶኛል፡፡ ደግሞስ እንዲህ ያለ መደብ መፍጠርስ ይቻላል ወይ? እንግዲህ ነገ ይህንን የደምበኛን ደረጃ የሚያሳየውን ጽሑፍ ያነበቡ የልዩ ልዩ ነገር ደምበኞቻችን፤ ደረጃ እያወጡ ‹‹በደረጃችሁ መሠረት እናስተናግዳችኋለን›› እንዳይሉን እፈራለሁ፡፡

‹‹ምርጥ ደምበኛ›› የሚልም ሃሳብ በዚሁ በአቶ አያሌው ጽሑፍ ውስጥ ተነስቷል፡፡ ደምበኛን የማበላለጫ ቃል፤ እና ‹‹ ምርጥ ›› የሚለው ቅጽል ‹‹ምርጥ›› ያልሆነ ደምበኛ እንዳለ ይጠቁማል፡፡ ምርጥ ሲባልስ ከምን አንፃር ነው? ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ በቢዝነሱ ዓለም ይህንን ‹‹ምርጥ›› የሚለውን ቃል መጠቀም በደምበኞች መሀል ልዩነትን አይፈጥርም ይሆን?

አሁን ሃሳቤን ወደ መደምደሚያው ላቻኩለውና እንዲህ ልበል፤ አቶ አያሌው ንጉሤ ‹‹ ደንበኛ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ከደንበኛም በላይ ነው ! ›› የሚለውን ሃሳብ ሲያቀርቡ ‹‹ የካሳይ ሞሪኖ ››ን ጽሑፍ ተመርኩዤ ነው ያቀረብኩት ፤ ሃሳቡ የእርሱ ነው ›› ብለው ምላሽ ይነፍጉኛል ብዬ አላስብም፤ ስለሆነም ላነሳኋቸው ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ይሰጡኛል ብዬ እገምታለሁ፤ ምክንያቱም ያላወቅሁትን ነገር ለማወቅ ጉጉት አለኝና!!

በተረፈ ‹‹አንድ ደንበኛ ወይም አገልግሎት ፈላጊ እና አገልግሎት ሰጪው ወይም አቅራቢው ፤ እኩል ማንነት ያላቸው በመከባበር ግንኙነት ሊያደርጉ የሚችሉ ማንነቶች (entities) ናቸው›› የሚል ነው የኔ የመጀመሪያም የመጨረሻም ሃሳብ፡፡ ስለዚህ ሃሳቦቻችን ወይ ይስማማሉ ወይ አይስማሙም፤ ዋናው ነገር አንድ ሃሳብ ተነሰቶ እርሱን በማንሸራሸር ዕውቀት መጨበጡ ነው፡፡ ስለዚህ አቶ ጌታቸው ሠናይም ሆኑ አቶ አያሌው ንጉሤ ስላቀረቡት ሃሳብ ሊመሰገኑ ይገባል፤ እያልኩ በሌላ ነገረ- ጉዳይ ብቅ እስከምል ብዙ ሰላም ለአንባቢዎቼ ተመኘሁ ! ሰላም!!

 

ፀሐፊው ሳምናስ (አምደኛ)

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0004233109
TodayToday4066
YesterdayYesterday10887
This_WeekThis_Week16654
This_MonthThis_Month100001
All_DaysAll_Days4233109

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።