በባለውለታዎቿ የከበረች፤ እነሱንም መልሳ ያከበረች አገር

07 Nov 2015

 

የአዘርባጃን ብሔራዊ አባት ተደርገው የሚቆጠሩ                                     በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የሠፈረው

ት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አይደር አልዬ፤                                               የአዘርባጃን ትልቁ ሰንደቅ አላማ፤

 

የጉዞ ማስታወሻ

ክፍል ሶስት

ጭልጥ ካለው እንቅልፌ ያነቃኝ የመኝታ በሬ ተከፍቶ የሰዎች መግባት ነበር። በድንጋጤ ውስጥ እንዳለሁም እንኳን ደህና መጣህ... ማን ልበል? ስል እንግዳውን ጠየኩት። አልቤርቶ እንደሚባልና የመኝታ ክፍል ተጋሪዬና ጣሊያናዊ መሆኑንም ጨምሮ ነገረኝ። እኔም በተራዬ እራሴን አስተዋውቄ ወደ ተቋረጠው እንቅልፌ ተመለስኩ።

የባኩ የሁለተኛ ቀን ጀንበር በመስኮቴ መፈንጠቋን እንደተመለከትኩ ከአልጋዬ ወርጄ ለእለቱና ለባኩ በሚመጥን አለባበስ ወደ ተቀሩት መሰሎቼ ከአልቤርቶ ጋር በመሆን አቀናሁ፡፡ ቁርሳችንን ከበላን በኋላም ትህትናና ፈገግታ በማይለያቸው አናር እና ኦርሀን በተባሉ ሁለት የአዘርባጃን ወጣቶች መሪነት ወደ ተዘጋጀልን መኪና አቀናን፡፡

ማታ የተዋወኳቸውን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ጋዜጠኞችም መጨመራቸውን ልብ አልኩ፡፡ ለመቁጠርም ሞከርኩ፡፡ አስራአንድ ነን፡፡ ብቸኛው ጥቁር ሰው ደግሞ እኔ፡፡ ዘግየት ብዬ እንደተረዳሁትም ከአፍሪካ የተጋበዝኩት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ስለሆነም ልዩ የመሆን ስሜት ፈጠረብኝ፡፡

የባኩ ጎዳናዎች ፍጹም ውብና ማራኪ ብዙም እግረኛ የሌለባቸው ናቸው፡፡ የአራት ኪሎን የሰው ማዕበል፣ የመርካቶን ትርምስ፣ የፒያሳንም ግፊያ ለለመደ ሰው የባኩን ጎዳና ቢመለከት ወይንም እግር ጥሎት እግረኛ ቢሆን ከተማው ለእግረኛ በተከለከለ ስፍራ እርሱ ክልከላውን ጥሶ እየተጓዘ ሊመስለው ይችላል፡፡ በዞርንባቸው ቦታዎች ሁሉ መኪና እንጂ ብዙም እግረኛ ያለመመልከቴ ነገር ብርቅ ቢሆንብኝ ጊዜ አናርን ብዙ ሰው እንደማላይና ምናልባት የስራ ሰዓት ስለሆነ ይሆን ስልም ግምቴን ጨምሬ ጠየኩት፡፡ አናር ግን ይሄ የተለመደ እንደሆነና እግረኛ የሚበዛባቸው ሌሎች አካባቢዎችም እንዳሉ በተለይ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ በርከት ያለ እግረኛ እንደሚኖር አጫወተኝ፡፡ እኔ ግን በቆይታዬ የአራት ኪሎን ያህል ሰው የበዛበት፣ የፒያሳንም ያህል በትከሻ ግፊያ ሰው የሚተላለፍበት አንዳችም ስፍራ አልተመለከትኩም፡፡

የባኩን ጎዳናዎች ዳርና ዳር የሞሏቸውን ውብና ማራኪ ህንጻዎች እየተመለከትን ተጉዘን ስናበቃ መኪናችን ከአንድ ስፍራ ደርሶ ቆመ፡፡ ትልቅ ጊቢ ነው፣ ውስጡም በተለያዩ ዛፎችና አበባዎች የተዋበ መሆኑን ልብ አልኩ፡፡ ቤተ መንግስትም መሰለኝ፡፡ መሰለኝም ብቻ ሳይሆን እርግጠኛም ሆንኩ፡፡ ምክንያቱም ከግቢው ውብነትና ድባብ ከባድነት ባሻገር በራፍ ላይ ያሉ የደህንነት ሰዎች አለባበስና ግርማ ሞገስ ከዚህ ውጪ ለማሰብ እድል አልሰጠኝም፡፡

በራፉ ላይ የጠበቁን ወጣትና ፍልቅልቅ አዘሪዎች ቀያይ አበባዎችን ለእያንዳንዳችን በማበርከት «እንኳን ደህና መጣችሁ» ሲሉ ተቀበሉን፡፡ ከመካከላቸውም እኛን ወደ አዘርባጃን የጋበዘንና «አይለሪ» የተባለው የወጣቶች ማህበር ሊቀመንበሩን አንደበተ ርቱዕ ወጣት ሚርሀሰን ሴይዶቭን ተዋወቅን፡፡ በመቀጠልም ወደ ጊቢው እንድንገባ ተፈቅዶልን ገባን፡፡ ቤተ መንግስት ውስጥ ሳንፈተሽ መግባታችን አስገረመኝ፡፡

የገባንበት ጊቢ ቤተ መንግስት አለመሆኑን ያወኩትና በራሴ ፈገግ ያልኩትም ጊቢው የመቃብር ስፍራ መሆኑን ስመለከት ነበር፡፡ በእውነት የሚገርም ስፍራ ነው፡፡ ይህ የመቃብር ስፍራ «Alley of Honour» ይባላል፡፡ የአዘርባጃን ታላላቅና ባለውለታ የሆኑ ሰዎች የተቀበሩበት የክብር ስፍራ ነው፡፡

በዚህ የመቃብር ስፍራ የአዘርባጃን ብሄራዊ አባት የሆኑት የቀድሞው ፕሬዚዳንት የአይደር አሊዬ መቃብርና ሀውልት ይገኛል፡፡ እኛም የተሰጠንን ቀያይ አበባዎች በፕሬዚዳንቱ መቃብር ስር ካስቀመጥንና የህሊና ፀሎት ካደረስን፣ ፎቶዎችንም ከተነሳን በኋላ ጊቢውን ለቀን ወጣን፡፡ አዘርባጃንን ለመጎብኘት የመጣ ሰው ይሄንን ቦታ እንዲጎበኝ አበባም እንዲያስቀምጥ የማድረግ ልማድ በአዘሪዎች ዘንድ መኖሩን እነ ኦርሃን ነገሩኝ፡፡

በመቀጠልም ወደሌላ ስፍራ ተጓዘን፡፡ ይሄኛው ስፍራ ደግሞ በአይነቱ ልዩና ከአገሪቱ ፓርላማ አካባቢ፣ ከአዘርባጃን ምልክት ከሆነውና ፍሌም ታወር ከሚባለው ግዙፍ ህንጻ ፊት ለፊት የሚገኝ የአዘርባጃን የነጻነት ታጋዮች የመቃብር ስፍራ ነው፡፡ ይህ መሀል ከተማ የሚገኝ የመቃብር ስፍራ በጣም የተዋበና ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ማየት በሚያስችል ከፍታ ላይ የተገነባ ማራኪ ስፍራ ነው፡፡

በዚህ ስፍራ ላይም ከሶቪየት ህብረት ጋር ለነጻነት በተደረገው ትግል የተሰዉ የ170 የአዘሪዎች ባለውለታዎች መቃብር እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተገንብቶ ይታያል፡፡ በዚህ ስፍራም የተሰጠንን አበባ አስቀምጠን ወደ ቀጣዩ ጉብኝታችን አቀናን፡፡

ቀጣዩ ጉብኝታችን የአዘርባጃን ሰንደቅ ዓላማ በትልቅ ከፍታ ነግሶ በሚውለበለብበት አካባቢ መሆኑ ተነገረን፡፡ አካባቢው ፍላግ ስኩዌር ይባላል፡፡ በዚህ አካባቢ ደግሞ የአገሪቷ ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ሙዚየምና ክሪስታል የሚል መጠሪያ ያለው ዘመናዊ አዳራሽ ይገኛል፡፡ ከሙዚየሙ አናት ላይ ደግሞ በዓለም ላይ በትልቅነቱ የሶስተኛ ደረጃን የያዘውና በዓለም የድንቃድንቅ መዘገብ ላይ የተመዘገበው ባለ ሰማያዊ፣ ቀይና አረንጓዴው የአዘርባጃን ሰንደቅ ዓላማ ይውለበለባል፡፡

ይህንን ሰንደቅ ዓላማ የተሸከመው ሰንደቅ ወይንም ቋሚ ብረቱ 162 ሜትር ቁመት ሲኖረው ባንዲራው ደግሞ 35 ሜትር በ70 ሜትር መጠን አለው፡፡ ሰንደቅ አላማውን እንደ ሶስቱ ፍሌም ታወሮች ሁሉ ከየትኛውም የከተማዋ ከፍል ላይ ሆኖ መመልከት ይቻላል፡፡ ሙዚየሙ ደግሞ ስለ ሰንደቅ ዓላማው ታሪክ የሚናገረው አለው፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኘው፡፡

አዘርባጃኖች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ያላቸውን ታሪክ የሚያሳይና በተለያዩ ዘመናት ይጠቀሟቸው የነበሩ ሰንደቅ ዓላማዎችን፣ የገንዘብ ኖቶችን፣ ሳንቲሞችን፣ የአገሪቱ የክብርና የጀግንነት ኒሻኖችን፣ በተለያዩ ክፍሎች የሚያገለግሉ የሰራዊታቸውን ዩኒፎርሞችና ሌላ ሌላም ታሪኮችን የሚዘክሩ ቁሳቁሶች በሙዚየመው ውስጥ አሉ፡፡ ይሄንን ሁሉ ታሪክም ጥሩ እንግሊዝኛ በምትናገረውና ፍልቅልቅ በሆነችው አሚና በተባለችው አስጎብኛችን ታግዘን ኮመኮምነው፤ የማስታዋሻ ፎቶም ተነስተን ወጣን፡፡

ይህ ሙዚየም ዙሪያውን የተከበበው በካስፒያን ባህር ሲሆን በባሀሩ ዳርቻም በክፍት መኪና በመሆን ተዟዙረን ጎብኝተነዋል፡፡ ይህ ባህር አዘርባጃንን ከጥቁር ባህር ጋር የሚያገናኛት አንዱ የኢኮኖሚዋ አጋር ነው፡፡ የመኪና ሽርሽራችንን ካበቃን በኋላም ወደ ምሳ አመራን፡፡ በዚህ መሀል የገረመኝ የሰዓቱ ከእኩለ ቀን ማለፉ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የጸሀይዋ እንደኛዋ ፀሀይ የማትፋጅ ፍጹም ተናፋቂና የማትጠገብ መሆኗ ነበር፡፡

ከምሳ መልስ ያከናወነውም የጉብኝታችን ዋና አጀንዳ የሆነውን ጉዳይ ነበር፡፡ በመጀመሪያው የጉዞ ማስታዎሻዬ ላይ ጠቀስ እንዳደረኩልዎት ለጉብኝታችን ምክንያት የሆነው አዘርባጃን ከአርሜኒያ ጋር ያላት የድንበር ግጭት ነው፡፡ አዘሪዎች አምባገነናዊና ወታደራዊው በሆነው የአርሜኒያ መንግስት የተወሰደባቸው ግዛት አላቸው። ይህ አካባቢ ናጎርኖ ካራባህ ይባላል። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የአርሜኒያ መንግስት በአስቸኳይ ከአካባቢው እንዲለቅ ውሳኔ ቢሰጥም ዛሬም ድረስ ወታደራዊው የአርሜኒያ መንግስት እንቢ እንዳለ ነው።

በዚህ ችግር ውስጥም የተነሳ የአዘርባጃን መንግስት ምን ያህል አስተዋይና ሰላም ናፋቂ እንደሆነ፣ ከጦርነትም ምንም የሚገኝ ነገር እንደሌለ የተረዳ ብልሀ መንግስት መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እንዴት? በዚህ ጉዳይ ያገኘሁትን መረጃና ምናልባትም እርስዎንም ሊያስደምም የሚችለውን የአዘሪዎችን ታጋሽነት፣ የየሚያሳየን ድርጊት ነገ እመለስበታለሁ፡፡

 

አርአያ ጌታቸው

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።