ብዙ ግፍ የተፈጸመባት ባለ ታሪኳ የአዘሪዎች ምድር Featured

09 Nov 2015

 

ባኩ የሚገኘውና የሆጃሌ ሰማዕታትን ለመዘከር የቆመው ሃውልት፤                   በጉባ ከተማ የሚገኘው የሰማዕታት ሙዚየም፤

 

የጉዞ ማስታወሻ

የመጨረሻ ክፍል

እነሆ ዛሬም አዘርባጃን ነኝ፤ ዋና መዲናይቱ ባኩ ላይ። ባኩ ቆንጆ ናት፤ ቆንጆዎች የሞሉባት የቆነጃጅት አገር። በዚህች ውብ ምድርና ህዝቦች ላይ ብዙ ውብ ያልሆኑ በደሎች በተለያዩ ጊዜያት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ታሪክም ከትቦታል። አዘሪዎች ይሄን ታሪካቸውን አዲሱ ትውልድም ይሁን እንደ እኔ ወደ አገራቸው ጎራ ያለ እንግዳ ሁሉ ያይላቸውና ያውቅላቸው ዘንድ ለበደሉ ሁሉ ያቆሟቸው ሀውልቶችና ቋሚ መዘክሮች አሏቸው።

አንድ የአገራችን አባባል አለ፤ «እኔ ሰላም አንድሆን ጎረቤቴን ሰላም አውለው» የሚል። እውነት ነው። ጎረቤቴ ሰላም ከሌለው እኔ የቱንም ያህል ሰላማዊ ብሆን የእሱ ችግር እኔምጋ መድረሱ አይቀርም። አዘርባጃኖችም ያጋጠማቸው ይሄው ነው።

አዘርባጃንን ከሚያዋስኗት አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው አርሜኒያን የሚያስተዳድረው ወታደራዊ መንግስት በአዘርባጃኖች ላይ በተደጋጋሚ የፈጸመውን በደል ለመስማት ቀርቶ ለማሰብም የሚከብድ ነው። ከብዙው በጥቂቱ ሁለቱን አስጎብኝተውናል።

እአአ በ2007 አዘሪዎች በአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ ጉባ በምትባለው ከተማ የሚገኘውን ስታዲየም ለማደስ ፈለጉ፡፡ መሀንዲሶቻቸውም ስታዲየሙን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስቸላቸውን የንድፍ ስራ ከጨረሱ በኋላ ቁፋሮው ይጀመራል፡፡ ይህ የግንባታ ቁፋሮ ግን ብዙም አልዘለቀም፡፡ ዛሬም ድረስ እንቆቅልሹ ያልተፈታ ጉዳይ አጋጠማቸው፡፡ የጅምላ መቃብር፡፡ ወዲያውኑም ስራው ይቋረጥና አርኪዎሎጂስቶች በቦታው ተተኩ፡፡

አርኪዎሎጂስቶችም ቁፋሮውን ገፍተውበት አምስት ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ላይ ደረሱ፡፡ ይህ ጉድጓድ ደግሞ በሰዎች አፅም የተሞላ ሆኖ አገኙት፡፡ አርኪዎሎጂስቶቹ ካገኟቸው በርካታ አፅሞች መካከል 24ቱ የህጻናት፣ 28ቱ የሴቶች ሲሆን የተቀረው የወንዶች መሆኑን በፍተሻቸው አረጋገጡ፡፡

አዘሪዎች ይህን አፅም በተገኘበት ስፍራ ላይ መጠለያ ቤት በመስራት እንዳለ ዓለም ይመለከተው ዘንድ አስቀምጠውታል፡፡ እኔም ዙሪያውን በቀይ አበባ የተሞላውን አጽም ስመለከት ሰውነቴ ተረበሸብኝ፡፡ የሰው አፅም አይቼ አላውቅማ፡፡ አስጎብኛችን እንደነገረችንም በወቅቱ ግድያው የተፈጸመው ዘግናኝ በሆነ መልኩ ለመሆኑ ማረጋገጫው ዛሬም ድረስ በተገኙት የጭንቅላት ቅሪቶቹ ውስጥ ረጃጅም ምስማር መሰል ብረቶች ተሰክቶባቸው መታየቱ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ታዲያ አርኪዎሎጂስቶቹ ስራቸውንም ሰርተው ሳይቋጩ ከጎናቸው ሌላ ሁለተኛ አጽም የተሞላበት ጉድጓድ አገኙ፡፡ አስጎብኛችን እንደነገረችንም ይሄ አጽም የተሞላው ጉድጓድ እስካሁን ድረስ አልተነካም፡፡ ዓለም የራሱን እርምጃ ይውሰድበት በሚል በዚያው በመጠለያው ውስጥ እንዳለ ነው፡፡

አርኪዎሎጂስቶቹ በጥናታቸው መጨረሻ የደረሱበት የጅምላ ጭፍጨፋው የተካሄደው እእአ በ1918 በአርሜኒያ ወታደራዊ መንግስት አማካኝነት በጉባ ይኖሩ በነበሩና የተራራው አይሁዶች በሚል መጠሪያ በሚታወቁት አይሁድ አዘሪዎች ላይ ነው፡፡

አጽሙ ከተገኘበትና ካረፈበት መጠለያ ፊት ለፊት ታሪኩን የሚገልጽ የተራራ አይሁዶችን ማንነትና ታሪክ የሚያስረዳ በተራራ ቅርጽ የተሰራ ዘመናዊ ሙዚየም ተገንብቷል፡፡

በከተማዋ ዛሬም ድረስ አይሁዶች ይኖሩባታል፡፡ እጅግ ጥንታዊ የሆነ ቤተ መቅደስም አላቸው፣ እኛም ጎብኝተነዋል፡፡ እስራኤላዊው ጋዜጠኛ አሚርም በዚህ ቤተመቅደስ ጸሎቱን አድርሶ ከተራራ አይሁድ ዘመዶቹ ጋር አውግቶ ነበር አመሻሹን ወደ ባኩ የተመለስነው፡፡

ሁለተኛው የጎበኘነው የሰማዕታት ሀውልት ደግሞ በዋና ከተማዋ ባኩ የሚገኘውና ሆጃሊ የሚባለው ነው፡፡ ይሀ የሰማዕታት ሀውልትም የተገነባው በተመሳሳይ በአርሜኒያ ወታደሮች እአአ በፌብሩዋሪ 25 እና 26 ቀን 1992 ሁለት ምሽቶች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ ለመዘከር ነው፡፡

የአርሜኒያ ወታደሮች በፌብሩዋሪ 26 ምሽት አምስት ሰዓት አካባቢ በሆጃሊ ከተማ ነዋሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ዘግናኝ በሆነ ግድያም 83 ህጸናት፣ 106 ሴቶች፣ 70 አረጋውያንን ጨምሮ በአጠቃላይ 613 አዘሪዎች ተገደሉ፡፡ ስምንት ቤተሰብ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ተገድሏል፡፡ 25 ህጻናት ወላጅ አልባ ሆነዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቁስለኛና ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ሲሆኑ 76ቱ ህጻናት ናቸው፡፡ አንድ ሺ 275 አዘሪዎች ደግሞ ተማርከው ተወስደዋል፡፡ 150 ያህሉ ደግሞ ዛሬም ድረስ የገቡበት አይታወቅም፡፡ በተጨማሪም አምስት ቢሊዮን ሩብል ያህል ንብረት ወድሟል፡፡

በአዘሪዎች ላይ የተፈጸመው ግፍ በዚህ አያበቃም፡፡ ሌላም ሌላም ግፍ በአርመኒያ ወታደራዊ መንግስት እንደተፈጸመባቸው ነው የተረዳሁት፡፡ በጣም የሚገርመው ግን አንድም የአዘርባጃን ዜጋም ይሁን ያነጋገርናቸው የመንግስት ባለጥልጣናትና የሲቪክ ሶሳይቲ አባላት አርሜኒያውያንን አይወቅሱም፡፡ እንደውም ለአርሜኒያ ዜጎች ትልቅ አክብሮትና ፍቅር እንዳላቸው በአዘርባጃንም በሰላም እንደሚኖሩ ነግረውናል፡፡ ጠላታችን ብለው የሚወቅሱትና የፈረጁት ዛሬም ድረሰ ስልጣን ላይ ያለውን ወታደራዊ መንግስት ብቻ ነው፡፡

አዘርባጃኖች በዚሁ ወታደራዊው የአርሜኒያ መንግስት ናጋርኖ ካራባህ የተባለ ግዛታቸውንም ተነጥቀዋል፡፡ ይህ የአዘሪዎች ግዛት በአርሜኒያዎች እጅ የገባው በተመሳሳይ በወታደራዊ እርምጃ ሲሆን የሞቱት ሞተው እግሬ አውጭኝ ሲሉ ስደት የወጡት የአካባቢው ነዋሪዎች አንድ ሚሊዮን እንደሆኑም ተነግሮናል፡፡ ይህ ቁጥርም በዓለም ላይ በአገር ውስጥ ከተፈጸሙ ዜጎችን የማፈናቀል ድርጊቶች መካከል ቅድሚያውን ይይዛል፡፡

አዘሪዎች ከካራባህ ለተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ስደተኞቸ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት በመስራት እንደማንኛውም የአዘርባጃን ዜጋ እየተማሩ፣ እየሰሩ፣ እየመረጡና እየተመረጡ እየኖሩ ናቸው፡፡ በትላልቅ የስራ ኃላፊነት ላይ ሳይቀር የተቀመጡ እንዳሉ በቆይታችን ወቅት ተመልከተናል፡፡

የአዘርባጃን መንግስት የተወሰደበትን ግዛት ለማስመለስ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊውን መንገድ በመከተል ለዓለም መንግስታትና ዓለም አቀፍ ድርጀቶች አቤት ብሏል፡፡ በዚህም አራት ጊዜ አራት ውሳኔዎች ተላልፈውለታል፡፡ አራቱም የተወሰደው ግዛት የአዘርባጃን መሆኑን አረጋግጠው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የአርሜኒያ መንግስት አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ውሳኔ ግን ሳይፈጸም እነሆ 20 አመታት አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሂክማት ሀይዬቭ "ይሄንን ግዛታችንን ለማስመለስ መሄድ ያለብንን ርቀት ያህል ሄደናል፡፡ እኛ በጦርነት አናምንም፡፡ በጦርነት አሸናፊም ተሸናፊም የለም፡፡ ስለሆነም ዓለም የወሰነልን ግዛታችን ሊመለስልን ይገባል፡፡ በጦርነት ለማስመለስ የሚያስችል ወታደራዊ አቅም አለን፡፡ የእኛ የመከላከያ በጀት የአርሜኒያን ጠቅላላ በጀት ሁለት ጊዜ ይበልጣል፡፡ የእኛ አገራዊ በጀት ደግሞ ከእነሱ በጀት በብዙ እጥፍ የሚልቅ ነው፡፡ የራሳችንን የጦር መሳሪያ ሰው አልባ አውሮፕላን ሳይቀር እናመርታለን፡፡ ይሄ ሁሉ አቅም አለን፣ ነገር ግን ጦርነት አንፈልግም" ሲሉ ነበር ሁላችንንም ያስደመመ ንግግር ያሰሙን፡፡

በእውነት በዚህ ንግግር መጨረሻ አፍሪካን አሰብኩ፡፡ አንድ የአፍሪካ መንግስት ጠላቴ በሚለው አገር መንግስት ላይ ይሄንን ያህል ብልጫ ያለው ወታደራዊ አቅም እያለው ግዛቱን ተነጥቆ 20 ዓመት ይታገሳል? አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው አዘሪዎችንና መንግስታቸውን አስተዋይና ብልህ ማለቴ፡፡

አዘሪዎች የካራባህን ጉዳይ ዓለም በውል እንዲያውቀላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ለዚያም ነው እኔን ጨምሮ 11 ጋዜጠኞችን ከተለያዩ ዓለማት ጠርተው ጉዳዩን ማስረዳታቸው፡፡ ከጦርነት ይልቅ ሚዲያውን መጠቀም እንፈልጋለን ሲሉም ነው የነገሩን፡፡

በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የፕሬዚዳንቱ አማካሪ፣ የሲቪክ ሶሳይቲ ማህበራት ተወካዮችና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች አቋማቸው ተመሳሳይ ነው፡፡

የአዘርባጃን የመጨረሻ ቀን ጉብኝታችን ለቀድሞው ፕሬዚዳንታቸው አይደር አልዬ መታሰቢያነት ያሰሩት እጅግ ታላቅና ዘመናዊ ሙዚየምን መመልከት ነበር፡፡ ይህ ሙዚየም በሁለት ክፍሎች የተዋቀረ የባህር ማዕበል ሲነሳ ውሃው የሚይዘውን አይነት ቅርፅ አስመስሎ የተሰራ ግዙፍ ህንጻ ነው፡፡ ውስጡም የፕሬዚዳንታቸውንና የአገሪቱን ሙሉ ታሪክ የሚያሳይ የተለያዩ ግን ዘመናዊ ግብዓቶች የተሟሉበት ነው፡፡ ሙዚየሙ ምንም አይነት አስጎብኝ አያስፈልገውም፡፡ ሁሉም ታሪኮች በተች ስክሪኖች ላይ የተጫኑና ጎብኝው እንደፍላጎቱ በምስል ወይንም በድምፅ አማርጦ የሚመለከታቸው ናቸው፡፡

ሁለተኛው የሙዚየም ክፍል ደግሞ የአዘርባጃንን ታሪክ የሚያሳይ ነው፡፡ ሙዚቃዎቻቸውን፣ አልባሳቶቻቸውንና አጠቃላይ ማንነታቸውን የሚያስተዋወቁበት ክፍል ነው፡፡ ይሄንን ስመለከት የመለስ ፋውንዴሽን ምን እየሰራ ነው ስል አሰብኩ፡፡ ለታላቁ መሪ አቶ መለስ እስካሁን ድረስ ከወረቀት ላይ ያለፈ ነገር አለመመልከቴ አሳዝኖኛል፡፡ እናም አልኩ የመለስ ፋውንዴሽን ሰዎች ወደ አዘርባጃን ሄደው ተሞክሮ ቢወስዱ መልካም ነው፡፡

በመጨረሻም የመጨረሻው ቀን መጣ፡፡ ወደ ውቢቷ አገሬ የምመለስበት ሰዓት ደረሰ፡፡ እናም ከመጨረሻው የእራት ግብዣ በኋላ ሁላችንም አድራሻ ተለዋውጠንና ተሰነባብተን ተለያየን፡፡ እኔም የበረራ ሰዓቴን አክብሬ እንደአመጣጤ ሁሉ በቱርክ አየር መንገድ አዲስ አበባ የገባሁት ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነበር፡፡ ከቦሌ ኤርፖርትም ትሁቱና ሰው አክባሪው የአዘርባጃን ኤምባሲ ዲፕሎማቱ ሚስተር ዛሁር ከጥሩ እንክብካቤ ጋር እቤት አደረሰኝ፡፡ ሲመለስም ከአዘርባጃን ይዣቸው ከመጣኋቸው ጥቂት ቃላት መካከል አንዷን ለሚስተር ዛሁር ጆሮ አደረስኳት «ሳሆል» ስል፡፡ አመሰግናለሁ ማለቴ ነበር፡፡ ዛሁር ተደስቶም ስቆም ነበር የተሰናበተኝ፡፡

የእኔም የጉዞ ማስታዎሻ እዚህ ላይ አበቃ፡፡«ያሻሲን አዘርባጃን» ረጅም እድሜ ለአዘርባጃን ማለቴ ነው፡፡ ደህና ይሁኑ፡፡

 

 

አርአያ ጌታቸው

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።