‹‹ዶከተረ›› ማለት…

23 Oct 2016

‹‹…አሁንስ በዛ! እነርሱም ነጋዴነቱን ተያያዙትና ዐረፉት!! ›› አሉ አንድ ዕድሜ ጠገብ አድማጭ የሚሉት ቢቸግራቸው፡፡ ለመሆኑ ‹‹እነርሱ›› የተባሉት እነማን ይሆኑ? ለዚህ ጥያቄ ምላሹን በሂደት እንደርስበታለን፡፡ መቼም መች ከማስታወቂያ ነገር ሌላ ሊሆን አይችልምና!!

እንደ እውነቱ ከተባለ የዚህ የማስታወቂያ ነገር ‹‹ጥቂት›› የሚባል ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹እጅግ›› ያ ብቻም ሳይበቃ ‹‹እጅግ በጣም›› የሚገርም ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ለነገሩማ በድንቅነትም ሳይገታ ወደ ማሳዘኑ ሳያዘነብል አልቀረም፡፡

በመሠረቱ ‹‹ማስታወቂያ›› ሲባል በቁሙ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት እስከዚህ ከበድ ያለ አይደለም፡፡ ‹‹ማስታወቂያ›› ማለት ያው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ድርጅት ለመግለጽ የፈለገውን ወይም ይተላለፍለት ዘንድ የወደደውን፣ለአደባባይ ድብቅ ሆኖ እንዳይከርም፣ ከሕዝብ ጆሮና ዓይን ሽሽግ ሆኖ እንዳያዘግም የፈቀደውን ነገር ጽፎ በሚታይ ቦታ ላይ የሚለጥፈው ወይም በራዲዮና በቴሌቪዥን የሚያስነግረው፣በጋዜጣ የሚያስነብበው መግለጫ …›› ነው፡፡ እንግዲህ ፍቺው ይኸው ነው፡፡ ከዚህ በላይ የሄደ ማስታወቂያ አንድያውን ‹‹ዐዋጅ›› ካልተባለ በቀር ሌላ መጠሪያ ሊሰጠው ከቶውን አይቻልም፡፡

አሁን በየዜና ማሰራጫዎች የምናስተውለው የማስታወቂያ ዓይነትና መልክ ግን እንዲያው ማስታወቂያው ‹‹እውን ማስታወቂያ ነውን?›› እስከማሰኘት አድርሷል፡፡ በተለይ ‹‹የግል ›› በተባሉት የዜና መንዣዎች!! ግና ዳሩ ያም ይሁንና የመንግሥት ራዲዮና ቴሌቪዥንም እንዲያው ‹‹ጥቂት ሻል ›› ይላሉ ለማለት እንደሆነ እንጂ ሙሉ በሙሉ የማይመለከታቸው ናቸው ብሎ ለመደምደም እንዳልተሞከረ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡

ለምሳሌ የቢራ ማስታወቂያን እንኳ ያደመጥን እንደሆነ ለዚህ አባባል ዓይነተኛ ማሳያ ሳይሆን የቀረ አይመስልም፡፡ ለአብነት ያህል በማስታወቂያው መቋጫ ላይ ‹‹ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ ›› የሚለው ማሳረጊያ ዘወትር እጅግ የሚደንቅ እየሆነ መምጣቱን እየታዘብን ጊዜ አሸምግለናል፡፡

ከሆነስ ሆነና ያን ያህል በአርኪነቱና በጣዕሙ እየተወደሰ፣በጥራቱ እየተሞገሰ ብዙ የተባለለት ቢራ በዕድሜ ገደብ መከለሉ፣ ‹‹ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የማይሸጥ›› መባሉ ጥቂት አያወያይ፣በአስተሳሰብ አያለያይ ይሆን? እስከነ አካቴው አጠያያቂስ አያደርግ ይሆን?

ለመሆኑ የትኛው ዘመን አዳጊ ወጣት ነው እንዲያ ብዙ የተባለለትን መጠጥ ቢያንስ ጥቂት እንኳ ለመቅመስ የማይመኝ? ያውም እንዲያ ‹‹የልብ አድርስ፣መንፈስ አድስ….›› እየተባለ ሲወደስ፣ ሲሞገስ የተደመጠውን ዕፁብ ድንቅ ቢራ!! ወይስ አሥራ ስምንት ዓመት ሆኖት የዕድሜ ልደት ያከበረው ታላቅ ወንድሙ ወይም ያከበረች ታላቅ እህቱ ፣አልያም ጓደኛውና ሌሎችም ሆነው ደስ ብሏቸው ሲጎነጩ፣እርሱ ግን እያየ ሲጎመጅ ሊቀር ነው?

አንዳንድ ወላጆች በርግጥ ልጆቻቸውን በሥነ ሥርዓት አሳድገው የመጠጥን ጎጂነት አሳምነው የሚታዩ አጋጥመውኛል፡፡ አንዳንዶች ግን እንኳን ልጆቻቸውን ‹‹በዲሲፕሊን›› ኮትኩተው ሊገኙና ራሳቸውም በቀኝ እጃቸው ልምጭ ይዘው፣ በግራ እጃቸው ጠርሙሱን ጨብጠው እየተጎነጩ ‹‹ሥነ ሥርዓት! ሥነ ሥርዓት!›› እያሉ የሚያፌዙ መኖራቸውን እኔ ራሴ በግሌ አይቻለሁ፡፡ በአሳዛኝ መልኩ ለዚህ ዓይነቱ ምስክርነት የበቃሁበትን ኩነት አልዘነጋውም፡፡

አልፎ አልፎ ደግሞ ‹‹አይዞህ! ጥቂት ቀን ነው የቀረህ ትደርስበታለህ፤አይዞሽ! ጥቂት ቀን ነው የቀረሽ ትደርሺበታለሽ ፤ወዘተ፣ወዘተ..›› እያሉ ለልጆቻቸው የቢራ ቀጠሮ የቆረጡ መሆናቸውን እታዘብ ዘንድ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡ ወላጆቹ በውኑ ቢቸግራቸው እንጂ ወደው እንዳልሆነ ግን መገንዘብ የሚያሻን ይመስለኛል፡፡ ማስታወቂያው ለዚህ ዓይነቱ ድርጊት አሳምሮ ይጋብዛልና!!

የዚህ የማስታወቂ ጉዳይ እንዲያው እንደ ዋዛ ሊታለፍ የሚገባው አይመስልም፡፡ በአሁኑ ‹‹ሠለጠነ›› በተባለ ዘመናችን ገጽታው ለየት ያለ ሆነ እንጂ ጥቂት ሰንበትበት ባለበት ወቅት የነበረውን መልክ ለአፍታ ዘወር ብለን ብንቃኝ መልካም ነው፡፡ ያኔ እንደ ዛሬው የግል ጣቢያዎች እንደ ልብ በሀገራችን ስርጭት ባልተፈቀደላቸው ወቅት ያው ‹‹የኢትዮጵያ ራዲዮ›› ተብሎ በልሳነ መንግሥትነት የሚያሰራጨው ብቻ ስለነበር ‹‹ማስታወቂያ በራዲዮ ተነገረ›› ከተባለ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ‹‹ መንግሥት ተናገረ›› የመሆን ያህል ይቆጠር እንደነበር እኔ ራሴ የማስታውሰው ኩነት ነው፡፡ ዛሬም እንደ ጥንቱ የከፋ አይሁን እንጂ፣ ሙሉ በሙሉ ‹‹መንግሥት ዐወጀ›› አይባል እንጂ ጭርሱን ጠፍቶ እንደ ሰሙ ‹‹ዘመናዊ ብቻነትን አግኝቶ ‹‹አንዳችም እንከን የሌለው ነው›› ማለት ግን አይደለም፡፡ ማስታወቂያ ሲነገር ከአንድ የሆነ ‹‹መንፈስ›› የመጣ ያህል መቆጠሩን ዛሬም ታዝቤአለሁ ..‹‹ጥሩ ባይሆን መች ይናገሩት ነበር!›› ሲባልም ሰምቻለሁ፡፡..ይህን ልብ ማለት ያሻል፡፡

ወደ ቢራው ‹‹ልዩ ማስታወቂያ›› ደግሞ መለስ ስንል በዚህ በሎተሪ መልክ በጠርሙሱ ቆርኪ ውስጥ ያለው ቁጥር ትክክለኛ ባለ ዕጣ ሆኖ ሲገኝ ‹‹መኪና፣ፍሪጅ፣ሞባይል፣ምኑ ቅጡ፣ስንቱ ስንቱ ይወራል፡፡ እንግዲህ መቼም መች ‹‹ዕድል አንድ ነው›› የሚባል አነጋገር ቢኖርም ደጋግሞ ቢራውን እየጠጣ የዕድሉን ሁኔታ በጠርሙስ ቆርኪ ሲሞክር፣ሲጥር፣መገኘቱን አይተውም፡፡ በየሄደበት መሸታ ቤት ጠርሙስ ደርድሮ ሲቆጥር አምሽቶ የሚገባ እየበረከተ መሄዱን ሳናስተውል አልቀረንም፡፡

እዚህ ላይ ግን መዘንጋት የሌለብን ተጠጥቶ ሳይሰከር አለመቅረቱን ነው፡፡ ታዲያ በየዕለቱ ያን ያል ቢራ እየተጠጣ፣ያንም ያህል እየተሰከረ በመጨረሻ የተጓጓለት መኪና፣ፍሪጅ፣ሞባል ወይም ሌላ ዕጣ ብዙውን ጊዜ አይገኝም፡፡ በከንቱ ብር ተመንዝሮ፣በከንቱ ተሰክሮ ቀረ ማለት ነው፡፡ መቼም ‹‹ብዙ የጠጣ ባለ ብዙ ጣጣ›› ነውና የጤና ጉስቁልናውስ ጉዳይ እንዴት ይረሳል? የትዳሩስ፣ የሕይወቱስ አጠቃላይ ሁኔታ እንዴት ዋጋ ያጣል?

በውኑ የዚህ የማስታወቂያ ታሪክ ተነግሮም፣ ተወርቶም ያልቃል ማለት ዘበት ነው፡፡ ይህንን ያህል እንግዲህ በቢራው ከቆየን ጹሑፉ በመጀመሪያ ሲንደረደር ወደ አመለከተው ጉዳይ ተሻግረን ከእልባት እናድርስ፡፡

እናም ‹‹አሁንስ በዛ !እነርሱም ነጋዴነቱን ተያያዙትና ዐረፉት!!›› ሲሉ አንድ የዕድሜ ባለጸጋ አዛውንት ‹‹ተናገሩት›› ወደ ተባለው እናምራ ፡፡ ለመሆኑ ‹‹ነጋዴነቱን›› የተያያዙት እነማናቸው? እኒያ ‹‹እነርሱ›› የተባሉት?

ዛሬ ዛሬ እንደ ‹‹ፋሽን›› ተቆጥሮ የሕክምና ባለ ሙያዎች ከጸጉር ሠሪ፣ ከአረቄ ቸርቻሪ እና ከሌላውም ባላነሰ፣ አንዳንዴም በበለጠ አኳኋን የማስታወቂያ ዕወጃውን ተያይዘውት ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም ‹‹ እገሌ ነጋዴ ነው ወይስ ሐኪም?›› ተብሎ ሰውን ግራ ወደ ማጋባት ደረጃ የተደረ ሰበት ወቅት ላይ መሆናችንን መካድ ጅልነት ይመስለኛል፡፡

በመሠረቱ ‹‹ሐኪም›› ከተባለ በሕክምና ሳይንስ የተመረቀ፣በሕክምና ተግባር ላይ የተሠማራ ባለሙያ፣ ለተግባሩ ሥምረት፣ ለቃል ኪዳኑ ክብረት ዋጋ የሚሰጥ ልዪ ባለሙያ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ማስታወቂያቸዉን ያየና ያደመጠ ሰው ያ የተገባ ቃል ኪዳን ምን እንደዋጠው ማወቅ ይሳነዋል፡፡

እንግዲህ ‹‹ነጋዴ›› ማለት ትርፍ ለማግኘት ሲል የሚሠራ ፣የሚሸጥ፣የሚለውጥ የሚሸቅጥ ነው፡፡ እንደ ሐኪም ለሰብዓዊ ግልጋሎት፣ ለተግባረ ረድኤት ራሱን ሰውቶ፣ቃል ኪዳን ገብቶ የሚገኝ አይደለም፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ግን ‹‹ዶከተረ›› ማለት ‹‹ነገደ›› እንዲያ ሲልም ‹‹ሸጠ፣ ሸቆጠ›› ከማለት ምንም እንደማይተናነስ ከመታዘብ አልታቀብንም፡፡ አንድ ሐኪም ክሊኒክ በሚከፍትበት ጊዜ እንኳ የአካባቢውን አቀማመጥ የሚያጠናው ከትርፍ አኳያ ብቻ ሆኗል፡፡ በተለይ በላቦራቶሪ፣ እንደነ አልትራ ሳውንድና ራጂ ባሉ የራዲዮሎጂ መሣሪያዎች አማካይነት የሚካሄደው ንግድ ይህ ነው አይባልም፡፡ እንዲያውም በማስታወቂያዎ ቻቸው ውስጥ ያሉትን የቃላት አጠቃቀሞችና ዘዬዎች ብናስተውል ከመንግሥተ ሰማያት የወረዱ፣ከተአምረ መንፈስ ቅዱስ ጋር የተዋሀዱ ያህል ሆነው ነው የሚቀርቡት፡፡ የግል መድኃኒት ቤት ሳይቀር በዚያው በክሊኒካቸው ቆርቁረው የሚጧጧፈው ንግድ አያድርስ ነው፡፡

‹‹አይበለውና ሕመም ቢያጋጥሞትም የ…..ክሊኒክ አለልዎት›› እያሉ በሥልጣነ መለኮት ሙት የሚያስነሡ፣ ሕሙም የሚፈውሱ፣ የወጣች ነፍስ የሚመልሱ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ታዲያ ነጋዴስ ከዚህ ወዲያ ምን አደረገ ? በዛሬ ጊዜ ‹‹ዶከተረ›› ማለት ‹‹ነገደ፣ሸጠ፣ሸቀጠ›› እንጂ ሌላ ስም አይወጣለትም፡፡ ብቻ…… ጤንነቱን አንጣ እንጂ በእነርሱ በኩል ያለው ተስፋ ያለቀለት ይመስለኛል፡፡

በሰላም ያገናኘን

አሸናፊ ዘደቡብ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።