የአሜሪካንና የሰሜን ኮሪያ ውዝግብ

15 Feb 2017

የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ሙከራ

በዛሬዋ ዕለት  እ.አ.አ የካቲት 8ቀን 1998 እና 1979 አሜሪካ ውጤታማ  የሚባሉ ሚሳይል የማስወንጨፍ ሙከራዎችን አድርጋ ነበር፡፡ ከ38 ዓመት በኋላ ሰሜን ኮሪያ የተባበሩት መንግሥታት ያስቀመጠውን ሚሳይል የማስወንጨፍ ሙከራ ማዕቀብ ስምምነትን በመጣስ እኤአ የካቲት 12ቀን2017  ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያውን ሚሳይል የማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጓን ቢቢሲ የዜና ማሰራጫ አውታር ዘግቧል፡፡

በሰሜን የኮሪያ ልሳነ ምድር ፒዮንጋንግ ግዛት አየር ጣቢያ በኪም ጆንግ መሪነት  እንዲወነጨፍ የተደረገው ሚሳይል ስኬታማ በሆነ መልኩ ወደ ጃፓን ባህር አቅጣጫ 500 ኪሎ ሜትር አካባቢ አምዘግዝጎ ማረፉን ደቡብ ኮሪያ ገልፃለች። የአሁኑ የሰሜን ኮሪያ የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ በተለያዩ አገራት ውግዘት አስከትሎባታል። አሜሪካን፣ ጃፓን፣ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ለተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት በማድረግ ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡

 ሀገራቱም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የሰሜን ኮሪያን የሚሳይል ሙከራም ድርጊት እንዲሁ አውግዞታል። የኔቶ ዋና ፀሃፊ ጀንስ ስቶተንበርግ ፒዮንግያንግ ውጥረት ከመፍጠር እንድትቆጠብ እና ከአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር ውጤታማ ውይይት እንድታደርግ አሳስበዋል።

የአውሮፓ ህብረትም ሙከራውን ያወገዘ ሲሆን፥ ሀገሪቱ አለም ዓቀፍ ግዴታዎችን በተደጋጋሚ መጣሷ ፀብ አጫሪነት ያለው ተግባር  ነው፤ ይህም ተቀባይነት የለውም ብሏል።

 በተመሳሳይ ትራምፕ ድርጊቱን አውግዘው እንደዚህ አይነቱን ድርጊት አንታገስም ብለዋል፡፡ የፒዮንያንግ ሚሳይል ማስወንጨፍ ለአዲሱ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ትልቅ ፈተና መሆኑን ተንታኞች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም ከጃፓን ጎን እንደሚቆሙ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ ሚስተር ትራምፕ ለጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሺንዞ አቤ እንዳረጋገጡት “አሜሪካን ከጃፓን ጎን ትቆማለች ፡፡ ትልቅ አጋሯም ትሆናለች ፡፡መቶ በመቶ “ብለዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እሁድ ዕለት  በተደረገው የሚሳይል ሙከራ መደሰ ታቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ሙከራው “የሀገሪቱን ጥንካሬ የሚጨምር ነው” ብለዋል። የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ፒዮንግያንግ የሚሳይል ትንኮሳ ሙከራውን ያደረገችው አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ምላሽ ለማድመጥ  ነው ብሏል።

            ባለፈው ጥር ወር የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጦራቸው ረዥም ርቀት የሚጓዝ ሚሳይል ለመሞከር እንደተቃረበና አሜሪካም መድረስ እንደሚችል ተናግረው ነበር ፡፡ሚስተር ትራምፕ በቲውተር ገፃቸው እንዳሰፈሩትም ድርጊቱን “ሊሆን የማይችል “ሲሉ በቁጣ መግለፃቸው የሚታወስ ነው ፡፡

የባሊስቲክ ሚሳይሉ ምድር ለምድር ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት የሚምዘገዘግ ነው ተብሏል። የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የዜና ወኪል ኬ ሲ ኤን ኤ እንደዘገበው፥ይህን የተሳካ ነው የተባለለት የሚሳይል ሙከራ “ፑክጉክሶንግ 2” የተሰኘው ሚሳይል ኒዩክሌር መሸከም ይችላል ተብሏል።

ይህ የአገሪቱ የሚሳይል ሙከራ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው ሲሆን በተያዘው የፈረንጆች ዓመትም ስድስተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከኒውክሊየር መርሃ ግብሯ ጋር በተያያዘ ከምዕራባውያን ጋር ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ፒዮንግንግ መርሃ ግብሯን ከማቋረጥ ይልቅ አጠናክራ መቀጠሏን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 ለሁለተኛ ጊዜ ተደርጎ የነበረው  የሚሳይል ሙከራ ስኬታማ ሳይሆን አየር ላይ ተበታትኖ እንደቀረ ይታወሳል፡፡ ሮዶንግ; የሚባለው ሚሳይል እስከ 1300 ኪሎ ሜትር ያህል የመወንጨፍ ብቃት አለው ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የሚሳይል ሙከራውን ተከትሎ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ከጸብ አጫሪ ድርጊቷ እንድትቆጠብ አስጠንቅቃ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሰሜን ኮሪያ ዓለም አቀፉን ህግ በሚጻረር መልኩ የኒውክለር ሙከራ በማድረጓና ሳተላይት በማስወንጨፏ አዲስ ማዕቀብ ሀገሪቱ ላይ መጣላቸውም ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም በሙሉ ድምፅ ድርጊቱን ማውገዙንና የዓለም አቀፍ ህግ ተላልፋለች በሚል በአይነቱ ከባድ የተባለለትን ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

ፒዮንግያንግም ዋሽንግተን ማዕቀቡንና ሌሎች በአገሪቱ ላይ የምታደርጋቸውን ትንኮሳዎች ካላቆመች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ሙሉ ለሙሉ ለማቋረጥ እንደምትገደድ ማስጠንቀቋን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

 እአአ ሃምሌ1ቀን2008 አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሚሳይል መከላከያ ሃይል ለማሰማራት መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ስምምነቱ ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘርባትን የጠብአጫሪነት ትንኮሳ ለመመከት ያለመ መሆኑን መገለፁ የሚታወስ ነው፡፡ ዘ ተርሚናል ሃይ አልቲቲዩድ ኤሪያ ዲፌንስ/THAAD/ የተሰኘው የሁለቱ አገራት የጸረ ሚሳይል ሃይል  የሚሰማራበት ትክክለኛ ቦታና ማን እንደሚቆጣጠረው ከሁለቱም ወገን ግልጽ መረጃ እንዳልተሰጠ ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

ፒዮንግያንግ ባለፈው ዓመት በዚሁ ወር የረጅም ርቀት ሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በጉዳዩ ዙሪያ ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ሀገራት አሁን በደረሱበት የሚሳይል መከላከያ ስምምነት መሰረት የሚሰማራው ትሃድ የተባለው ሃይል ከፒዮንግያንግ በኩል የሚሰነዘርን የተወንጫፊ ሚሳይል ጥቃት ማክሸፍ የሚችልና ሚሳይሎችን አስቀድሞ መከላከል የሚችል ነው ተብሏል፡፡

ፒዮንግያንግ ይህን ማስጠንቀቂያም ሆነ ማስፈራሪያ ከእቁብም ሳትቆጥረው እኤእ  ነሀሴ 4ቀን 2016 ዓ.ም የባላስቲክ ሚሳይል ሙከራ አድርጋለች፡፡ አገሪቱ ያስወነጨፈችው ሚሳይል በጃፓን ግዛት በሚገኝ ባህር ውስጥ መውደቁም ይታወሳል፡፡ ሚሳይሉ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር መምዘግዘግ የሚችል እንደሆነም የደቡብ ኮርያ እና ጃፓን  በወቅቱ አስታውቀዋል፡፡ ፒዮንግ ደቡብ ኮርያ እና አሜሪካ የመከላከያ ሚሳይሎችን ለመትከል እቅድ መንደፋቸውን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ፍተሻዋን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ የጦር መሳሪያ ፍተሻው አገሪቱ አጎራባቾቿ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያላትን ፍላጎት ያሳያል ሲሉ የደቡብ ኮሪያ እና የጃፓን መንግሥታት አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት ለመከላከልና በአገሪቱ አስተማማኝ የጸጥታ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሆኑን ገልፀው ፤ የሚሳይል መከላከያ ሃይሉም በፍጥነት ወደተግባራዊ ስራው እንደሚሰማራ የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።