የአሜሪካ አዳዲስ ማዕቀቦች Featured

28 Jul 2017

አዲሱ የማዕቀብ ረቂቅ ይፋ የሆነው ፕሬዚዳንት ትራምፕና ፕሬዚዳንት ፑቲን በጀርመን ተገናኝተው ከመከሩ አንድ ወር እንኳ ሳይሆናቸው ነው፤

የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሩስያ፣ በኢራንና በሰሜን ኮሪያ ላይ የሚጣሉ አዳዲስ ማዕቀቦችን ለማፅደቅ በአብላጫ የድጋፍ ድምፅ ወስኗል፡፡ ውሳኔዎቹም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራቱ ላይ ማዕቀቦችን ከመጣላቸው አስቀድመው የአገሪቱን ፖለቲከኞች ይሁንታ ለማግኘት ያስችሏቸዋል ተብለዋል፡፡

የማዕቀቦቹ ረቂቅ ሃሳቦች የምክር ቤቱን አባላት ይሁንታና ድጋፍ አግኝተው ይፋ የሆኑት ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ መግባቷና አለመግባቷ እየተመረመረ ባለበት ወቅት ላይ መሆኑ ነገሩን አስገራሚ አድርጎታል ተብሏል፡፡

ኢራን ሽብርተኝነትንና ሽብርተኞችን ትገድፋለች፤ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በተደጋጋሚ የሚሳይል ሙከራዎችን እያደረገች ነው በሚሉ ክሶች ሰበብ በሁለቱ አገራትም ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን ለመጣል የሚያስችሉ የውሳኔ ረቂቆችም ይፋ ተደርገዋል፡፡

ምክር ቤቱ ያሳለፋቸውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቦች ይፋ መደረግን ተከትሎ ሩስያና ኢራን ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አላባከኑም፡፡ የሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ሪያብኮቭ፣ እርምጃው ዋሽንግተንና ሞስኮ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ የሚያሻክር እንጂ የሁለቱን አገራት ትብብር የሚያጠናክር እንዳልሆነ ለኢንተርፋክስ የዜና አገልግሎት ተናግረዋል፡፡

እርምጃው የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት ላይ እጅግ የበዛ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው” በማለት ለዜና አገልግሎቱ ገልፀዋል፡፡

የሩስያ የላይኛው ምክር ቤት አባል የሆኑት ኮንስታንቲን ኮሳችዮቭ በበኩላቸው ሞስኮ ለዋሽንግተን ድርጊት የሚሆን ምላሽ ማዘጋጀት እንደሚገባት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ኮሳችዮቭ በፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ማዕቀቡ የአሜሪካን እና የሩስያን ግንኙነት ማሻሻል ሳይሆን ወደባሰ አዘቅት ውስጥ ይከተዋል፡፡

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ የማዕቀብ ውሳኔው በግልፅ ጥላቻን የሚያመለክት እርምጃ በመሆኑ የኢራን መንግሥት ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ቴህራን ለዋሽንግተን የምትሰጠው ተገቢ የተባለው ምላሽ ምን እንደሆነ ግን በግልፅ የታወቀ ነገር የለም ተብሏል፡፡

ሪፐብሊካኖች በብዛት የተቆጣጠሩት የአገሪቱ ምክር ቤት (ሴኔት) አሁን ይፋ የተደረገውን የማዕቀብ ረቂቅ በከፍተኛ ድጋፍ እንዳሳለፈው ይታወሳል፡፡

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ኤድ ሮይስ፣ ማዕቀቡ የሚጣልባቸው ሦስቱም አገራት የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚቃረኑ ተግባራትን እየፈፀሙና የጎረቤቶቻ ቸውና የቀጠናቸውን ሰላም እያደፈረሱ ያሉ በመሆናቸው ቅጣቱ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል፡፡

የማዕቀቡ ረቂቅ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ቀርቦ ይሁንታ የሚያገኝበት አልያም ውድቅ የሚደረግበት ቀን መቼ እንደሆነ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡

የአልጀዚራዋ ዘጋቢ ሄይዲ ዦ-ካስትሮ ከዋሽንግተን ዲሲ ባስተላለፈችው ዘገባ፣ ረቂቅ የማዕቀብ ሃሳቡ በሴኔቱ ይሁንታ አግኝቶ በተያዘው ወር መጨረሻ ለፕሬዚዳንቱ ፊርማ እንደሚቀርብ ይጠበቃል ብላለች፡፡ ሪፐብሊካኖች በብዛት የተቆጣጠሩት የአገሪቱ ምክር ቤት (ሴኔት) አሁን ይፋ የተደረገውን የማዕቀብ ውሳኔ የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቅ ቀደም ብሎ በከፍተኛ ድጋፍ ማፅደቁ፣ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ትራምፕ ከሩስያ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው የሚለው ስጋታቸው ከፍ ማለቱን የሚያሳይ ነው ብላለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ የአልጀዚራዋ ዘጋቢ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ የማዕቀቡን ሀሳብ ይሁንታ ሰጥተውት የሚያፀድቁት ከሆነ ሩስያ በአወዛ ጋቢው የ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ መግባቷን እውቅና ይሰጣሉ፤ በምክር ቤቱ የቀረበውን የማዕቀብ ረቂቅ የማያፀድቁት ከሆነ ደግሞ የቅርብ አማካሪዎ ቻቸውና የቤተሰባቸው አባላት ሰውየውን ወደ ነጩ ቤት ለማምጣት ከሩስያ ጋር ግንኙነት አድርገዋል ተብለው እየተብጠለጠሉ የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል” ብላለች፡፡

በአሁኑ ወቅት ሩስያ በአወዛጋቢው የ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ መግባቷና አለመግባቷ እየተመረመረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ምርመራው ፕሬዚዳንት ትራምፕን ብዙ ያስደሰተ አይመስልም፡፡ ለዚህም ነው ፕሬዚዳንቱ “ምርመራው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ውጤት ለመቀበል ባልፈለጉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የተጠነሰሰ ሴራ ነው” በማለት የተቃወሙት፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን የጨበጡት አግባብ ባልሆነ መንገድ ነው” የሚል የፀና አቋም ያላቸው የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በየዕለቱ ሰውየው ላይ ምርመራ እንዲካሄድባቸው የውሳኔ ሃሳቦችን ከማቅረብ አልቦዘኑም፡፡ ለአብነት ያህል ሰሞኑን ፕሬዚዳንቱ ከሞስኮና ከክሬምሊን ሰዎች ጋር የነበራቸውን የፋይናንስ ግንኙነት ለማጣራት እንዲችሉ የግምጃ ቤት ሰነዶችን ለማግኘት የሚያስችል ሃሳብ አቅርበው በሪፐብሊካውያኑ ውድቅ እንደተደረገባቸው ይታወሳል፡፡

አንተነህ ቸሬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።