ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ስልጣን ለቀቁ፤ ቀጣይስ ምን ይፈጠራል? Featured

01 Aug 2017

ሥልጣናቸውን የለቀቁት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ

 

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኃላፊነታቸው ካገዳቸው በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል። ቀጣይስ ምን ይፈጠራል? ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ስልጣናቸውን ለቀቁ? የእርሳቸውን ስልጣን መልቀቅ ተከትሎስ በቀጣይ ምን ይሆናል? የሚለውም የሰሞኑ የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛ አጀንዳና መነጋገሪያ ሆኗል።

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባም፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መውረድ «ፓናማ ፔፐርስ፤ የፓናማ ሰነዶች» በሚል የሚታወቁት የሚስጥር ሰነዶች ቀዳሚና ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ሰነዶች በርካታ የቀድሞና የወቅቱ መሪዎች፤ የቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች ያገኙትን ከፍተኛ ገንዘብ በአገራቸው በሚገኙ ባንኮችና ሌሎች ተቋሞች በማስቀመጥ በህጋዊ መንገድ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ በድብቅ ወደውጭ እያሸሹ በምስጢር ኩባንያዎችና አክሲዮኖች ስም ከግብር ነፃ በሆነ መንገድ በማትረፍ ህገወጥ ተግባር ላይ በስፋት መሰማራታቸውን ያረጋግጣሉ።

በዚህ መንገድ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ስምና ሌሎች መረጃዎች የያዙት እነዚህ ሰነዶች ከ11ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፤ «ሞሳክ ፎንሴካ» በተባለና ከአርባ ዓመታት በላይ ሲሰራ የቆየው የፓናማ የጥብቅና ድርጅት ስር የነበሩ ናቸው።

ድርጅቱ የአፍሪካን የሚገኙትን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች፤ ከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ ባለሀብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ከአገራቸው የሚያሸሹትን ገንዘብ ኩባንያዎችን ያቋቋሙ አሊያም አክሲዮኖችን የገዙ በማስመሰል ከግብር ነፃ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ህገ ወጥ ገንዘብ ሕጋዊ እያስመሰለ የማዘዋወር ብቃት ያለው ነው። ከውጭ አገሮች በሕገወጥ መንገድ የሚወጣውን ገንዘብ የሚያስቀምጠው ወይም በሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርገውም በተለያዩ አገራት በሚያቋቁሟቸው የምስጢር ኩባንያዎች ነው።

ድርጅቱ በምስጢር ጠባቂነታቸው ከታወቁ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መካከል አንዱ ምናልባትም ግንባር ቀደሙ እንደሆኑም መሪዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገንዘባቸው እንዲጠበቅ አሊያም በስራ ላይ እንዲያውል ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን ይሰጡታል።

ይሁንና ከሁለት ዓመት በፊት የድርጅቱ የምስጢር ሰነዶቹ ማንነቱ ባልተገለፀ የመረጃ ምንጭ አማካኝነት ይፋ ወጥተዋል። የምስጢር ጠቋሚ ግለሰብም ሰነዶቹን «ሱዴች ዛይቱንግ» ለተባለው የጀርመን ጋዜጣ ያቀበለ ሲሆን፤ ጋዜጣውም ከዓለም ዓቀፉ የምርመራ ጋዜጠኝነት ኅብረት ጋር በመተባባር ከሰማንያ አገራት መገናኛ ብዙኃን በተውጣጡ ጋዜጠኞች አማካኝነት ምርመራ ካደረገ በኋላ ሰነዶቹን ይፋ አድርጓቸዋል።

ከዚህ ምስጢራዊ ሰነድ ጋርም በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ በማሸሽና ከግብር ነፃ በሆነ መንገድ አትራፊ ለመሆን የሚታትሩ  በርካታ የዓለማችን መሪዎች ስም አብሮ ወጥቷል። የቀድሞው የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፣ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ፣ የሊቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ፣ እንዲሁም የግብፅ የቀድሞ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ይገኙበታል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍም የዓለም ባለፀጐችና ባለሥልጣናት ገንዘብና ንብረታቸውን እንዴት ከሕዝብ ሸሽገው ከግብር አርቀው እንደሚያስቀምጡ ከሚያስረዳው ሰነዱ ጋር የሚተሳሰር ስም ካላቸው መሪዎች አንዱ ናቸው። የሚስጠራዊን አደባባይ መውጣት ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰነዱ በልጆቻቸውና በሃብታቸው ዙሪያ ያወጣውን ዘገባ ሲያስተባብሉና የቤተሰባቸው ሃብት በህጋዊ መንገድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ ያካበቱት እንደሆነ ለማሳመን ሲወተውቱ ቆይተዋል። የጉዳዩ እያደር ትኩስ መሆን ትኩሳት የሆነበት የፓኪስታን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታዲያ ጉዳዩ እንዲመረመር ትዕዛዝ አስተላልፏል። በትዕዛዙ መሰረተም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት አስራ አምስት ወራት የተለያየ ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቷል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሙስና ጋር በተያያዘ የቤተሰባቸውን ሀብት ካጣራ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልጆቻቸው ከሀገር ውጭ ኩባንያ እንዳላቸው አረጋግጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከገቢያቸው በላይ ኑሮን እየኖሯት መሆኑንና በዱባይና በለንደን በርካታ ሃብትና ንብረት እንዳላቸው በማረጋገጥ ከስልጣናቸው እንዲታገዱም በሙሉ ድምጽ ወስኗል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሙስና ዶሴ እንዲከፈትና ክስ እንዲመሰረትባቸው የተጠየቀ ሲሆን፤ ክሱ ደግሞ ልጆቻቸውን፤ የሀገሪቱን የገንዘብ ሚኒስተር ኢሻቅ ዳርና ሌሎችንም ይጨምራል ነው የተባለው።

ፓኪስታን ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀችበት ከዛሬ ሰባ ዓመት በፊት አንስቶ ላለፉት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ያገለገሉ መሪዎች አምስቱን ዓመት የስልጣን ዘመን ቆይታቸውን በሰላም አጠናቀው አያውቁም። አብዛኞቹ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተገርስሰዋል፤ አሊያም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከኃላፊነት ተነስተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ በፓርቲያቸው ግፊት ቀሪዎቹ ደግሞ በግድያ ከስልጣን ተወግደዋል።

ናዋዝ ሸሪፍም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንበረ ስልጣን ብቅ ያሉት በ1990 ነው። ይሁንና ስልጣናቸውን ማቆየት የቻሉት ለሶስት ዓመታት ብቻ ነበር። በ1997 ዳግም ወደ ስልጣን ቢመጡም ከሁለት ዓመት በኋላ በፔርዜዝ ሙሻረፍ መፈንቅለ መንግስት ስልጣናቸውን ተቀምተዋል። ለዓመታት ለስልጣን ርቀው ለሶስተኛ ጊዜ እኤአ በ2013 ወደኃላፊነት የመጡት ሸሪፍ፤ ላለፉት አራት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

 በዚህ ሂደት አምስቱን ዓመት የስልጣን ዘመን ቆይታቸውን በሰላም በማጠናቀቅ የቀደመ ታሪክ ለመቀየርና አንድ ዓመት ብቻ የቀራቸው ሸሪፍም፤ ከሰሞኑ እንደወትሮው በኃይል ሳይሆን በሙስና ምክንያት በመጨረሻዋ ሰዓት ከስልጣን ወርደዋል።

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባም፤ ከሚስጥራዊ ሰነዶቹ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ቤተሰቦቻቸውና ጠበቃቸው ነፃ የሚያደርጋቸውን በቂ መረጃ ለአገሬው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ሳይሆንላቸው ቀርቷል። ያቀረቧቸው መረጃዎች እውነት አልባና አሳማኝነት ጎድሏቸዋል። የሚሊየን ዶላር ክምችትም አንድ ዳኛ መግዛትና ውሳኔውን የማስለወጥ አቅም እንደሌለው ማረጋገጫ ሰጥቷል። በዚህ ሰነድ ቀውስ ስልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሲለቁ ሸሪፍ የመጀመሪያው መሪ ግን አይደሉም። ከዓመት በፊት የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲግማንዱር ጉንላውግሰን ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።

እንደ ዱራን ታይምስ የዜና አውታር የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አዳም ጌሪ ከሆነ ግን ከሚስጥራዊ ሰነዱ የሙስናው ቅሌት ጀርባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መውረድ ምናልባትም የምዕራባውያንና ሌሎች አገራት እጅ አለበት። እንደፀሃፊው እምነት፤ ሰውየው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚና ደካማ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ረገድ አገራቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባራት በመከወን ረገድ ውጤታማ እንደነበሩ ይገልፃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፓኪስታን በመወከል ባህር ስንጠቃ ጉዞዋን ለምታቀላጥፈው መርከብ ዋነኛው ካፒቴን ናቸው። በተለይ በዲፕሎማሲው መሰክ ሰውየው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከቻይና ከኢራን ጋር ከኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ አጋርነት የመሰረቱት ጥሩ ወዳጅነት በተለይ «በአንድ መቀነቱ» የቻይና የንግድ ፖሊሲ ይሁንታ መቸራቸውና የቻይና ፓኪስታን የኢኮኖሚ ኮሪደር ተግባራዊ እንዲሆን በመፈቀዳቸው ቅናትና ስጋት ያደረባቸው አገራት አሉ። ፍላጎታቸውም ሁለቱንም አገራት የማዳከም ነው።

ምንም እንኳን የአገሪቱ የውስጥና የውጭ ፖለቲካል መዘውር በአንድ ሰው እጅና እጣ ፈንታ ላይ እንደሆነ ባይታመንም የሰውየው ቁልፍነት ግን አይካድም። ይህ እስከሆነም፤ ለሰውየው ከስልጣን መውረድ የአንዳንድ አገራት የምዕራባውያን እጅ እንዳለበት እሙን ነው። ጎረቤቷሞቹ ህንድና ፓኪስታን በካሽሚር ግዛት ሁሌም ቢሆን ስምምነት ኖራቸው አያውቅም። እናም የኒውዴሊ መንግስት ለሰውየው መውረድ አስተዋፆኦ አበርከቷል ተብሎ በመገናኛ ብዙሃኑ ከተገመቱ አገራት መካካል አንደኛው ሆኗል። ህንድ በአንፃሩ  በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች። የቢቢሲው ዘገባ፤ ኢያስ ካሃን፤ ከሆነ ደግም ምክንያቱ፤ ለዘመናት የዘለቀ የአገሪቱ የፖለቲካ ኡደትና የህዝብን ድምጽ የመወሰን መብት የመገደብ አካሄድ መሆኑን አትቷል።

የሰውየው ከስልጣን መውረድ መሰል ምክንያቶች መደርደር ቢቻልም፤ የሚስጥራዊ ሰነዱ ቅሌት ግን በቀጣዩ ዓመት አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዋዜማ ላይ ለምትገኘው ፓኪስታን ትልቅ ዱብ እዳ ነው። እንደ ኤኤፍ ፒ ዘገባ፤ አገሪቱ አሁን ላይ መንግስት አልባ ናት። እናም ከአገራዊው ምርጫው በፊት ሰውየውን በቶሎ መተካት ይቀድማል።ምንም እንኳን የሰውየው ምትክ በቀናት ውስጥ የሚካሄድ ቢሆንም፤ ከቀጣዩ ዓመት በፊት አገራዊ ምርጫ ማካሄዱ ግን አይታሰብም። ይልቅስ ሰውየውን ማን ሊተካው ይችላል የሚለው አሳሳቢ ነው።

ምንም እንኳን ሰውየው ከስልጣን ቢወርዱም የአገሪቱ ዋነኛ ፓርቲ የበላይ ተጠሪ ናቸው። ፓርቲያቸውም 342 መቀመጫ ካለው የአገሬው ፓርላማ 209 የሚሆነው መቀመጫ በበላይነት የተቆጣጠረ ነው። ይህ እንደመሆኑም የሰውየው ምትክ ሌላ የፓርቲው አባል እንደማይሆን እርግጥ ነው። ለሰውየው ምትክነት ወንድማቸው ሰሃባዝ ከፍተኛውን ቦታ ቢወስዱም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆን ተወዳዳሪያቸውን በማቅረብ የእድላቸውን መሞከራቸው ግን አይቀሬ ነው።

እንደ አልጀዚራ ዘገባ፤ የአገሪቱ ፓርላማ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምትከ ለመምረጥ ዛሬ ይሰበሰባል። እንደ ቪኦኤ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ምንም እንኳን ምርጫው ይካሄድ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው አገራቸውን መምራታቸውን ይቀጥላሉ።

ላለፉት ሃያ ዓመታት በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ያሳለፈውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገ ወጥ ገንዝብ ማከማቸታቸውንና በሙስና መዘፈቃቸውን በተደጋጋሚ ሲገልፅ የሚሰማው የአገሬው ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ኢምራን ከሃን በአንፃሩ በቀጣዩ የአገሬው ምርጫ ብርቱ ፉክክር በማድረግና በማሸነፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክቶ አገሪቱን በበላይነት እንደሚመራ ለሮይተርስ  ሲገልፅ ተሰምቷል። ባሳለፍነው ቅዳሜም በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬው ዜጎች በአገሪቱ ዋና ከተማ ኢስላማባድ ለኢምራን ከሃን ድጋፋቸውን ሲሰጡ ታይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻሪፍ ፓርቲ በሌላ ጎን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ኃላፊነታቸው ያከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ምርጫው አሸናፊ እንዲሆን እንደሚያግዘው ተማምኗል። የፓርቲው ተጠሪ የሆኑት ከሃዋጅ ሳድራፊክ፤ፓርቲያቸው በአገሪቱ የበላይ ተቋም የተላለፈውን ውሳኔ በፀጋ እንደሚያከብር፣ እንደሚቀበልና አባላትና ደጋፊዎቻቸውም ከአምፅ ይልቅ በተረጋጋ መልኩ ጉዳዩን እንደሚከታተሉት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

አንዳንዶች በአንፃሩ በአገሪቱ ውጥረት እንደሚከሰት እርግጠኛ ሆነዋል።ታዋቂው የአገሬው ዋን ቲቪ ጋዜጠኛ ራሂም ሻምሲ የዚህ  እሳቤ ተጋሪ ነው። እንደ ጋዜጠኛው እምነት በቀጣዩ ዓመት አገራዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ውጥረት መኖሩ አይቀሬ ነው።

ታምራት ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።