ኢትዮጵያ በውጭ መገናኛ ብዙሃን እይታ Featured

07 Aug 2017

በቱርኩ  ያፒ መርከዚ በኢትዮጵያ ውስጥ  ከሚገነባቸው የባቡር ሐዲድ ከፊል ገጽታ፤

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ስኬታማ ተግባራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በድረገጾቻቸው ለንባብ አብቅተዋል። በተለይም በኢኮኖሚው መስክ እየታየ ያለው ለውጥ፣ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማከናወን ላይ ያሉት ተግባራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን አቅጣጫ እንደያዙ ዘገባዎቹ የዳሰሷቸው እውነታዎች ናቸው። ባለፈው ሳምንት መልካም ገጽታዎችን አጉልተው ካስነበቡት መካከል የኢትዮጵያ የአየር መንገድ አዲሱ በረራ ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር መነገሩ፣ የቱርክ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክት የአፍሪካ «የታመነ የልማት አጋር» እየሆነ መምጣቱ፣ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝና የውጭ ንግድ መዳከም  ይገኙበታል፡፡

  የቱርክ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክት የአፍሪካ «የታመነ የልማት አጋር»

እየሆነ ነው

የቱርክ ግዙፉ የሕንፃ ግንባታ ኩባንያ ያፒ መርከዚ  በኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ውስጥ በ3 ቢሊዮን ዶላር ዘመናዊ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት እየገነባ ሲሆን ይህም በአፍሪካ «የታመነ የልማት አጋር» እንዲሆን እንዳደረገው አናዶሉ ኤጀንሲ የወሬ ምንጭ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ የመሠረተ ልማት አውታር እና የካላብጋን እና የአልጀርስ ባቡር መስመሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 2ሺህ600 ኪሎ ሜትር መስመር  እና ሌሎች አሥራ ሁለት የባቡር መስመሮች በተሳካ ሁኔታ በመገንባት ኩባንያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የፋይናንስ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሙራት ኦካል ለአናዶሉ እንዳሉት፤ የመጀመሪያ ሁለቱ የአፍሪካ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ አገራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ «ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ደረጃ ሊባል በሚችል ልኬት ተጠናቀዋል። እናም የእኛን የብቃትና የቱርክንም የቴክኖሎጂ ዕድገት ያሳየናል» ብለዋል፡፡ ኦካል አክለውም በቅርቡ በኢትዮጵያና ታንዛኒያ  የሚገነባው ደረጃውን የጠበቀ የባቡር ሀዲድ ለኩባንያው በአፍሪካ የመጀመሪያውና ትልቁ  ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

እ.አ.አ በ 2015 በ 1ነጥብ7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተጀመረው 3 ሺ 910 ኪሎ ሜትር አዋሽ-ኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት  ሰሜን እና ምሥራቅ ኢትዮጵያን በማገናኘት ወደ ጅቡቲ ወደብ በቀላሉ ለመድረስ እንደሚያግዝ ምንጩ ዘግቧል፡፡ ይህ የባቡር መስመር  ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ  ባለው የጎረቤት አገር ጋር ለማገናኘትና በተለይም ሸቀጦችን ለማጓጓዝ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ምንጩ አስነብቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የእድገትና የትራንስፎር ሜሽን እቅድን መሠረት በማድረግ የሀገሪቱን ውስጣዊና ውጫዊ መጓጓዣ እና የመንገድ ትራንስፖርት አቅም እያጠናከረ ነው፡፡ ምንጩ  እንደዘገበው አዋሽ እና ኮምቦልቻ  ብዛት ያላቸው ረዣዥም ድልድዮች እና ዋሻዎች የያዘው የመጀመሪያው ዙር ግንባታ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ ፕሮጀክቱ እንደታቀደው በ 2020 ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 12 የመንገድ ዋሻዎች፤ 51 ድልድዮች፤ 14 መሻገሪያዎች እና አንድ መተላለፊያ ይገነባል፡፡ «በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ 50 በመቶ ተጠናቅቋል፤ 83 ከመቶ የመጀመሪያው ዙር ተጠናቅቋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውና በሰዓት  ከ100 ኪሎሜትር በላይ ፍጥነት ያለው እንደሆነ በሙከራ መረጋገጡን ምንጩ ዘግቧል፡፡ በሙከራው ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መገኘታቸውን ዳይሬክተሩ አቶ ሙራት ኦካል  ተናግረዋል፡፡

ኦካል ጨምረው እንዳሉት፤  ሁለተኛው ደረጃ  ግንባታ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልገዋል። እናም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ያስተካክላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ሥራውን በተቀመጠለት ጊዜ እንደሚጨርሱ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ ውስጥ 7ሺ200 ሠራተኞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 4ሺ600 ኢትዮጵያውያን እና 2ሺ200 ቱርካውያን ናቸው፡፡ 400 ሠራተኞች ደግሞ የሌሎች አገሮች ተቀጣሪዎች ናቸው፡፡

ለአናዶሉ ኤጀንሲ በስልክ መረጃ የሰጡት ኢንጂነር ሀብታሙ በቀለ  «የባቡር ፕሮጀክቱ የተለየ ባህሪ አለው ለበርካታ ዓመታት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ መሠረተ ልማት ተቋራጮች ጋር ሰርቼያለሁ፤ የቱርክ ባለሙያዎችን ልዩ የሚያደርጋቸው ግን ክህሎታቸውን ለማካፈል  ፈቃደኞች ናቸው» ብለዋል። የኮምቦልቻ ነዋሪ የሆነው ሱሌይማም ሙሃመድ የባቡር መስመር ሥራው ለነዋሪው ተስፋ እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡ «የቱርክ ሠራተኞች ከአካባቢያችን ማህበረሰብ ጋር እንዴት እንደሚኖሩ እና እንደሚሰሩ ያውቃሉ፤ እኛም ተመሳሳይ ባህል አለን» ማለታቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

(ANADOLU AGENCY 2 August 2017)

 

የአየር መንገዱ አዲሱ በረራ ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጥራል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመዳረሻ አድማሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስፋፋ በመምጣት በቅርቡ በሰሜን ምዕራብ ናይጀሪያ የምትገኝ ካዱና ግዛት አዲስ የበረራ አገልግሎት ጀምሯል፡፡ የግዛቱ አስተዳደር የበረራው አገልግሎት መጀመሩ የግዛቱ የምጣኔ ሀብት መነቃቃት ይፈጥራል ማለታቸው ዘ ጋርድያን ድረገጽ አስነብቧል፡፡

     የካዱና ግዛት ለባህር ወደብ ቅርብ ያለመሆን ችግር በማያቋርጥ የዓለም አቀፍ በረራ እንደሚቀረፍ አስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ካዱና የሚደረገው የቀጥታ በረራ ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ የማቀላቀል አንድ እርምጃ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

    የካዱና ግዛት በመላክና ማስገባት ንግድ ሥራ የአየር መንገዱ ካርጎ በመጠቀም በቀላሉ አገልግሎቱን የሚያገኝ  ሲሆን፣ መደበኛ በረራ እንዲያደርግ አየር መንገዱን እንደሚደግፉትም የግዛቱ አስተዳዳሪ ናስር ኢል ሩፋይ ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተዳደሩ አገላለጽ  የተገኘው መልካም አጋጣሚ የካዱና ግዛት የልማትና እድገት ስትራቴጂ በመደገፍ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ገቢ ለማሳደግና የነዋሪዎቹን ኢኮኖሚ ለማጠናከር የሚረዳ ነው፡፡

     የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሦስት ቀን በግዛቱ መደበኛ በረራ የሚያደርግ ሲሆን፣ የካዱና አየር ማረፊያ የአቡጃ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ለእድሳት በተዘጋበት ጊዜም ቢሆን ምቹ ማረፊያ በመሆን በማገልገሉ አየር መንገዱ የሚተማመንበት መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞ ቁጥጥርና ሽያጭ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ  ፍሬሕይወት መኮንን  መናገራቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

(The Guardian 2 August 2017)

  

  የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ የውጭ ንግድን አዳክሟል

የዓለም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ በታቀደው መሠረት ግቡን እንዳይመታ ማድረጉ ዢንዋ ድረገጽ አስታወቀ፡፡ በበጀት ዓመቱ የሀገሪቱ የውጭ ንግድ አፈጻጸም 61 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ተገልጿል። የ4 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር  ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም የተገኘው2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው።፡፡

የውጭ ንግድ ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም በበጀት ዓመቱ በነበረው የማምረቻ ፋብሪካዎች አስፈላጊ ግብአቶች አቅርቦት እጥረት፣ እንዲሁም የሕገ ወጥ ንግድና መሰል ችግሮች የውጭ ንግዱ እንዲዳከም ማድረጉን የንግድ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ታደሰን ዋቢ በማድረግ ዘገባው ገልጿል፡፡

በንግዱ ላይ የግብርና ምርት 2 ነጥብ 18 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲኖረው የፋብሪካ ምርቶች 413 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የማዕድን ዘርፍ 230 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ማስገኘታቸውን ድረገጹ አስነብቧል፡፡

(Xinhua 2017-07-31)

በሞኒተሪንግ ክፍል

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።