ልዕል ኃያሏ አገር ሕገደንብ ለማዘጋጀት ለምን ሰነፈች? Featured

10 Oct 2017

በአሜሪካ የመሣሪያ ቁጥጥር ህገ ደንብ አነጋጋሪ መሆኑን ቀጥሏል፤

 

የአሜሪካ ሕገመንግሥት የነፃነት ቀንዲል ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደአርአያ ይነሣል፤ ይወደሳል፡፡ እ..1789 በወጣው በዚህ ሕገ መንግሥት የመብቶች ድንጋጌ ሁለተኛው ማሻሻያም ሰዎች መሣሪያ የማግኘትና የመያዝ መብት እንዳላቸው ማረጋገጫን ይሰጣል። በዚህም ምክንያት በልዕል ኃያል አገር የነፍስወከፍ ጦር መሣሪያ ገበያ (የጠመንጃና ሽጉጥ ገበያ) ለሁሉም ክፍት ነው። መሣሪያ የሚሸጡም ሆነ የሚገዙ ሰዎችን ቁጥርም በየጊዜው የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም አገሪቱ ከ 3 ሚሊዮን በላይ የነፍስወከፍ ጦር መሣሪያ አላት። ይህም አንድ ግለሰብ ከአንድ በላይ መሣሪያ አለው እንደማለት ነው። የመሣሪያ ንግዱ በሚጦፍባት በዚህች አገር ግን የጦር መሣሪያ ሽያጭ መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ የለም። በዚህም ምክንያት በየጊዜው በመሣሪያ የታገዘ ሁከትና ጥቃት ይፈፀማል። በክስተቱም ዜጎች ይሞታሉ። በጅምላ ይጨፈጨፋሉ። ብዙዎች ያለቅሳሉ። ውስጣቸውም ይደማል።

በአገሪቱ ድንገተኛ የጦር የመሣሪያ ጥቃት ሲፈፀም የመሣሪያ ባለቤትነት ሕግ ደንብ ሁሌም ቢሆን ወቅታዊ መነጋጋሪ ይሆናል። ወሬውም ለአንድና ሁለት ሳምንታት ከተወራ በኋላ የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል። ተቃዋሚዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ጋዜጠኞችም ወደ ሌላ ወሬ ይሸጋገራሉ።

የሕይወት ጥፋትና ሁከት ረገድ አሜሪካ በዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ ትይዛለች። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጦር መሣሪያ አማካይነት የሚፈጸም ሁከትና ጥቃት ወረርሺኝ ሆኗል። እንደ ዘጋርዲያን የሰሞኑ ዘገባም በአገሪቱ በ 1 735 ቀናት ውስጥ 1516 የጅምላ ተኩስ ተፈፅሟል።

በቅርቡ ታሪክ ስናስታውስ እንኳን በላስ ቬጋስ የሙዚቃ ኮንሰርት በታደሙ ሰዎች ላይ ስቴፈን ፓዶክ የተባለ የ64 ዓመት ታጣቂ በተፈፀመ ጥቃት ከ59 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ቁማርተኛና የቀድሞው የሂሳብ አያያዝ ባለሙያ እንደሆነ በተነገረለት ግለሰብ የተፈፀመው ጥቃትም በኦርላንዶ 49 ሰዎች ከሞቱበትና በወቅቱ የከፋ ከተባለው አደጋ ልቆ በአሜሪካ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከተፈጸሙት ሁሉ በላይ ደም አፋሳሽ ሆኗል።

አገሪቱ ምንም ልዕል ኃያል ብትሆንም ለመሰል ጥቃቶችንም እልባት መስጠት አልቻለችም። የሰላማዊ ሰዎች እልቂት ለመቆጣጠር የሚያስችልና መሣሪያ የመያዝ (የመግዛት) እንዲሁም በባለቤትነት ነፃነት ላይ ገደብ የሚጥል ጠበቅ ያለ ፖሊሲና ሕግ የማውጣት አቅምም አጥታለች።

በእርግጥ በጦር መሣሪያ አማካይነት የሚፈጸም ሁከትና ጥቃት አሜሪካ ውስጥ ብቻ የሚፈፀም አይደለም። በሌሎች አገራትም ይከሰታል። ይሁንና ሌሎች አገራት መሰል ጥቃት ሲያስተናግዱም ሆነ ከማስተናገዳቸው ቀድመው በጦር መሣሪያ ባለቤትነት ላይ ጠንካራ ሕግ አውጥተዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆና የምትጠቀሰው ደገሞ አውስትራሊያ ናት።

አውስትራሊያ እ..1996 በቱሪስቶች መንደር ለ 35 ሰዎች ሞት እንዲሁም ለ 28 በላይ ሰዎች ጉዳት ምክንያት የሆነውን የጅምላ ጭፍጨፋ ተከትሎ በመሣሪያ ቁጥርና ባለቤትነት ላይ ጠበቅ ያለ ሕግና ፖሊሲ አርቅቃለች። በዚህም ተጨባጭ ለውጥ አምጥታለች። በርካታ አገራትም የአውስትራሊያን ፈለግ በመከተል የጦር መሣሪያ የመያዝ (የመግዛት) መብትን የሚያጠናክሩ ሕጐችን አሻሽለዋል። አውስትራሊያ ያመጣችውን ለውጥ ለማምጣት አሜሪካ ብዙም ወጪና ድካም አይጠይቃትም። ዋናው የፖሊሲ ምርጫና ጠንካራ ሕግ የማርቀቅ ጉዳይ ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአገራቸው ውስጥ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን በጦር መሣሪያዎች አማካኝነት የሚፈፀመውን የሰላማዊ ሰዎች እልቂት የመቆጣጠር ድክመት መወገድ እንዳለበት ሲወተውቱ ቆይተዋል። «የጦር መሣሪያ ሕግ ሊወጣና መሣሪያ በመያዝና በባለቤትነት ነፃነት ላይ ገደብ ሊጣል ይገባል» የሚል አቋማቸው ለማሳመን እንባ አውጥተው እስከመማፀን ብዙ ጥረዋል።

የመሣሪያ ሻጮች የኋላ ታሪክ እንዲመረመር፣ ግዛቶች በቤተሰብ ውስጥ ሁከትን በመፍጠርና በአዕምሮ ሕመም ምክንያት የጦር መሣሪያ እንዳይገዙ ዕገዳ ስለተደረገባቸው ሰዎች ኢንፎርሜሽን እንዲያስተላልፉ፣ በእነዚህ አቅጣጫዎች የሚደረገውን ቁጥጥር ለማቀላጠፍ የአሜሪካ ምርመራ ፌዴራል ቢሮ (ኤፍቢአይ) በሠራተኞች ይበልጥ እንዲደራጅ ጠይቀዋል።

የአገሬው ኮንግረስ ግን ለዚህ የፕሬዚዳንቱ ተማፅኖና ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ዝምታ ነው። በዚህ የኮንግረሱ ዝምታ አሁንም ድረስ እንደ ቬጋሱ ዓይነት አሰቃቂ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ቀጥለዋል። የቬጋሱ ጥቃት ግን ከሁሉ በላይ በአሜሪካ የጦር መሣሪያ አያያዝና ባለቤትነት ሕግ ላይ ጫና ክርክርና መረር ያለ ወቀሳን ይዞ ብቅ ብሏል።

በተለይም ልዕል ኃያሏ አገር መሰል የሰላማዊ ሰዎች እልቂት ለመቆጣጠር የሚያስችልና መሣሪያ የመያዝ (የመግዛት) እንዲሁ በባለቤትነት ነፃነት ላይ ገደብ የሚጥል ጠበቅ ያለ ፖሊሲና ሕግ የማውጣት አቅም ለምን አጣች? የሚል ጥያቄ ተነስቷል። በዚህ ረገድ ሃሳባቸውን የሚያጋሩ የፖለቲካ ምሁራንና የመገናኛ ብዙኃን ጸሐፍት ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሉትን አጋርተዋል።

በተለይ እንደ ሲኤን ኤን የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሐፊውው ክሪስ ሲሊዛ ትንታኔ፤ በአሜሪካ ከአስር ሰዎች አራቱ በቤታቸው ጦር መሣሪያ አለ።74 በመቶ የአገሬው ዜጎችም መሣሪያ በቤታቸው በመኖሩ ብቻ ነፃነት ይሰማቸዋል። መሠረታዊ መብትና ነፃነታቸው መሆኑንም ያምናሉ። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የአገሬው ዜጎች መሣሪያ የመያዛቸውን ዋነኛ ምክንያት ሲያስረዱ ለአደን ግልጋሎት የሚል መልስ ይሰጡ እንደነበር የሚያስታውሰው ፀሐፊው፤ አሁን ላይ ዜጎች መሣሪያ የሚይዙበት ዋነኛ ምክንያት ግን ስጋት መሆኑን ያስረዳል።

እንደ ፀሐፊው ገለፃ፤ ከሕዝቡ በተጓዳኝ የአገሬው ፖለቲከኞች በጦር መሣሪያ ላይ ያላቸው አመለካከት ለየቅል ነው። ከሦስቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ብቻ ጦር መሣሪያ የአገሪቱ ዋነኛ ችግር መሆኑን ያምናል። ጦር መሣሪያን በቀላሉ ማግኘት መቻልም የጅምላ ጭፍጨፋ መነሾ ሊሆን እንደማይችል ያስባሉ። ይህም አገሪቱ የጦር መሣሪያ ሕገ ደንቡን እንዳትተገብር ማነቆ ሆኖባታል።

ይህ ብቻ ግን አይደለም። በጦር መሣሪያ ላይ የመንግሥት አቋም ምን መሆን አለበት በሚለው እሳቤ ላይ በእጅጉ የተቃረነ አመላካከት ይስተዋላል። በመሣሪያ ቁጥጥር ደጋፊዎች ሕግ ያስፈልገዋል በሚል የፍትህ ያለ ሲሉ ተቃዋሚዎች በአንፃሩ ሰዎች ሕግ ደንብ ማውጣት መፍትሄ እንደማይሆን እምነት አላቸው።

በተለይ የአገሬው ፖለቲከኞቹ በሕጉ ላይ ያላቸውን አቋም ግራና ቀኝ ነው። ዲሞክራቶች የመሣሪያ ባለቤትነት ቁጥጥሩ መጠናከር እንዳለበትና ለዚህም ሕገ ደንብ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ እምነት አላቸው። ሪፐብሊካኑ በአንፃሩ በተቃራኒ አቅጣጫ ቆመዋል። የፖለቲካ ምሁራኑ እንደሚተቻቸው ከሆነም ፤ሪፐብሊካኑ ክክስተቱ በኋላ ኀዘናቸውን መግለፅና መፀለይን ምርጫቸው ከማድረግ በዘለለ ስለ ሕጉ ተግባራዊነት ቃል አይተነፍሱም።

ሌላኛው የሲ ኤን ኤን ፀሐፊ ስቴቨን ኮሊንሰን አሜሪካ ሕጉን ለተግባራዊ ለማድረግ የሰነፈችበት ምክንያት አሁንም ቢሆን የሕጉ ተግባራዊነት አጠራጣሪ መሆኑን ሲያስረዳ እንደሚገልፀው፤ ሪፐብሊካን በነጩ ቤተ መንግሥትና በኮንግረሱ ያለውን የሥልጣን ኃይል ጠቅልለውታል። ይህ እንደመሆኑም የዲሞክራቶቹ ፍላጎት ተፈፃሚነት ዝቅተኛ ነው» ይላል።

እንደ ፀሐፊው ሀተታም፤«ናሽናል ራይፍል አሶሲየሽን» የሚል ስም የሚታወቀው የጦር መሣሪያ ሻጮች ማህበርም በሪፐብሊካኑ የፖለቲካ ምህዋር ላይ ያለው ሚና ከባድ ነው። ይህ ማህበር ደግሞ ለሕጉ ተፈፃሚነት በተፃራሪነት የቆመ ነው። ከባራክ ኦባማ በተሻለ ዶናልድ ትራምፕ ሕገ ደንቡን ለማዘጋጀት ዛሬም ድረስ ዳተኛ የሆኑትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ማረጋገጥ አይከብድም።

ቮክስ ኒውስ የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሐፊ ጀርማን ሎፔዝ እንደሚገልፀው፤ አሜሪካ ከሌሎች አገራት ሲነፃፀር የመሣሪያ ቁጥርም ሆነ በጦር መሣሪያ አማካኝነት በሚፈፀም ቀውስ የሚስተካከላት የለም። በአንድ አገር ብዙ መሣሪያ አለ ማለት ብዙ ቀውስና ሞት አለ እንደማለት ነው። እናም የመጀመሪያ ተግባር መሣሪያዎች መቀነስና ዜጎችን መሣሪያ በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የመሣሪያ ሕግ ማርቀቅ ይገባል። ይሁንና የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ይህን ማድረግ አልቻሉም። ይህ ቢያደርጉ የሰሞኑን የቬጋስ የጅምላ የተኩስ ጥቃት ማስቆም ይቻላቸው እንደነበር መረዳት ትክክለኛነት ነው።

መሰል ቀውስ ዳግም እንዳይከሰት ለጉዳዩ ፖለቲካዊ አንድምታን መስጠት ይገባል የሚል አቋሙን የሚያስረዳው ፀሐፊው፤ ፖለቲካ ማለት በሌላ ገለጻ የሕግ ተፈፃሚነት ነው፤ የጅምላ የጦር መሣሪያ ጥቃት ማለት አንድ ሁነት ነው፤ የተጠናከረ ሕግና ፖሊሲ በእጅጉ ሊቀንሰው የሚችል ነው፤ መሰል ቀውሶች እልባት የመስጠት የመንግሥትና የፖለቲካ ሥርዓቱ ኃላፊት ነው» ይላል።

እንደ ፀሐፊው ገለፃ፤ መንግሥት ግለሰቦችና ተቋማት በግል መፍታት ያቃታቸውን ችግሮች የሚፈታ አካል ነው። አንድ እስከፊ ክስትት ሲፈፀም መንግሥት አፋጣኝ ውሳኔ በመውሰድ ዳግም እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በመሆኑም ይህን ችግር ከወዲሁ አልባት ለመስጠት የፖለቲካ አስተዳደሩ መሰል ቀውስን የማስወገድ ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል። ፖለቲከኞችም በምርጫ ቅስቅሳው ወቅት መሰል ችግሮችን ለማስቆም የገቡትን ቃል ሊያክብሩ ይገባል። ምክንያትም የመረጥናቸው ቃል ስለገቡልን ነው።

«እናም የአገሬው ሕዝብ ጉዳዩን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊሰጠው ይገባል፤ ይህን እስካላደረገ ለውጥ ማምጣት አይችልም። ምክንያቱም እስካሁን እየተፈፀሙ የሚገኙ ጥቃቶች በሙሉ የመንግሥት የቸልተኝነት ውጤት ናቸው» በሚል ሃሳቡን ይጠቀልላል።ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን «በሕጉ ላይ መነጋገር ካስፈለገን የምንነጋገር በት ጊዜ አሁን አይደለም» የሚል አቋም ይዘዋል።

አንዳንዶች ግን በቂና በርካታ መሣሪያ ባለበት አገር ጠንካራ ሕግ ማርቀቅ ከተቻለ ቀውሱን ማስቆም ይቻላል ሲሉ ገሚሶቹ፤ የሕግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅም መጥፎ ሰዎች መጥፎ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ ይናገራል። እንደእሳቤው ደጋፊዎች እምነትም፤ የመሣሪያ ባለቤትነት ብቻውን ችግር አይደለም። ዋናው ዜጎች መሣሪያውን ለምን ግልጋሎት እንደፈለጉት ማወቅ ነው። እናም መንግሥት ማጤን ያለበት መሣሪያው ላይ ሳይሆን ሰዎች በመሣሪያውን በክፉ እሳቤ ለመጠቀም የሚያነሳሳቸው ተዋጽኦ ላይ ነው። አገሪቱ መስራት ያለባትም ይህን ነው የሚል አቋም ይዘዋል።

የለም የለም መሰል ጥቃቶች የሚፈፀሙት ከመሣሪያው ጀርባ የአደንዛዥ እጾች ቁጥጥር ላይ ያለመስሯቷ ውጤት ነው፤ ብዙዎች መሣሪያ በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ የሚገድብ ጠንካራ ሕገ ማዕቀፍ መኖሩ መልካም ቢሆንም መሰል ጥቃቱን ለማስቆም አገሪቱ አደንዛዥ እጾችን የመቆጣጠር ትግበራን ዳግም ማጤን ይገባታል ሲሉ የሚወተውቱም አልጠፉም። አሁን ላይ የመሣሪያ ቀውስ ለአሜሪካ ከባድ ራስ ምታት ሆኗል «በዚህ አጋጣሚ መነሾ አንድ እርምጃ መሄድ ካልተቻለ ለአገሪቱ የሚቀራት ጠባሳ ጎልቶ የሚታይ ይሆናል» የሚሉት ግን ለውጥን ይማፀናሉ።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።