ከሃራሬ የተነሳው የለውጥ አብዮት በአፍሪካ

05 Dec 2017

ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሐራሬው አብዮት አስግቷቸዋል፤

 

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ የሚታየው የህዝብን እውቅና አግኝተው ወይም በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ሳይሆን በመፈንቅለ መንግስት፤ በጦርነት ሀይል ስልጣንን በመቆጣጠር አሊያም በዘር ውርስ የስልጣን ርክክብ በማድረግ ነው።

በዚህ ሂደት ወደ ስልጣን የመጡ መሪዎችም አንዴ የመሪነትን ሃይል ከጨበጡ መንበረ ስልጣናቸውን ያደላድሉና አትንኩኝ ባይ ይሆናሉ። ከስልጣን ከመነሳት ሞትን ይመርጣሉ። የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘም ሲሉም ህገ መንግስቱን ከማሻሻል ጀምሮ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።

እነርሱን ከሚመስላቸው ውጭ ለሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅትም ሆነ አገርን ለመምራት አቅምም ሆነ ብቃቱ ላላቸው ግለሰቦች በማንኛውም መንገድ ቢሆን ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኞች አይሆኑም። በዚህም ምክንያት ከህዝባቸው ጋር አይጥ እና ድመት ሆነው ይኖራሉ። ተቃውም ቢበረታባቸውም እንኳ ዙፋናቸውን ለማስረከብ ፈቃደኛ አይሆኑም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የአንዳንድ አገራት ህዝቦች የማይደፈረውን በመድፈር የአንጋፋ መሪዎቻቸውን እድሜ ለማሳጠር ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል። በዚህ ተግባራቸውም ለመሪዎቹ የመውጫ በር ያሳዩ አገራትም ታይተዋል።

ያለፉትን ሶስት ዓመታት ብንመለከት እንኳን አንጋፋዎቹ መሪዎች በሚመሩት ህዝብ ጠንካራ ተቃውሞ ተፍረክርከው የሚወዱትን ስልጣን ሳይወዱ በግድ ለመልቀቅ ሲገደዱ አይተናል። ከእነዚህ መሪዎች ቀዳሚው የቡርኪና ፋሶው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓውሬ ናቸው። ብሌስ ኮምፓወሬ በስልጣን ለመቆየት ህገ መንግስታቸውን ለማሻሻል ሲዳዱ በህዝባቸው መሪር ተቃውሞ ለ 27 ዓመታት ከተቀመጡበት ዙፋን እ ኤ አ በ2014 ተነስተዋል፡፡

22 ዓመታት ጋምቢያን የመሩት ያህያ ጃሜ ባሳለፍነው ዓመት በምርጫ ተሸንፈውም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይሁንና በክፍለ አህጉርና አህጉር አቀፍ ደረጃ በተደረገባቸው ጫና የሚወዱትን ስልጣን እንዲለቁ ተገደው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲኮበልሉ ተደርገዋል። የአንጐላው ፕሬዚዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስም እንዲሁ ለአራት አስርት ዓመታት ከተቆናጠጡበት ፕሬዚዳንታዊ ስልጣን በያዝነው ዓመት በግፊት እንካችሁ ብለዋል።።

የቅርቡን እንኳን ብንወሰድ የዚምባቤዌን አብዮት ማንሳት እንችላለን። «ከአምላክ በቀር ስልጣኔን የሚወስድ አይኖርም በሚል እስከ ህልፈተ ሞታቸው በስልጣን ለመቆየት ያስቡ የነበሩት የ93 ዓመቱ አንጋፋ መሪ ሙጋቤ፤ በወታደራዊ ሃይል በተደረገባቸው ጫና ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አስረክበዋል።

በመሰል የህዝባቸው ጠንካራ ተቃውሞም ይሁን በምርጫ ስልጣን ያስረከቡ መሪዎች የመኖራቸውን ያህል አሁንም ለረጅም ዓመታት የተቀመጡበትን ዙፋን ማስረከብ የማይፈልጉና የመሪነት ስልጣናቸውን የሙጥኝ ብለው የተቀመጡ አንጋፋ መሪዎችም አሉ።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉዌማ እ ኤ አ ከ1979 ጀምሮ ዛሬም ድረስ በስልጣን ላይ ናቸው። የካሜሮኑ አቻቻው ፖል ቢያም ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር ማስተዳደር ከጀመሩ አራት አስርት ዓመታት ለመድፈን ተቃርበዋል። ሌላኛው የኮንጎ ብራዛቪል መሪ ዴኒስ ሳሱ ንጉዌሶ በመንበረ ስልጣናቸው ከተቀመጡ 33 ዓመት ተቆጥረዋል።

ከእነዚህ መሪዎች ቀጥሎ ረጅም ዓመታት በስልጣን በመቀመጥ ስማቸው ከሚጠቀሱ መሪዎች አንዱ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ናቸው። ሙሴቬኒ እኤአ በ1986 በመፈንቅለ መግስት ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት መርተዋል።ፕሬዚዳንቱ በእነዚህ ዓመታት መንበረ ስልጣናቸውን አላስደፈሩም። አገራቸው ያካሄደቻቸው አምስት ምርጫዎች ውጤትም የእሳቸውን አሸናፊነት ከማብሰር ይልቅ የተለየ ነገር ይዘው አልመጡም።

ሙሴቬኒ ስልጣን ስለመልቀቅ አስበው አያውቁም። ፍላጎቱም የላቸውም። ይልቅስ በቀጣዩ የአገራቸው ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ መሳተፍ ይፈልጋሉ። እርሳቸው ስልጣናቸውን ማራዘም ይፈልጉ እንጂ እንደ ቀደሙት ጊዜያት አሁን ፍላጎታቸውን በቀላሉ ማሳካት የሚሆንላቸው ግን አይመስልም። የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የአገራቸው ህገ መንግስት ነው።

የዩጋንዳ ህገ መንግሥት አንቀፅ 102 አንድ ሰው ፕሬዚዳንት ለመሆን ብቁ ነው የሚያሰኘውን የእድሜ ጣሪያ ገደብ በግልፅ አስቀምጧል። በህገ መንግሥቱ መሰረትም ማንኛውም ሰው አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ለማስተዳደር ብቁ የሚሆነው እድሜው ከ 35 ዓመት በላይ እና ከ75 ዓመት በታች ሲሆን ብቻ ነው።

ሙሴቬኒ አሁን 73 ዓመታቸው ነው። ዩጋንዳም ቀጣዩን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እ..አ በ2021 ታካሂዳለች። ያኔ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት 76 ዓመት ይሆናቸዋል። በዚህ ስሌት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን መቆየት የሚችሉት ሙሴቬኒ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ይቸገራሉ። ይህ እንዳይሆን ከተፈለገና በምርጫው እንዲወዳደሩ ለማድረግ ታዲያ የአገሪቱን ህገ መንግሥት መለወጥ የግድ ይላል። ሙሴቪኒ ስልጣናቸውን ለማራዘም ያላቸውን ፍላጎት እውን ለማድረግ እድሜን በሚመለከት በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ህገ ደንብ ለማሻሻል ሲንደረደሩ ቆይተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ሂደት ላይ እያሉ ነበር ከወደ ሃራሬ ያልተጠበቀ የለውጥ አውሎ ነፋስ የተከሰተው። ይህ የረጅም ጊዜ የስልጣን አጋርና አቻቸውን ሮበርት ሙጋቤን ዙፋን የነቀነቀው የለውጥ አውሎ ንፋስ ታዲያ ለሙሴቬኒ ሰላም የሰጠ አይመስልም። አውሎ ንፋሱ ለሙሴቬኒ ብቻም ሳይሆን በመግቢያችን ለጠቀስናቸው ለሌሎች አንጋፋ መሪዎችም የማንቂያ ደውል ይሆናል። ከሁሉም በላይ ግን ሙሴቬኒን ያስደነገጠ ሳይሆን አልቀረም።

እንደ የሰሞኑ የሮይተርስ ዘገባ፤ በሃራሬ የተነሳው የለውጥ ነፋስ ከማንም በላይ አንጋፋዎቹን መሪዎች ያስጨንቃል። በተለይም ለካምፓላው መንግስት አስደንጋጭ የሆነ ይመስላል። የፕሬዚዳንቱ የሰሞኑ ተግባር ደግሞ ይህን እንደሚያስመሰክር ዘገባው ያትታል።

ዘገባው ፕሬዚዳንቱ «የኡጋንዳ ኢኮኖሚ እየተሻሻለ ነው፤ የአገሪቱ መንግስትም፤ ለወታደራዊ ሃይሉ ለመንግስት ሰራተኛው ለጤና ባለሙያዎች ለመምህራን የደሞዝ ማሻሻያ ያደርጋል»ሲሉ በቲውተር ገጻቸው ላይ መልዕክት ማስተላለፋቸውን በዋቢነት ይጠቅሳል።

ዘገባው እንዳመለከተው ይህ የፕሬዚዳንቱ ተግባር 37 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርባት አገር የተለያየ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል። ተግባሩን በቀናነት የተመለከቱት ጥቂቶች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ውሳኔ የደረሱት ስልጣናቸውን ለማቆየት ካላቸው ፍላጎት የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት በሃራሬ የተነሳው የለውጥ አብዮት ካምፓላ እንዳይደርስ በመስጋት ነው ይላሉ።

ፐሬዚዳንቱ ለአገሪቱ ሰራተኞች ደሞዝ በማሻሻል ብቻ አለመወሰናቸውን የሚናገሩም አሉ። በሜልና ዘጋርዲያን የዜና አውታር ላይ አስተያየቷን ያሰፈረችው ኢቴል ሻኪራ «ሙሴቬኒ ደሞዝ ማሻሻያ ብቻም ሳይሆን የአንዳንድ የካቢኔ አባላት ለውጥም አድርገዋል፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን የማሸጋሸግ ተግባርም ፈፅመዋል» ትላለች።

በፕሬዚዳንቱ ወገን የተሰለፉ አካላት በአንፃሩ የወታደራዊ አመራሩ ሽግሸግ የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ለመተካት የተካሄደ እንጂ ሌላ ስጋትን ተከትሎ የተፈፀመ እንዳልሆነ በማስረዳት ይሟገታሉ። ለስራተኞች የተደረገው የደሞዝ ማሻሻያም ቢሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ አስደማሚ የተባለ እምርታ ማስመዝገቡን ተክትሎ የተወሰደ እርምጃ መሆኑ ይታወቅ» እያሉ ናቸው፡፡

አሶሼየትድ ፕሬስ በበኩሉ ሙሴቬኒ በወታደሩ ሃይል ላይ ማተኮራቸው ታቅዶበት የተከወነ መሆኑን ያትታል። እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ሰውየው ስልጣን የያዙት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ነው። እናም የወታደር አቅም ምን ማለት እንደሆነ እስከ ምን እንደሚጓዝ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከወታደራዊ ሃይሉ ድጋፍ ውጪ በስልጣን መቆየት እንደሚቸግራቸው አይጠፋቸውም።

እንደ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ፤ፕሬዚዳንቱ ምትክ የሚሉት የላቸውም። ምትክ ብለው ሲናገሩለት የሚደመጥም የለም። ምትክ ብለው ማስቀመጥ አይወዱም። ፓርቲያቸውም ቢሆን ድንገተኛ ለውጥ ቢመጣና አፋጣኝ ምትክ ቢፈለግ እንኳ ከመዋከብ ይልቅ አፋጣኝ መልስ የመስጠት አቅም ሆነ አደረጃጃት የለውም።

ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር በሙሴቬኒ የስልጣን ዘመን ይህ ነው የሚባል የተጋነነ ተቃውሞና ሁከት ደርሶባት አያውቅም። ይሁንና አሁን ነገሮች እየተለወጡ ነው። በተለይ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን እድሜ ገደብ ለማንሳት የተደረገው ሂደት ብዙዎችን አስኮርፏል። እናም በአገሪቱ ህዝብ ተቃውሞና ነውጥ መታየት የጸጥታ አካላትም አፀፋውን መመለስ ጀምረዋል።

በሃራሬ የተነሳው የለውጥ አውሎ ንፋስ ከኡጋንዳ ተሻግሮ በሌሎች አገራት አንጋፋ መሪዎች ላይ ጭንቀት ማሳደርም ጀምሯል። አንጋፋዎቹ ስልጣን ወዳድ መሪዎች በሚያስተዳድሯቸው አገራት የሚኖሩ ህዝቦችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንፃሩ የልብ ልብ አግኝተዋል። እናም የአንጎላና የዙምባብዌን አንጋፋ መሪዎች የተካው አይነት የለውጥ አብዮት ወደ ሌሎች አፍሪካ አገራትም እንደሚደርስ አትጠራጠሩ የሚሉ ተበራክተዋል።

አገራቸውን ማስተዳደር ከጀመሩ አራት አስርት ዓመታት ያስቆጠሩት የካሜሩኑ ፖል ቢያ ደግሞ ይህ ስጋት ከተደቀነባቸው አገራት መሪዎች አንዱ ናቸው። የካሜሮን ህዝብ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ፍራንኪ ኢሲ እንደሚገልፀው፤መሪዎች ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ በማድረግ ምትክ እንዲያገኙ መወሰን ይኖርባቸዋል፤ይህ ካልሆነ የተወሰነ ጊዜያትን ቢወስድም በስተመጨረሻ የአገራቸው ህዝብ ራሱ የመውጫ መንገድ ያሳያቸዋል» ሲል ተደምጧል።

የቶጎ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ብርጊቲ አጃማድቡ ጆንሰን በሃራሬ የተነሳው የለውጥ አውሎ ንፋስ ቶጎ ሎሜ እንዲደርስ ፍላጎት አለው። ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስልጣንን የማስተላለፍ ሂደት በዙምባብዌ ህዝብ ዘንድ ደስታ እንደፈጠረ ሁሉ ቶጎአዊያንም በመዲናቸው ዋና ዋና ጎዳናዎች ደስታቸውን ሲገልፁ መመልከት ይፈልጋል።ይህ እንደሚሆንም ተስፋ አለው።

 

ታምራት ተስፋዬ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።