በእስራኤልና ፍልስጤም ላይ ጥቁር ጥላን ያጠላው የትራምፕ ውሳኔ Featured

06 Dec 2017

ከግራ ወደ ቀኝ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢንጃሚን ኔታነያሁ፤

 

እስራኤል እንደ አገር ከቆመች ዛሬ ልክ 69ኛ ዓመት ሆናት በራቀው ዘመን አይሁዳውያን በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች ተበትነው ይኖሩ ነበር፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ 40 ሺህ አይሁዶች በዛን ጊዜዋ ፍልስጤም እንዲሠፍሩ ተደረገ፡፡ በተለያዩ ጊዜዎችም የሠፋሪዎቹ ቁጥር እያደገ መጣ፡፡ በተለይም በ2ኛው የዓለም ጦርነት ሂደት በአይሁዶች ላይ ቁምስቅልና መከራቸው መብዛቱ የራሳቸውን አገር የማበጀት አስፈላጊነቱን አጐላው፡፡ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ የአይሁዳውያኑ ቁጥር ከአጠቃላይ የፍልስጤም ምድር ነዋሪዎች 33 በመቶ ደረሰ፡፡ ከጦርነቱ ሁለት ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ በአይሁዶችና በፍልስጤማውያን አረቦች መካከል ከጊዜ ወደጊዜ እያየለ የመጣውን ግጭት ለማስወገድ የዛኔዋ ፍልስጤም በአይሁዶችና በአረቦች ይዞታነት ለሁለት እንድትከፈል ወሰነ፡፡ ከወራት በኋላ ነፃ የእስራኤል መንግስት ታወጀ፡፡ ይሄ ከሆነ 69ኛ ዓመታት ተቆጠሩ።

የእስራኤል ነፃ መንግስትነት ያስቆጣቸው እንደ ግብፅ፣ ሶሪያ፣ትራንስዮርዳኖስና ኢራቅ በማግስቱ ከእስራኤል ጋር ወደ መዋጋቱ ገቡ፡፡ በዚህ ጦርነት አረቦቹ ተሸነፉ፡፡ ከዚያ ሁለት አስር ዓመታት በኋላ በአረቦችና በእስራኤል መካከል ሌላኛው ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ የእስራኤልና የአረቦች ጦርነት የሚባሉት ጦርነቶችን ከተካሄዱ 44 ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡ ከእስራኤልና አረቦች ተደጋጋሚ ጦርነቶች በኋላ ፍልስጤማውያን ከነፃ መንግስትነት እንደራቁና ለዚህም እንደጣሩና እንዳለሙ ይኖራሉ፡፡መሬት ለሰላም የተሰኘው የሰላም ስምምነት ፍቱን መፍትሄ ነው ተብሎ ተስፋ ተጣለበት፡፡ የስምምነቱ ፈራሚ የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ራቢን የዚያን ጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው ሺሞን ፔሬዝና የፍልስጤማውያኑ የነፃነት መሪ ያሲር አራፋት በኦስሎው ስምምነት መልካም አደረጋችሁ ተብለው የኖቤል የሰላም ሸልማትን ተቀበሉ፡፡ ስምምነቱ ስራ ላይ ሳይውል ይስሃቅ ራቢን ተገደሉ።

የፍልስጤማውያኑ መሪ ያሲር አራፋትም የናፈቋትን ነፃይቱን ፍልስጤም ሳያዩና ሳይደርሱባት አለፉ፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል አልፎ አልፎ ጦርነት አካል ግጭቶች ሲቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን አካባቢው ጦርነትም ሰላምም የሌለበት ሁኔታ ፍጥጫና ምንጊዜም ስጋት እንዳንዣበበበት ቀጥሏል። የሁለቱን አገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት ወደ ሰላም ለማሻገር የአለም አገራት በየጊዜው ጥረት ቢያደርጉም ተሳካ ሲባል እየከሸፈ አመታት አልፈዋል።

ባሳለፍነው ዓመት ፈረንሳይ በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል ተቋርጦ የነበረውን የሰላም ውይይት ተመልሶ እንዲያንሰራራ ስታደርግ የነበረውን ጥረት ማስታወስ ይቻላል። የአሜሪካ፣ የሩስያ እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ወደ ፓሪስ በመጥራት የሁለቱን ወገኖች ጉዳይ ወደ አለም አቀፍ አጀንዳነት ለመመለስ ስትሞክር የቆየችው አጋጣሚ ለዚሁ ማሳያ እንደሆነ አልጀዚራ ያመላክታል። ከተቋረጠ ሶስት አመት የሆነው የእስራኤልና ፍልስጤም የሰላም ድርድር በሁለት ሀገራት ውይይት ደረጃ እንዲቀጥል አዲሱ የትራምፕ አስተዳደርም እያደረገ ያለው ጥረት ማሳያ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የአለም አገራት በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ ለውጥ ማምጣት አልተቻላቸውም።

ከሰሞኑ የአለም ታላላቅ የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚቀይር ከስተት መፈጠሩን በስፋት በዘገባቸው ዳሰውታል። የአሜሪካው መሪ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ለዓመታት ተግባራዊ ሳይደረግ ሲንፏቀቅ የኖረውንና አሜሪካ ቴላቪቭ ከተማ ላይ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩስአሌም የማሸጋገር ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተደመጠው ይህ ጉዳይ አገራቱ ሰላም እንዲያሰፍኑ እየተደረገ በሚገኘው ጥረት ላይ ጥቁር ጥላውን የሚጥል ይሆናል ሲል የዘገበው ሲኤን ኤን ነው። አሜሪካ የሁለቱ አገራት ጉዳይ ከምንም በላይ ያገባኛል በሚል ስሜት ሰላምን ለማውረድ ላለፉት 20 ዓመታት በጽኑ አቋም ስትታትር ቆይታለች።አገራቱን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማድረስም ያስችላሉ ያለቻቸውን የመፍትሄ ሃሳቦችን በጊዜው በነበሩት መሪዎቿ በማቅረብ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል።

በትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ዘመንም ይሄው ሁኔታ የቀጠለ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ አሜሪካ ላለፉት 20 ዓመታት በጽኑ አቋም ስታሳየው ከነበረው የሁለት ሀገርነት የመፍትሔ ሃሳብ የተለየ ሆኖ ታይቷል። በወቅቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በእስራኤል እና ፍልስጤም ጉዳይ ላይ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ካለው፤ የአንድ ሀገርነት መፍትሔም ይስማማኛል ሲሉ የአገራቱን ሰላም ለመመለስ ትራምፕ በሚያደርጉት ጥረት ላይ በጎ ፍንጭ ያሳየ ክስተት ተብሎለት ማለፉንም ዘገባው ጠቅሷል።

ዘ ኢንዲፔንደንት በሌላ ወገን ጉዳዩ የእስራኤል እና የፍልስጤምን ትኩሳት ዳግም የቀሰቀሰና አሜሪካ አገራቱን ለማስማማት በምታደርገው ጥረት ላይ ጥላሸት የሚጥል እንደሆነ በስፋት ዳሶታል። ዘገባው እንዳሰፈረው፤ ለአስተዳደሩ ምናልባትም ኤምባሲውን የማዘዋወር ሂደቱን መጀመሩ የሚኖረው አደጋ አነስተኛ ቢመስልም፤ ነገር ግን አሜሪካ አገራቱን ለማስማማት በምታደርገው የሰላም ድርድር ላይ ትልቅ ተጽእኖ የሚኖረው ነው።

የሲኤንኤን ዘጋቢው አሮን ዴቪድ ሚለር እየሩሳሌምን እንደ እስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠቱ አደጋው ከፍተኛ መሆኑን በትንታኔው አቅርቧል። ከዚሁ ጋር በማያያዝም የአሜሪካን በእስራኤል እና ፍልስጤም ድርድር ፍትሃዊ መስመር የመያዙ ሃቅ ላይ ጥያቄ የሚፈጥር እንደሆነ በዘገባው ተዳስሷል። በዶናልድ ትራምፕ ዘመንም ከአድሎአዊነት በነፃ መልኩ ለአገራቱ የጋራ ጥቅም ዘብ ቆሜያለሁ የምትለውን አሜሪካንን ልብ መርምሮ ያሳየ ክስተት ሆኗል ተብሏል። አገራቱን ለማስማማት የምታደርገው ጥረት የእስራኤልን ጥቅም ለማስከበር ያለመ መልክ አለው ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ እንደሆነም ሲኤን ኤን ፅፏል።

የእስራኤል እና ፍልስጤም የዘመናት የደም መፋሰስ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ እየሩሳሌም የእኔ ምድር ነች የሚለው የሁለቱ አገራት ክስ ነው። አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም የማዘዋወሯ ጉዳይ ለእስራኤል እውቅና እንደመስጠት የሚቆጠር መሆኑንም ዘገባው አስፍሯል።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለመምጣት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኤምባሲውን የማዘዋወሩ ጉዳይ አንዱ አጀንዳቸው ነበር። ይሄንንም በቅርቡ አደርገዋለሁ በማለት ቃል መግባታቸውን ዘገባው አስፍሯል። ባሳለፍነው እሮብ እለት አሜሪካ ኤምባሲዋን ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም ታሸጋግራለች በማለት ይፋዊ መግለጫ በመስጠት ቃላቸውን መጠበቃቸውን ለማሳየት እየጣሩ እንደሆነ ዘገባው አመላክቷል። ይህ ውሳኔ ግን በፍልስጤም እና በእስራኤል ድንበር ደም መፋሰስ የሚያስከትል መሆኑን ዘግቧል።

ቢቢሲ በሌላ በኩል ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን በቀጥታ እውቅና አይስጡ እንጂ በተዘዋዋሪ እንደማረጋገጫ የሚቆጠር ነው ሲል ዘግቧል። ይህንን ንግግራቸውን ተከትሎም ከአረቡ አለም አገራት በኩል ተቃውሞ መሰንዘሩን በመረጃው አካቷል። የከተማይቱ ዕጣ ፋንታ በእስራኤል እና በአረቦች መካከል ከሚፈጠሩ እኩይ ችግሮች አንዱ ነው። በመሆኑም የአሜሪካ የእየሩስአሌምን ዋና ከተማነት ለእስራኤል ማረጋገጫ የመስጠቱ ዳፋ በቀጠናው ለተኩስ እና ለደም መፋሰስ ምክንያት እንደሚሆን ምንም እንደማያጠያይቅ ቢቢሲ ዘግቧል።

1995 አሜሪካ በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ ላይ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩስአሌም ለማዘዋወር ከእስራኤል ጋር መፈራረሟን በማስታወስ የዘገበው ደግሞ ሲ ኤን ኤን ነው። አሜሪካ ፍላጎቷን በወቅቱ ይፋ ታድርግ እንጂ ተግባራዊ ለማድረግ ሳትችል በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። የአሁኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጨምሮ ባለፍት 22 ዓመታት አሜሪካንን የመሩት ፕሬዝዳንቶች ሁሉም በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ የሚገኘውን ኤምባሲውን ለማዘዋወር የስምምነታቸውን ፊርማ አኑረዋል። ይሄው ጉዳይም የአሜሪካ ኮንግረንስ በሚያደርገው ስብሰባ ሁሉ አጀንዳ ሆኖ በመቅረብ ውትወታው ሳይቋረጥ ዘልቋል። ይሁን እንጂ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ያሰበ እንጂ የተገበረ መሪ ግን አልነበረም ሲል ፅፏል።

ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩትን አስተያየቶች እና ተቃውሞች ለማስተባበልም አሜሪካ እየሞከረች መሆኗን የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ አቋማቸውን አይናገሩ እንጂ፤ በአገሪቱ ፀጥታ ጉዳይ የዋይት ሃውስ አማካሪው ማችማስተር ውሳኔው በአገራቱ ህልውና ላይ ተፅእኖ የሚኖረው እንደማይሆን መናገሩን ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።