የትራምፕ ስኬትና ፈተናዎች Featured

07 Dec 2017

በአሜሪካን ታሪክ የሪፐብሊካኑ ፓርቲ ተመራጭ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንትነት አወዛጋቢ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ አብዛኛው የድጋፋቸው መሰረት የሆነውን ነጩን የሕብረተሰብ ክፍል ጨምሮ ሌላውም ሕብረተሰብ በፕሬዚዳንቱ ያልተለመደ ቁጡ ባሕርይ በሚሰጡት አወዛጋቢ ውሳኔና በትዊተር ገጻቸው በሚለቁት አጭርና ቆንጣጭ አነጋጋሪ መልዕክታቸው በውሳኔያቸው ሽንፈትን ካለመቀበላቸው ጋር ተደማምሮ ዶናልድ ትራምፕን በአሜሪካን የፕሬዚዳንትነት መንበር ያልተለመዱ ያልተጠበቁ አስደማሚና አነጋጋሪ ሰው አድርጓቸዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ማንም ምን አለ ያሰቡትን ከማድረግና ከመፈጸም ወደኋላ የሚሉ ሰው አይደሉም፡፡ ገና ሀ ብለው ቃለመሀላ ፈጽመው ነጩ ቤተመንግሥት ገብተው በፕሬዚዳንትነት ወንበሩ ሲቀመጡ የተወሰኑ የሙስሊም ሀገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እገዳ አስተላልፈው በፊርማቸው አጽድቀው ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ውሳኔያቸው በመላው አሜሪካና በዓለም አረብ ሀገራት ጭምር ከፍተኛ ተቃውሞ ቀሰቀሰ፡፡ ውሳኔያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ በአቤቱታ ቀርቦ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

ከዚያን ጊዜ በኋላ ልክ ትራምፕ አስቀድመው እንደሰጉት አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎችም የአውሮፓ አገራት በአክራሪ ሙስሊሞች አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ሰሞኑን ቀደም ሲል ትራምፕ የተወሰኑ የሙስሊም ሀገራት ዜጎች አሜሪካን እንዳይገቡ ሲሉ ያሳለፉትን ውሳኔ ሴኔቱ ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡ በወቅቱ በትራምፕ ላይ የተሰነዘረው ከባድ ነቀፌታና የስድብ ውርጅብኝ ከአሜሪካ ሴኔት አባላት ሪፐብሊካንና ዴሞክራቶች ጀምሮ እስከ ሙስሊም ሀገራትና ሕብረተሰብ ድረስ እጅግ የከፋ ነበር፡፡ ሰውየው ግን ፍንክች አላሉም፡፡

ለዚህ ነው ይሄንንና ሌሎችንም አወዛጋቢ ጉዳዮችን የተመለከተው የዋሽንግተን የሲኤንኤን ዘገባ ፕሬዚዳንቱ የግርፊያ ናዳ ቢወርድባቸው አያስገርምም ያለው፡፡ ትራምፕ አሜሪካንን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ከተመረጡበት ቀን ጀምሮ ያሳለፉትን ምርጥና አስከፊ ቀናት በተመለከተ ሲኤንኤን ሰፊ ዘገባ አቅርቧል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የካፒቶልሂል ቆይታቸው የአመራር ጊዜያቸው ያስመዘገቡትን ውጤት ከፍ ለማድረግ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት አሸናፊነታቸውን ለማረጋገጥ 10 ረጅም ወራትን ጠብቀዋል፡፡ ሴኔቱ በታክስ ማሻሻያ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ጨምሮ ያስመዘገቡዋቸው ድሎች ለእሳቸው መጥፎ በሆነው ጊዜ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ሆነው በመምራታቸው ጠልሽተዋል፡፡ የጠቡ መንደርደሪያ የተነሳው ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው የነበሩትን ሚካኤል ፍሊንን አጥምደው ማባረራቸው የልዩ ምክር ቤቱ (ስፔሻል ካውንስል) ሮበርት ሙለር ወደ ኦቫል ኦፊስ የሚያደርጉትን ጉዞ አሳጥሮታል፡፡

በቅርብ ቀናት ይህንን ጥርጣሬ የተመላበትን ሁከትና አመጽ የነገሰበትን የፖለቲካ ዘመን ያስተሳሰረው ክር ምንነት የታክስ ማሻሻያ አዋጁ፤የሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃገብነት ምርመራ፤ከሰሜን ኮርያ ጋር እየተጋጋመ የመጣው የጦርነት አደጋ ተዳምረው የመካከለኛው ጊዜ (ሚድ ተርም) ምርጫ በመጪው ሕዳር ከመካሄዱ በፊት ሁኔታውን መልክ ሊያሲዙ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ሊፈጥር ስለሚችል በጣም አስደሳች ነው፤በታሪክ ውስጥ 45ስተኛው ፕሬዚዳንት የሚኖራቸውንም ቦታ ይወስናል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡

ሪፐብሊካን የታክስ አዋጁን በዓመቱ መጨረሻ በትራምፕ ጠረጴዛ ላይ ለፊርማ ማስቀመጣቸው ከሙለር የምርመራ ግኝት ጋር ተገጣጥሞአል፡፡ ሚካኤል ፍሊን አራተኛው የትራምፕ አጋር የነበረና የተከሰሰ ሲሆን፣ በፕሬዚዳንቱ፤በአማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር፤ በልጃቸው ዶናልድ ትራምፕ ጄአር ላይ ሊመሰክር ይችላል የሚል ከፍተኛ ግምት አለ፡፡ አንዱና ዋነኛው ቁልፍ ጥያቄ ዓርብ እለት ሙለር ፍሊንን በመቃወም የሰነዘረውን ከፍተኛ ምት በተመለከተ ትራምፕ እንዴት ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ የሚለው ነው፡፡

እንደተጠበቀው ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው በዚህ ጉዳይ ቁጣቸውን በመግለጽ ምንም የተሰራ ስህተት የለም ሲሉ ክደዋል፡፡ የራሳቸውን ኤፍቢአይ በመደብደብ በሙለር ምርመራ ፍትህ ይገኛል ብለው እንደማያምኑ የጥርጣሬ ወሳኝ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ ከሰጡት አስተያየት በመነሳት ሁሉም ተመልሶ ወደራሳቸው አንባርቋል፡፡ ትራምፕ የራሳቸው አስከፊ የፖለቲካ ጠላት መሆናቸውን የሚገልጽ ስሜት የተፈጠረ ሲሆን፣ አስተያየቶች ሙለር በኋይት ሀውስ ላይ ፍርሀት በመዝራቱ እንዲሁም ሊሆን የማይችል እንግዳ ሀሳብ የሚለውን በማንሳት ፕሬዚዳንቱ ያለማቋረጥ በትዊተር ገጻቸው መጠቀማቸው የስኬታቸው ቁልፍ ምስጢር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ትራምፕ የፍሊንን ግጭት በተመለከተ ቅዳሜ እለት በራሳቸው የትዊተር አካውንት የቀድሞውን ቅርብ ረዳታቸውን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ያሰናበቱት ለምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስና ለኤፍቢአይ ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር ስለተደረገው ንግግር ላይ በመዋሸቱ ነው ብለዋል፡፡

ትራምፕ የሰጡት አስተያየት ከፍተኛ የፖለቲካ ትኩሳትና ግለት ፈጥሮአል፡፡ ሆን ብለው ወይም ባለማወቅ ሕግን ማደናቀፉን ተቀብለውታልን የሚል ጥያቄም አስነስቷል፡፡ የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚ በገለጹት መሰረት ትራምፕ ፍሊን ለኤፍቢአይ መዋሸቱን ቢያውቁ ኖሮ ከብሔራዊ የደህንነት አማካሪነቱ መባረሩ ቀላል ይሆን ነበር፡፡ ወንጀልን እንደሸፈነና እንደተከራከረ ይታይ ነበር ብለዋል፡፡

የትራምፕ የሕግ አማካሪ ጆን ዶውድ ትራምፕ ሳይሆኑ እኔ ነኝ ትዊቱን የጻፍኩት ብለዋል፡፡ የሲኤንኤን የሕግ ተንታኝ ሚካኤል ዜልዲን በመጀመሪያ ደረጃ ዶውድ ትዊት ሊያደርግ የሚችለው ትራምፕ እንዲያደርግ ከጠየቁት ብቻ ነው ወይንም እሱ ራሱ ከባድ ስህተት ፈጽሟል ሲል ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት ለፕሬዚዳንቱ ግዙፍ ጥፋት ፈጥሮአል ብሏል ዜልዲን፡፡

ዜልዲን ትራምፕ ፍሊንን ሲያባርሩ ኤፍቢአይን መዋሸቱን ያውቃሉ ብሎ በፍጹም እንደማያምን ገልጿል፡፡ ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች በሚል የተጀመረውን ምርመራና የደረሱበትን ውጤት በተመለከተ ተከታታይ የሂደቱ ምእራፍ የሚሰጠው ፍንጭ ሙለር በሚወስዱት እያንዳንዱ እርምጃ ከፍተኛ ግፊትና በምእራቡ ክንፍ ፍርሀት መፈጠሩን የሚያሣይ ሲሆን፣ ይህም በሳምንቱ መጨረሻ ትራምፕ በሰጡት የተለመደ ያልተገራ ትዊታቸው ላይ መንጸባረቁን ይገልጻሉ፡፡ ሌላም ትራምፕን የበለጠ ጥልቅ የፖለቲካ አረንቋ ውስጥ የሚከት ትዊትም ታይቷል፡፡

ትራምፕ በእሁድ እለት ትዊታቸው በፍጹም ኮሚ ፍሊንን መመርመር እንዲያቆም አልጠየኩትም፤ሌላውን የኮሚ ውሸት የሚያሣይ የሀሰት የፈጠራ ዜና ነው ብለውታል፡፡ በራሱ በትዊተር ገጻቸው የተጻፈው ጽሁፍ ትራምፕ እውነቱን አወጡ ጥፋተኛነታቸውን አመኑ አያሰኝም፡፡ነገር ግን ቀለል አድርጎ በሕግ ደረጃ ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ኮሚ ለሙለር ቡድን ይህንን ቃል በቃለ መሀላ ከደገሙ በሕዝብ ፊት ለመመስከር ከፈጸሙት ቃለ መሀላ ጋር ይጋጫል፡፡

ይህም በዘመኑ ሰዎች ማስታወሻ ኮሚ እንደገለጹት ትራምፕ በተግባር በፍሊን ላይ የሚካሄደው ምርመራ እንዲያበቃ ጠይቀውኛል የሚል ነው፡፡ፕሬዚዳንቱ የራሳቸውን አቋም ከተቃወሙ በፌዴራል ምርመራው ላይ ጣልቃ ለመግባት መሞከራቸውን መቀበል ይሆንባቸዋል፡፡

ሁለቱም የድርጊት አማራጮች ለትራምፕና ለፕሬዚዳንትነታቸው ከባድ የሕግና የፖለቲካ አደጋ ያስከትላል፡፡ ሁለቱም የትራምፕን የወደፊት ዕድላቸውን የሚወስኑ ጥያቄዎች ያስነሳሉ፡፡ ለምንድነው ፕሬዚዳንቱ የፍሊንን ምርመራ ለማስቆም እንዲህ ጉጉት ያደረባቸው፤ የቀድሞውስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በአሜሪካን ምርጫ ላይ በሩሲያ ተፈጸመ ስለተባለውና አሁን ለሙለር ለመግለጽ ስለተገደዱት የማታለል ምስጢር ምን ያህል ያውቃሉ የሚሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

ኮሚ እሁድ ምሽት ራሳቸው ለትራምፕ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ትዊተር ውስጥ በመግባት ሰኔ ላይ በኮንግሬስ የሰጡትን ምስክርነት ወደኋላ ተመልሰው ጠቅሰዋል፡፡ የአሜሪካን ሕዝብ እውነቱን እንዲያውቅ እፈልጋለሁ፡፡ ኤፍቢአይ ሀቀኛ ነው፡፡ ኤፍቢአይ ጠንካራ ነው፡፡ ኤፍቢአይ ዛሬም ሁልጊዜም ነጻ ነው ሲሉ ኮሚ ትዊት አድርገዋል፡፡

የካሊፎርኒያው ሴኔተር ዲያኔ ፌይንስቴይን በኋይት ሀውስ አካባቢ ያንዣበበውን የጨለመ አውሎ ንፋስ በኤንቢሲ ቴሌቪዥን ሚት ዘ ፕሬስ ፕሮግራም ላይ በመገኘት አርአያነት ባለው መልኩ ቀለል አድርገውታል፡፡ ፌይንስቴይን አሁን መመልከት የጀመርነው ፍትሕን ለማሰናከል ሁሉም ዓይነት ጉዳዮች በአንድ ላይ መቀመጣቸውን ነው ብለዋል፡፡ በሴኔቱ የጁዲሸሪ ኮሚቴ የራሳቸውን የሩሲያ ምርመራ እያካሄዱ ያሉ ከፍተኛ ዴሞክራት ናቸው ፌይንስቴይን፡፡

የታክስ ማሻሻያውን አሸናፊነት በተመለከተ የሳምንቱ መጨረሻ ጥልቅ በሆነ ሴራ የተሞላ ነበር፡፡ የሙለር ምርመራ ፕሬዚዳንቱ በታክስ ማሻሻያው በሴኔቱ ሙሉ ፖለቲካዊ ዋጋ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ቅዳሜ እለት ጠዋት ፕሬዚዳንቱ በፕሬዚዳንትነታቸው ዘመን በሕግ አውጪነት የተለየና በጣም አስፈላጊ ስለሆነው ወቅት ምርጥ በሆነ ሁኔታ ሲገልጹ በመላው አሜሪካ ሠራተኛ ለሆኑት ቤተሰቦች ግዙፍ የታክስ ቅናሽ ለማድረግ አንድ እርምጃ ወደፊት ቀርበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የታክስ ማሻሻያ እርምጃው በከፍተኛ ደረጃ አነጋጋሪ ቢሆንም የገንዘብ አያያዝ ወግአጥባቂዎች ያለፈውን በኪሳራ በመቁጠር አንቀበልም በሚል ተቃውመውታል፡፡ ዴሞክራቶች ደግሞ በመካከለኛው መደብ መስዋእትነት ለከበርቴው የተደረገ ግዙፍ ስጦታ አድርገው ፈርጀውታል፡፡ ለሪፐብሊካኖች ደግሞ ትርጉም ያለው ታላቅ ድል ነው፡፡ ምክር ቤቱና ሴኔቱ የየራሳቸውን ትርጉም ሰጥተው በማቀናጀት ለትራምፕ ፊርማ ልከውታል፡፡ አዋጁ ከሬገን ዘመን ጀምሮ በጣም በርቀት ተደራሽ የሚሆን የታክስ ሕግ ማሻሻያ ነው፡፡

ትራምፕ በሚወሰደው የታክስ ማሻሻያ እርምጃ ላይ ሲፈርሙ አሁን እንደሚታየው ተቺዎቻቸው በፕሬዚዳንትነታቸው የመጀመሪያ ዓመት የቢሮ ቆይታቸው የፕሬዚዳንቱ ስልጣን ጣሪያ በነካበት ሰዓት አንድ ነጠላ የሆነ ግዙፍ ሕግ በአሸናፊነት በማሳለፋቸው ማፌዝና መቀለድ አይችሉም፡፡ ቢሆንም የታክስ አዋጁ የሚያስከትለውን ፖለቲካዊ እንደምታ ለመገምገም ገና ጊዜ ይወስዳል፡፡

ሪፐብሊካኖች በኮርፖሬት ታክስ ተመኑ ላይ 15 በመቶ ቅናሽ ማድረግ ወርቃማ የኢኮኖሚ ዘመን እንዲቀጣጠል ያደርጋል ብለው ያምናሉ፡፡ መሳጭ በሆነ ደረጃ በሦስተኛው ሩብ ዓመት በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የተገኘውን 3.3 በመቶ ዕድገት በትራምፕ ፕሬዚዳንትነት ዘመን የተገኘውን ውጤት የሚወክል ነው ብለው ያምናሉ፡፡

የደቡብ ካሮሊና ሪፐብሊካን ሴኔተር ቲም ስኮት ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን በተባለው ፕሮግራም ቀርበው ለሲኤንኤኑ ጄክ ታፐር ሲናገሩ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ነን፤ያንን ውድድር ማሸነፍ አለብን፤ይህ ማለት የታክስ ሕጋችን ከቀሪው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ይህ መሆን ሲችል የአሜሪካ ካምፓኒዎች የበለጠ ትርፍ ፤መንግሥትም የበለጠ ገቢ ያገኛል፤ብሔራዊ እዳችንንም ማቃለል እንችላለን በማለት ገልጸዋል፡፡

ቲም ስኮት ትክክል ከሆኑ የስቶክ ገበያው ይስፋፋል፤ብዙ የአሜሪካን ዜጎች ሥራ ያገኛሉ፤ ካምፓኒዎች አዳዲስ ፋብሪካዎችን ይከፍታሉ፡፡ ይህም ሪፐብሊካኖች ለመካከለኛው ምርጫ ሲያመሩ የተመቻቸ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በትራምፕ ግልፍተኛ ባሕሪ የመረራቸው የሪፐብሊካን ድምጽ ሰጪዎች ትራምፕ ከፍተኛ ለውጥና ሀገራዊ የሀብት እድገት ካስመዘገቡ ዳግም ለመመረጥ ለሚያደርጉት ውድድር እንዲያልፉ ምናልባት ሊፈቅዱላቸው ይችላሉ፡፡ግን ደግሞ ወቅቱ ለዴሞክራቶችም ቁልፍ ነው፡፡.

 

ወንድወሰን መኮንን

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።