አነጋጋሪው የእስራኤል ስደተኞችን የማስወጣት ውሳኔ Featured

11 Jan 2018

እስራኤል በሕገወጥ መንገድ በሀገሯ የሚኖሩ ብዙ ሺ አፍሪካውያን ስደተኞች ገንዘብ እየሰጠች ለማስወጣት ውሳኔ አሳልፋለች፡፡ ስደተኞቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ካልወጡ ግን ከመጋቢት መጨረሻ በኋላ እንደምታስርም ሮይተርስ ዘግቦታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በግልጽ በካቢኔ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ስደተኞችን የክፍያ ፕሮግራም አስመልክተው ሲናገሩ ስደተኞች ወደመጡበት ሀገር ወይም ወደ ሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ ይደረጋል ሲሉ በይፋ ለሕዝብ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል በ2013 ከግብጽ ጋር በሚያገናኛት ድንበር ሕገወጥ ስደተኞች ወደግዛቷ ማለፍ እንዳይችሉ ማገጃ ገንብታ ጨርሳለች፡፡ ይህ የማገጃ መስመር በመሰራቱ እስራኤል ሙሉ በሙሉ ውጤታማ በሆነ መልኩ ወደሀገሯ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡትን ስደተኞች ማስቆምና መግታት ችላለች፡፡ ማገጃው ከመሰራቱና ከመጠናቀቁ በፊት ሰልሳ ሺ ያህል ከአፍሪካ የፈለሱ ሕገወጥ ስደተኞች በግብጽ በኩል ያለውን በረሀ አቋርጠው ወደ እስራኤል ገብተዋል፡፡
ወደ እስራኤል የገቡት ብዛት ያላቸው ሕገወጥ ስደተኞች የመጡት ከኤርትራና ሱዳን ሲሆን ብዙዎች እንደሚሉት የተሰደዱት በአገራቸው ያለውን ጦርነትና ግድያ በመሸሽ እንዲሁም ከባድ በሆነ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው፡፡ ሆኖም እስራኤል በኢኮኖሚ ስደተኝነት ነው ያስተናገደቻቸው፡፡ እስራኤል ይፋ ባደረገችው እቅድ መሰረት ለአፍሪካ ስደተኞች ሦስት ሺ500 ዶላር (2900 ፓውንድ) ክፍያ በመስጠት ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ወይም ወደሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ እንዲሁም ነጻ የአየር መጓጓዣ ትኬት ከእስራኤል መንግስት ይሰጣቸዋል፡፡የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ሦስተኛ ሀገር የተባሉት ሩዋንዳና ኡጋንዳ መሆናቸውን ለይተዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ቀደም ባሉት ግዜያት ወደ 20ሺ ሕገወጥ ስደተኞችን አስወጥተናል፤ አሁን ያለው ግዳጅ ቀሪዎቹን መሸኘት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የስደተኞች መስሪያ ቤት ባለስልጣን፤ እስራኤል ውስጥ በሕገወጥ የሚኖሩ 38 ሺ የሚደርሱ ስደተኞች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንድ ሺ420 የሚሆኑት በሁለት የእስር ማእከሎች እንደሚገኙ ከመጋቢት በፊት በፈቃዳቸው ሀገሪቱን ለሚለቁት አነስተኛ ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን የገንዘቡ መጠን ጊዜው ሲጨምር እያነሰ እንደሚሄድ ሕገወጥ ስደተኞቹ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ተጠቅመው እስራኤልን ለቀው የማይወጡ ከሆነ አስገዳጅ የማሰር እርምጃዎች የሚጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አንዳንዶቹ ለጥቂት ዓመታት በእስራኤል በመኖር በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ባላቸውና ብዙ እስራኤላውያን በማይፈልጓቸው ስራዎች ተሰማርተው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡እስራኤል ከአጠቃላዩ አንድ በመቶ ለሚያንሱት ስደተኞች ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ላመለከቱትና ከዓመት በላይ የቆየ ማመልከቻ ላላቸው ጥቂቶች ብቻ ጥገኝነት ሰጥታለች፡፡ እስራኤል የአፍሪካ ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት ታዘገያለች ይህም በፖሊሲዋ ምክንያትና ጥያቄውን ሕጋዊ አድርጋ ባለመቀበል ነው ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይከሷታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የስደተኞች በእስራኤል መገኘት ለእስራኤል ማሕበራዊ ትስስርና ለአይሁዶች ባሕርይ አደጋ ነው ብለው ይጠሩታል፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ደግሞ ስደተኞቹን እንደ ካንሰር ናቸው ብሏል፡፡ ተክሊት ሚካኤል የ29 ዓመት እድሜ ያላት በቴል አቪቭ የምትኖር ከኤርትራ የመጣች ጥገኝነት ጠያቂ ስትሆን እስራኤል ይፋ ባደረገችው አዲስ እቅድ መሰረት አፍሪካውያን ስደተኞችን ለሌሎች መንግስታት ገንዘብ በመክፈል እንዲወስዱ ማድረግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው ትላለች፡፡
አንድ ስደተኛ በበኩሉ፤ በሩዋንዳና በኡጋንዳ ምን እንደሚገጥመን አናውቅም በምትኩ በእስራኤል እስር ቤቶች መቆየትን እንመርጣለን ሲል ለሮይተር ገልጿል፡፡ ኔታንያሁ በቴል አቪቭ ከተማ አካባቢ ባሉ በጣም ድሀ በሆኑ አጎራባቾች አካባቢ ግዙፍ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ ስደተኞች እንደሚኖሩ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ነባር የሆኑ እስራኤላውያን ነዋሪዎች ደሕንነት እንደማይሰማቸው ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለደቡብ ቴል አቪቭ እንዲሁም በሌሎችም በርካታ አጎራባቾች ለሚኖሩ ነዋሪዎች ዛሬ መረጋጋትን ለመፍጠር የግለሰብ ደሕንነትን ለመጠበቅ ሕግና ስርዓትን ለማስከበር የገባነውን ቃል ጠብቀናል ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የእስራኤል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሪየህ ዴሪነ እንዲሁም የሕዝብ ደሕንነት ሚኒስትር ጊላድ ኤርዳን ይፋ ያደረጉት ዕቅድ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ በእነዚህ አዲስ የእስራኤል መንግስት ዕቅዶች መሰረት የኤርትራና የሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች አፍሪካ በሚገኙ ሌሎች ሀገራት እንዲዛወሩ ይህንንም ወደው እንዲቀበሉ ይገደዳሉ፡፡ ካልተቀበሉ እስራኤል ውስጥ እስር ቤት ይገባሉ፡፡
እ.አ.አ መጋቢት 2015 የእስራኤል መንግስት አወዛጋቢ በሆነውና በኃይል ወደሌላ ቦታ የማዛወር ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ያስተ ዋወቀውን ፖሊሲ በተመለከተ ሕገወጥ ስደተኞች እስራኤልን ለቀው በሦስተኛ ሀገራት የተወሰነ መጠለያ እንዲያገኙ ዕድል የሰጠ ነው፡፡
እ.አ.አ ከታህሳስ 2013 እስከ ሰኔ 2017 ከዚህ ፕሮግራም መጀመሪያ አንስቶ አራት ሺ የሚሆኑ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን በመንግስት መርሐ ግብር መሰረት ወደ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት ሩዋንዳና ኡጋንዳ በፈቃደኝነታቸው እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡
ሕገወጥ ስደተኞችን በተመለከተ እስራኤል ያወጣችው ይህ አዲስ ፖሊሲ በከበበው ምስጢራዊነት፤ ተግባራዊነቱን በተመለከተ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ሁኔታውን ለመከታተል በእነዚህ የአፍሪካ ሀገራት እንዲዛወሩ የተደረጉት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ከባድ እንደሆነበት ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እነዚህ ሰዎች በቂ ደሕንነት ወይም በሄዱበት ዘላቂ መፍትሄ እንዳላገኙና በርካታዎቹ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ወደ አፍሪካ ወይም ወደ አውሮፓ ለመንቀሳቀስ ጥረት ማድረጋቸው ስለማይቀር ሁኔታው ያሳሰበው መሆኑን ገልጿል፡፡
እንደ 1951 የስደተኞች ኮንቬንሽን መሰረት እስራኤል ስደተኞችንም ሆነ ዓለምአቀፍ ጥበቃ የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎችን የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ አለባት ሲሉ የድርጅቱ የመከላከል ረዳት ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እስራኤል ዓለም አቀፍ ግዴታዋን እንድትወጣ ሲረዷት ቆይተዋል፡፡ይህም መልሶ በማስፈር ወይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከእስራኤል እንዲወጡ ለተደረጉት ሁለት ሺ400 ስደተኞች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እንድትፈልግ ማድረግን ያካትታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 27 ሺ 500 ኤርትራውያንና ሰባት ሺ800 የሚሆኑ ሱዳናውያን በእስራኤል ይገኛሉ፡፡ እ.አ.አ በ2009 እስራኤል የስደተኞችን ደረጃ እንድትወስን ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከተሰጣት በኋላ ስምንት ኤርትራውያንና ሁለት ሱዳናውያን ብቻ ናቸው በሕጋዊ ደረጃ በባለስልጣናት የሚታወቁት፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።