የአሜሪካን ወታደራዊ አቅም የሚያፈረጥም በጀት Featured

13 Feb 2018

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ አንስቶ ላለፈው አንድ አመት የተለያዩ አነጋጋሪ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ውሳኔና እርምጃቸውም አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት እስከ መባል አድርሷቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አለም በአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ውስጥ በወደቀበት እና ሀገሮች ይህን ለመመከት የተለያዩ እርምጃዎችን በጋራና በተናጠል እየሰሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ሀገራቸው የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አካል እንዳትሆን አድርገዋል፡፡ በዚህም ከአሜሪካ የሚጠበቀው የፋይናንስ ድጋፍ እንዲቀር አርገዋል፡፡ በቅርቡም የአሜሪካንን ፖሊሲ የማያስፈጽሙ ሀገሮች ከሀገሪቱ የሚያገኙት ድጋፍ እንደሚቀንስባቸው አስታውቀዋል፡፡ ሌሎች በርካታ ወገኖችን ሊጎዱ የሚችሉ ውሳኔዎችንም እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን ደግሞ ቅድሚያ አሜሪካ / አሜሪካ ፈርስት/ የሚለውን አቋማቸውን የሚያረጋግጥ እርምጃ በኮንግረሱ አፅድቀዋል፡፡ ሀገሪቱ ለተለያዩ አለም አቀፍና ሀገራዊ ተግባሮች የምትሰጠውን ድጋፍ እየቀነሱ ያሉት ፕሬዚዳንቱ የሀገራቸውን የመከላከያ ሀይል በአያሌው የሚያፈረጥም እና የሚያሳብጥ በጀት ባለፈው ሳምንት አፅድቀዋል፡፡
በኮንግረሱ የጸደቀውና ፕሬዚዳንቱ ፊርማቸውን ያኖሩበት ይህ በጀት 700 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት በታሪክ አይቶት የማያውቅ ሲል አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል፡፡ በጀቱ ከአሜሪካ የቅርብ ተፎካካሪዎች ከሩሲያና ቻይና ወታደራዊ በጀት በእጅጉ ያላቀ ተብሎለታል፡፡ በጀቱ የአሜሪካ ጦር በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ለማሰማራት፣ በርካታ ስልጠናዎችን ለመስጠት፣ አያሌ የጦር መርከቦችን ወደ ጦሩ ለመቀላቀልና ሌሎች ወታደራዊ ተግባሮችን ለማከናወን እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
ይህ በጀት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 716 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያሻቅብ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ማቲስ የሁለቱ አመት በጀት በአጠቃላይ የሀገሪቱን የውጊያ ዝግጁነት በማሳደግ በአፍጋኒስታን ግጭት እንዲሁም በኮሪያ ባህረ ሰላጤ የተደቀነውን የጦርነት ስጋት ለመመከት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ ጦር ከፍተኛ ወጪ በማድረግ አቅሙን እንዲያጠናከር በጀቱ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ዘገባው ጠቁሞ፣ ከዚህ በጀት ፔንታጎን ካለፈው አመት በ94 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው በጀት እንደሚደርሰው ተጠቁሟል፡፡ ይህም ካለፈው አመት በጀቱ በ15 ነጥብ 5 በመቶ ልዩነት እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡
የሀገሪቱ የመከላከያ በጀት በየአመቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ፣የዘንድሮው በጀትም ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ26 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ እኤአ በ2002 ከነበረበት 345 ቢሊዮን ዶላር እኤአ በ2003 ወደ 437 አድጎ እንደነበር ዘገባው አስታውሶ፣ ይህ በጀቱ የጨመረበት ወቅትም አሜሪካ በመስከረም 2001 ጥቃት ከደረሰባት በኋላ አፍጋኒስታንን እና ኢራቅን የወረረችበት እንደነበር አብራርቷል፡፡
እኤአ ከ2011 አንስቶ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የመጣ ሁሉ የሀገሪቱ ኮንግረስ ወታደራዊ እና የሀገር ውስጥ ወጪዎችን በመቀነስ አስፈላጊነት ላይ የወጣውን ህግ ለማስፈጸም ጥብቅ አሰራር ተግባራዊ ሲያደርግ እንደነበር ዘገባው አስታውሶ፣ ይህም የሀገሪቱ መከላከያ ሀይል በተጠንቀቅ ሆኖ ግዳጁን በመወጣት በኩል ውስንነት እንዲታይበት አርጎ እንደነበር አመልክቷል፡፡ ለአመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ የጦር መሳሪያዎች እየተሰነካከሉ እንደነበር እና ጦሩም በቂ ስልጠና ሲጠማ መቆየቱን አመልክቷል፡፡ ይህ የበጀት ችግር በአሜሪካ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ አስፈሪ ደመና አሳይቶ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
‹‹የበጀት እጥረቱ በጦሩና በጦሩ በቤተሰብ ሞራል ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ማጋነን አልፈልግም›› ሲሉ ማቲስ በጀቱ ከመጽደቁ በፊት ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶች ለፔንታጎን ተጨማሪ በጀት መመደብን እንደ ተራ መፍትሄ ሊቆጥሩት ይችሉ ይሆናል ሲሉም መከላከያ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ ከመጣው የጦሩ ወጪ ጋር በተያያዘ በጀቱን በታሪክ ታላቁ አሰኝቶታል ሲልም ነው ዘገባው የጠቀሰው፡፡
በደህንነትና በአለም አቀፉ ምርምር ማዕከል የወታደራዊ በጀት ተንታኙ ቶድ ሀሪሰን ወታደራዊ በጀቱ ለሀገሪቱ ጦር ከሚያስፈልገው ወጪ መጨመር፣ ዘርፉ ውድ ቴክኖሎጂዎችን እየጠየቀ ከመምጣቱ በተጨማሪ በአፍጋኒስታን ፣በኢራቅ፣ እና በመካከለኛው ምስራቅ ለአመታት ከዘለቀው ውጊያና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እያደገ መሄዱን ያብራራሉ፡፡ሰራዊቱ ከዚህ አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር መጓዝ እንዳለበትም ያመለክታሉ፡፡
‹‹የመከላከያ አቅማችን በአሁኑ ወቅት ተመናምኗል›› ሲሉ ባለፈው አርብ የገለፁት ሀሪሰን ፣ ይህን በመለወጥ እኛን የሚመጥን የመከላከያ ሀይል መገንባት አለብን ብለዋል፡፡ ይህን ደግሞ ገንዘብ ብቻ ሊያመጣው እንደማይችልም አስገንዝበዋል፡፡
ዘገባው እንዳመለከተው፤ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በኢራቅ ያላት ጦር ከአስር አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር ውስን የሚባል ነው፡፡ በአፍጋኒስታንም ቢሆን እ.ኤ.አ በ 2010 እና 11 ከነበረበት 100 ሺ ወደ 15 ሺ ወርዷል፡፡ በአንጻሩ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘመን በሶማሊያ እና በየመን ወታደራዊ ዘመቻ እየተካሄደ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ አፍጋኒስታን እያዘመቱም ናቸው፡፡ ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር መርሀ ግብሯን እንድትሰርዝ ግፊት እየተደረገባት ቢሆንም ፣ አሜሪካ ሀገሪቱን ለማንበርከክ ጦር እስከመምዘዝ እንደምትደርስ እየተገመተ ይገኛል ፡፡
ሀገሪቱ አሁን ለወታደራዊ ተግባር የምታውለው ወጪ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከጠየቁት በጀት በላይ የሚፈልግ ነው ተብሏል፡፡ ለ2018 ከተመደበው 700 ቢሊየን ዶላር በጀት ውስጥ ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ ፔንታጎን ለተለያዩ ተግባሮቹ 629 ቢሊየን ዶላሩን ይጠቀማል፡፡ 71 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋው ደግሞ በአፍጋኒስታንና በሌሎች አካባቢዎች ለሚካሄደው ወታደራዊ ተግባር እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ባለፈው አርብ ኮንግረሱ ያጸደቀው በጀት በ2019 ወደ 716 ቢሊየን እንደሚያድግ ያመለከተ መሆኑን ማቲስ ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮው በጀት አሸናፊዎች የሀገሪቱ የመከላከያ ተቋራጮች መሆናቸውም እየተነገረ ነው፡፡ በጀቱ ለፔንታጎን ከፍተኛውን ቅድሚያ በመስጠት የሀገሪቱ የሚሳኤል መከላከል አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተገልጧል፡፡

ኃይሉ ሣህለድንግል

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።