የኢራን የጦር መሣሪያ አቅም መጎልበትና የአሜሪካን ስጋት Featured

10 Mar 2018
ኢራን የጦር መሳሪያ አቅሟን በየጊዜው እያዘመነች ለአሜሪካ ስጋት መሆኗን እያሳየች ትገኛለች፤ ኢራን የጦር መሳሪያ አቅሟን በየጊዜው እያዘመነች ለአሜሪካ ስጋት መሆኗን እያሳየች ትገኛለች፤

የኢራን የጦር መሣሪያ አቅም መፈርጠም ለበርካታ አገራት አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙት የሳውዲ አረቢያ አገሮችና ለእሥራኤል ኢራን የጦር መሣሪያ አቅሟን ማሳደጓ በፍፁም የሚዋጥላቸው አይደለም። አሜሪካና የአውሮፓ አገራትም ቢሆኑ ምንጊዜም የቴህራንን የሚሳይል እንቅስቃሴ በቅርበት ሲከታተሉ ይስተዋላል።
በኢራን ከፍተኛ ኮማንደር የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል አሚር አሊ ሃጂ ዛዲ ከሦስት ቀናት በፊት እንደተናገሩት፤ ኢራን የጦር አቅሟን ለማጎልበት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ጠላቶቿ ገደብ በማስቀመጥ እንቅፋት ሊሆኑባት ቢጥሩም ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።
የኢራን የዜና ወኪል ፕሬስ ቲቪ ዘገባ እንደሚያ ትተው፤ በአገሪቱ የሚደረገው ጫና ቢበረታም ኢራን በጦር መሣሪያ ረገድ የበለጠ እየጠነከረች መጥታለች። ሃጂ ዛዲ በንግግራቸው በተለይም አሜሪካንን አብዝተው የተቹ ሲሆን፣ አሜሪካ በየዕለቱ የጦር መሣሪያ አቅሟን እያሳደገች በኢራን የሚሳይል መርሃግብር ላይ ብትሯን ታነሳለች ብለዋል። ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ከኢራን ተቃራኒ ቢቆም አገሪቱ የጦር መሣሪያ አቅሟን ከማሳደግ ወደ ኋላ እንደማትልም ጄነራሉ ገልጸዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ዬቪስ ሊ ድሪን ባለፈው ሰኞ ከቴህራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በአገሪቱ የባሌስቲክ ሚሳይል ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል። ሊ ድሪን አሁንም በኢራን የሚሳይል መርሃግብር ዙሪያ መሰራት ያለባቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ከአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች ሲገልጹ ተደምጠዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙሐመድ ጃቫር ዛሪፍ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው የመካከለኛው ምሥራቅን ሰላም እየነሱት እንደሚገኝ በትዊተር ገፃቸው ማስፈራቸውን መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡት ሰንብተዋል። የኢራን እንቅስቃሴ በሙሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተከለከለ አለመሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በዚህም «የኢራንን ሕዝብ ልክ በሳዳም ሁሴን የምዕራባውያኑ ድጋፍ ታክሎበት በተሰራ ሴራ ሚሳይል እንደወረደበት አሁን ላይ እንዲደገም አንፈልግም» ሲሉም መልዕክታቸውን አስቀምጠዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ሳላሚ ባለፈው ረቡዕ ቴህራን የጦር መሣሪያ አውደ ርዕይ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢራን አሁን ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለፀገ የጦር ባለቤት ከመሆኗ በተጨማሪ ባለሙያዎቿም እጅግ እየተራቀቁ መጥተዋል። «አሁን በጦር መሣሪያ ቴክኖሎጂ ረገድ ዓለም የደረሰበት ጥግ ላይ እንገኛለን፤ እጅግ የተራቀቁና ውስብስብ የጦር መሣሪያዎች በየዓይነቱ ማምረት ችለናል» ሲሉም ጄነራሉ በስፍራው ለነበሩ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሲገልፁ ተደምጠዋል።
ቴህራን ታይምስ እንዳስነበበው የኢራን የጦር መሣሪያ ቴክኒሺያኖች ባለፉት ዓመታት የዘመኑ አገር በቀል የጦር መሣሪያዎችን በማምረት የአገሪቱን ጦር ብቁ አድርገውታል። ይህ ግን ለቀጣናው አገራት የሚያስፈራና አደገኛ ሳይሆን በምክንያታዊነት የምትጠቀመው እንደሚሆን ዘገባው ያስቀምጣል።
በኢራን ጉዳይ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት መቼም እንደማይታሰብና ተቀባይነት እንደማይኖረው የገለፁት ሌላኛው የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር ኃላፊ ሆሳኒ ሳላሚ ከአል አረቢያን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያስቀምጡት የኢራን የመጨረሻው ግብ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ጦርነት ማካሄድ እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለይም በየመን ኢራን ጎልታ የሃውቲ አማፅያንን በማስታጠቅ ሳውዲ አረቢያን መፈታተኗ ለዚህ በምክንያትነት ይቀመጣል። ከዚህ በተጨማሪ ቴህራን የበሺር አል አሳድ መንግሥትን በኢራን የሚደገፉትን የሂስቦላ ታጣቂዎችን በማስገባት በሳውዲ አረቢያ የሚዛወሩ አማፅያን ላይ ፈተና እንዲሆኑ ማድረጓ ይታወቃል።
ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የቀጣናው የበላይነትን በተመለከተም የአሁኑ አቋሟ ከሳውዲ አረቢያ የተሻለ መሆኑ ግልፅ ነው። ለዚህም ነው ኢራን በጦር መሣሪያ ረገድ ጡንቻዋን ስታፈረጥም ሳውዲ አረቢያና አጋሮቿ ራስ ምታት የሚሆንባቸው። በቀጣናው ሁለት ኃያላን አይኖሩምና አንዱ ልቆ መውጣቱ የግድ ስለሚሆንም ኢራን ሳውዲ አረቢያን ልቃ መገኘቷ አሜሪካንም ይሁን አውሮፓውያንን ሊያስደስት አይችልም።
ሁለቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጎረቤታሞች ኢራንና ሳውዲ አረቢያ ጠላትነታቸው ዘመናትን የተሻገረ ከመሆኑ በተጨማሪ የቀጣናው ሰላም በእነሱ እጅ ይገኛል። ሳውዲ አረቢያ በምዕራባውያኑ ጠንካራ አጋሮች ድጋፍ ተመክታ ለዘመናት ኢራንን በመወንጀል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያገላት ብታደርግም በቀጣናው ላይ ግን የበላይነቱን አሁንም ድረስ በእጇ ልታስገባ አልቻለችም። ቀደም ባሉት ዘመናት ከኢራን ጎን መሰለፍ ከባድ የሆነባቸው አገራት ጭምር አሁን ላይ ከጎኗ መቆም መጀመራቸው የዚህ ትክክለኛ ማሳያ ተደርጎ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ይነሳል።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ከሰሜን ኮሪያ በተጨማሪ አሜሪካንን በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ዙሪያ እንደ ኢራን የተፈታተናት አገር የለም። ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ላቲን አሜሪካ ድረስ ቴህራን የጦር መሣሪያ አቅሟን በማጎልበትና የአሜሪካን የጦር ኃይል አቅም በመወሰን ተፅዕኖዋን ከፍ ማድረግ እንደቻለች ይታወቃል። አሜሪካ ለዚህ አፀፋ አደገኛ ሊባሉ የሚችሉ ስትራቴጂዎችን ከመከተል በዘለለ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣል ኢራን ከተቀረው ዓለም እንድትገለል ትግሏን ብትቀጥልም የተሳካላት ወይንም የሚሳካላት አይመስልም።
አሁን ላይ የአሜሪካ ዓመታዊ የጦር በጀት ከኢራን ዓመታዊ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ቢሆንም ቴህራን በየትኛውም ሁኔታ እጅ ለመስጠትና ከአሜሪካ ወታደራዊ ስትራቴጂ ጋር ስታብር አትታይም። ይልቁንም ኢራን አሜሪካን ሊያስደነብር የሚችል የተለያየ ዘመናዊ ባሊስቲክ ሚሳይልና ሌሎች ግዙፍ የጦር መሣሪያዎችን ማምረት ተያይዛለች። በሰሜን ኮሪያ ዲዛይን የተደረገው «ሻሃብ» በሚል ስያሜ በተለያየ መልኩ የተሰራው ባሊስቲክ ሚሳይል ኢራን ደረቷን እንድትነፋ ከሚያደርጓት ዋነኛው ሲሆን አሜሪካንም በዚህ መሣሪያ ምክንያት እንቅልፍ እንደማትተኛ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ መሣሪያ በተጨማሪ «ሴጂል 1 እና ሴጂል 2» በሚል ኢራን ያመረተችው ሚሳይልም አሜሪካ ላይ ሌላ ፍርሃት የሚፈጥር መሣሪያ ነው። እነዚህ መሣሪያዎች ኢራን እአአ 2008 ላይ የሞከረቻቸው ሲሆኑ መካከለኛና ረጅም ርቀቶችን የመምዘግዘግ አቅም ያላቸው ናቸው።
እአአ 2009 ላይ የአሜሪካ መከላከያ ዋና ጸሐፊ ሮበርት ጌትስ ሴጂል የተባሉት የኢራን ሚሳይሎች በአማካኝ ከሁለት ሺ እስከ ሁለት ሺ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ሊወነጨፉ እንደሚችሉ መናገራቸው ይታወሳል። ይህንንም የኢራን ትላልቅ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በተለይም የመከላከያ ሚኒስትሩ ብርጋዴር ጄነራል ሙስጠፋ ሙሐመድ በወቅቱ ማረጋገጣቸው ይታወቃል። እነዚህ ሚሳይሎች ይህን ያህል ርቀት ሰባት መቶ ሃምሳ ኪሎ ግራም የሚመዝን ቦምብ ተሸክመው እሥራኤልን ብሎም ምሥራቅ አውሮፓን ድባቅ የመምታት አቅም ያላቸው ናቸው። እነዚህ ባሊስቲክ ሚሳይሎች ይህ አቅም የነበራቸው ከአስር ዓመት በፊት ነው። አሁን ላይ ኢራን የጦር መሣሪያ አቅሟን ማዘመኗ ሚሳይሎቹ የኑክሌር ቦምብ የመሸከም አቅም እንዲኖራቸው ሊያደርግ የሚችል ደረጃ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ደግሞ አሜሪካም ሆኑ አጋሮቿ ለሰከንድም ቢሆን ሊሰሙት አይፈልጉም።

ቦጋለ አበበ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።