ጣልቃ ገብነት የሊብያን አንድነት ስጋት ውስጥ ከቶታል Featured

12 Mar 2018

ሊብያ፣ በንጉስ እንድሪስ ሳኑሲ አገዛዝ ስር በነበረችበት እአአ ታህሳስ 24 ቀን 1951 ላይ ነበር ነፃነቷን ያገኘችው፡፡ ከአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ነፃ በመሆኗም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሆነች፡፡ የተባበሩት ሊብያ ሶስት ክልሎችን በመያዝ የተመሰረተች ሲሆን፤ በምዕራብ ትሪፖሊታንያ፣ በምስራቅ ሳይረኒንካ እንዲሁም በደቡብ ፍሬዛናን ይዛለች፡፡ ክልሎቹ የየራሳቸው አስተዳደር ቢኖራቸውም በፌዴራል ስርዓት አንድ በሆነ ህግ ይተዳደሩ እንደነበር አልጀዚራ በድረ ገፁ አስፍሯል፡፡
በወቅቱ እንደ አዲስ የተቋቋመችው ሊብያ፣ ድህነት ያጠቃት በመሆኗ ምንም አይነት መሰረተ ልማት ያልነበራትና ህዝቦቿን ለመመገብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እርዳታ ያቀርብላት ነበር፡፡ ከአስር ዓመታት በኋላ ግን የነዳጅ ሀብቷን በማውጣት በአካባቢው የነዳጅ ምርት አቅራቢ ለመሆን መብቃቷን ዘገባው ያስታውሳል፡፡
ሊብያ በዚህ መልኩ ወደ ሀብታም አገር ብትለወጥም፣ አዲስ ችግር ገጠማት፡፡ አለም አቀፍ የነዳጅ አምራች ድርጅቶችም አገሪቱ የምትተዳደርበት የፌዴራል ስርዓት ደስተኛ አላደረጋቸውም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ድርጅቶቹ ከአንድ አገር ጋር ሳይሆን ውል የሚፈራረሙት ከተለያየ የክልል መንግስታት ጋር በመሆኑ ነበር፡፡ በዚህም እአአ 1963 ላይ ሊብያ በሶስት ክልል ተከፍሎ የነበረውን የአስተዳደር ስርዓት ወደ አንድ በማምጣት በአንድ መንግስት መተዳደር ጀመረች፡፡
ወደ አንድ አገር ከተሸጋገረች ከሀምሳ ዓመታት በኋላ የነዳጅ ሀብቷ የወደፊት እጣ ፈንታዋ ላይ ጥላ አጠላ፡፡ ከአመታት በኋላም ህብረተሰቡ እኩል የሀብት ተጠቃሚ ለመሆን ያለው መብት እንዲረጋገጥለት፤ የክልል መንግስታት አገሪቱ እያፈራች ካለችው ሀብት ተጠቃሚ ለመሆንና በክልሎች ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ለረጅም ዓመታት የሊብያ አድራጊና ፈጣሪ ሆነው የቆዩት ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ እ.አ.አ በ2011 ከተገደሉና ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቱ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አልባ ሆና ዜጎቿ የሰቀቀን ኑሮ ይገፋሉ፤ አገራትም በአገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አንድነቷን ስጋት ላይ ጥለውታል፡፡
እአአ የካቲት 2011ን ለውጥ ተከትሎ በሊብያ ለተከታታይ ሰባት አመታት አለመረጋጋት፣ በግጭትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ ገባች፡፡ በአገሪቱ ጠንካራ መሪ ባለመኖሩ የሊብያን ድንበር የሚያስጠብቅ ቋሚ የሆነ የጦር ሀይል ባለመኖሩም የተለያዩ አገራት ወታደሮች ከድንበር አልፈው ጣልቃ መግባት የጀመሩት ብጥብጡ ከተነሳበት ቀን አንስቶ ነበር፡፡
በደቡብ- የቻድ እና የሱዳን
አማጽያን ጣልቃ ገብነት
ወደ ሊብያ ድንበር የውጭ ሀይሎች እንደፈለጋቸው የገቡት በደቡባዊ ክልል በፍሬዛን ክልል ሲሆን፤ ይሄም ከኒጀር፣ ከቻድና ከሱዳን ጋር የሚያዋስናት ድንበር ነው፡፡ በድንበሩ በኩል ምንም አይነት ቁጥጥር የሚያደርግ የሊቢያ መንግስት ወታደር የለም፡፡ በዚህም የውጭ ሀይሎች ወደ ክልሉ እንደፈለጋቸው በመግባት የራሳቸውን ፍላጎት እያራመዱ እንደሚገኙ ነው ዘገባው የሚያሳየው፡፡
በዚህ አካባቢ ከሚንቀሰቀሱ ቡድኖች መካከል የቻዱ አማፂ ቡድን አንዱ ሲሆን፤ ቡድኑ በክልሉ ከሚገኘው የካሊፍ ሀፍታር ቡድን ጋር እየተዋጋ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ሀፍታር በፍሬዛን ክልል ከሌሎች የውጭ ሀይሎች ድጋፍ እያገኘ ያለ ቡድን መሆኑን ዘገባው ያሳያል፡፡ ከደጋፊዎቹ ውስጥ የሱዳኑ የእኩልነትና የፍትህ አራማጅ ተቃዋሚ ቡድን የሚያገኘውን ድጋፍ ዘገባው በማሳያነት ይጠቅሳል፡፡ በዚህም ባለፈው ወር መጨረሻ አካባቢ በፍሬዛን ክልል ያለው ሁኔታ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፤ በአካባቢው የሚገኙት የውጭ ታጣቂ ሀይሎች በክልሉ ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋር ጦርነት እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
በአካባቢው ያለው ግጭት በስድስት ብርጌድ የተከፈለውን የሊቢያ ናሽናል አርሚ መሪ ሀፍታር ጦር ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ በተደረጉት ጦርነቶች ከቲቡ ብሄር ስድስት ንፁሀን ዜጎች ሲጎዱ ብዙዎች መቁሰላቸውን፤ በጦርነቱም በርካታ የውጭ ሀይሎች መሳተፋቸውን መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡ የሳብሀ ግዛት ከንቲባ ተደርጎ የተመረጠው ሀመድ አል ካሃሊ እንዳለው፤ የቻድና የሱዳን ተዋጊዎች በሳብሃ የሚገኘውን የሊቢያ የጦር ሀይል ላይ ጥቃት አድርሶ ክልሉን የመቆጣጠር አላማ አላቸው፡፡ የቻድ ታጣቂ ቡድን በጊዜያዊነት ቁልፍ የከተማዋን ቦታ መያዙን ማስታወቁን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
በምስራቅ- የተባበሩት አረብ ኢምሬትና የግብፅ ጣልቃ ገብነት
እአአ ሰኔ 2017 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የተባበሩት አረብ ኢምሬት የካሊፍ ሀፍታርን ቡድን እየደገፈች እንደምትገኝ አስታውቆ ነበር፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬት የወታደራዊ ሀይል መሰረት በሊቢያ አል ካሃዲም ከምስራቅ ቤንጋዚ 100 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ አላት፡፡ ይህ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኢምሬት ከክልሏ ውጪ ካላት የወታደራዊ ሀይል መሰረት ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ የተባበሩት አረብ ኢምሬት ለሀፍታር በማገዝ የሂሊኮፍተር ጥቃት በሊብያ የጦር ሃይል ላይ ጥቃት እያደረሰች እንደምትገኝ ዘገባው ያሳያል፡፡
ሀፍታር፣ የተባበሩት መንግስታት በትሪፖሊ ያቋቋመው መንግስት በመቃወም ከቶርቡኩ የህዝብ ተወካዮች ጋር ጥምረት ፈጥሯል፡፡ የሀፍታር መንግስት ምስራቁንና መሀል ሊቢያን ላለፉት አመታት የተቆጣጠረ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለተባበሩት አረብ ኢምሬት ጥቅም ማስገኘቱ ዘገባው ያትታል፡፡
ሀፍታር እራሱን ችሎ ወታደራዊ ሀይል ማቋቋም ባለመቻሉ ከሌላኛዋ አረብ አገር ግብፅ ድጋፍ እየተደረገለትም ይገኛል፡፡ ግብፅ በተለይ ላለፉት አራት አመታት ለሀፍታር ከወታደር ስልጠና ጀምሮ የጦር መሳሪያዎችና ሂሊኮፍተሮች ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በተጨማሪም የሀፍታር ተቃዋሚ የሆኑ ቡድኖችን በተለይ በደርና ከተማና በሌሎች ላይ ጥቃት ማድረሷን ዘገባው ያትታል፡፡
የተከፋፈለች ሊብያ
ሊብያ በክልል፤ በጎሳ እንዲሁም በፖለቲካ መከፋፈልዋ በአገሪቱ ታሪክ አሳዛኝ ከሚባሉ መካከል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተጨማሪም በውጭ ሀይሎች ጣልቃ መግባት አገሪቱ ለሶስ ክልል መከፋፈላቸውን፤ ክልሎቹም እርስ በርስ እየተጋጩ ቢሆንም ያሉባቸው ችግሮች ግን ተመሳሳይ መሆናቸውን ዘባው ያመለክታል፡፡
በምዕራብ ሊቢያ በምትገኘው ትሪፖሊ አለም አቀፍ እውቅና የተሰጠው መንግስት ይገኛል፡፡ በምስራቅ በኩል ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢምሬትና በግብፅ ድጋፍ የሀፍታር ቡድን ተቆጣጥሮታል፡፡ ደቡባዊ ክፍሉ የተለያዩ የውጭ ሀይሎች ታጣቂ ቡድንና በሀፍታር ታማኝ ሀይሎች ቁጥጥር ስር ነው፡፡ የቻድና የሱዳን አማፂ ቡድኖች በደቡብ ያላቸውን ቦታ በማስፋት አሁን ያለውን የይዞታ አቀማመጥ በመለወጥ የሊብያ መንግስት ደግሞ ቦታውን እንዳይዘው ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ዘገባው ይጠቁማል፡፡
አሁን በአገሪቱ ለተፈጠረው ቀውስ ሊብያውያንና የሊብያ መሪዎች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አገሪቱን የተቆጣጠሩት ሀይሎች በአገሪቱ የሚገኘው ሀብት እኩል ለመከፋፈል የነበረው ሀሳብ ውድቅ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ጥቂት ሊብያውያን የክልሎችን ስልጣን ለማግኘት ፍላጎት አላቸው፡፡ ለዚህም የውጭ ታጣቂ ሀይሎችን ለግል ጥቅማቸው ወደ አገሪቱ እያስገቡ ይገኛሉ፡፡ በአሁን ወቅት የውጭ ታጣቂ ሀይሎች አገሪቱ ወደፊት ለምታስበው አንድነት ችግር ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም ያሉትን የርስ በርስ ግጭት አቁመው ወደ አንድነት ለመምጣት የሚያስችል እድሎች እንዳሏቸው ዘገባው ያሳያል፡፡
በፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራውና ራሱን የሊብያ ብሄራዊ ጦር ብሎ የሰየመው የጦር ኃይል የሊብያን ሁለተኛዋን ትልቅ ከተማ ቤንጋዚን ከታጣቂ ቡድኖች ነጥቆ በእጁ ማስገባቱን ባለፈው ሰኔ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ጦር ከተማዋን በቁጥጥሩ ስር ያስገባት ሦስት ዓመታትን ከፈጀ ዘመቻ በኋላ ነበር፡
ቤንጋዚን ለመያዝ በፊልድ ማርሻል ሃፍታር ጦርና በሌሎች ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተካሄደው ዘመቻ የቀድሞው የሊብያ መሪ ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ እ.አ.አ በ2011 ከስልጣን ተወግደው ከተገደሉ በኋላ በበርካታ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት አካል ነው፡፡

መርድ ክፍሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።