የብሩንዲ ዘግናኝ እልቂት እንዳይደገም Featured

15 May 2018

በብሩንዲ ህገመንግስት መሰረት ለአምስት ዓመት በሚዘልቀው ፕሬዚዳንታዊ የስልጣን ዘመን ፣አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ተከታታይ ጊዜ በላይ መመረጥ አይችልም፡፡ እ ኤ አ ከ2005 ጀምሮ ብሩንዲን መምራት የጀመሩት የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፒዬሪ ንኩሪንዚዛ በአንፃሩ ይህን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ተላልፈው አሁን ሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን እያጣጣሙ ይገኛሉ። በቀጣይም በዚሁ ስልጣን ለመቆየትም እየዳዳቸው ነው፡፤
የአገሪቱ ህዝብና ተቃዋሚዎች በወቅቱ ይህ የፕሬዚዳንቱ አካሄድ «ህገ መንግስታዊ አይደለም» ሲሉ ጠንካራ ተቃውሞ ቢያሰሙም፤ፕሬዚዳንቱ በአንፃሩ ‹‹እኤአ በ2005 ለፕሬዚዳንትነት የተመረጥኩት በአገሪቱ ፓርላማ ነው፤ በ2010 ደግሞ በህዝቡ ምርጫ ነው የተሾምኩት፤ ይህ እስከሆነ ድረስ የመወዳደርና የመመረጥ መብት ህገ መንግስቱ ሰጥቶኛል›› በማለት በምርጫው ለሶስተኛ ጊዜ ከሶስት ዓመት በፊት መወዳደር ብቻም ሳይሆን አብላጫውን የህዝብ ድምፅ ማግኘታቸውን አውጀው በፕሬዚዳንትነታቸው ቀጥለዋል።
ይህ የፕሬዚዳንቱ ህገመንግስትን የመጣስ ተግባር ታዲያ በወቅቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም አስከትሏል። ምርጫውም በውጥረት፤ በተኩስ ልውውጥና በፍንዳታ ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን፣ ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሞት፤ በመቶ ሺዎች ለሞቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረት መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ይህም እኤአ ከ1993 እስከ 2005 ድረስ ለ12 ዓመታት ከዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት ክስተት በሁዋላ በአገሪቱ ዜጎች አዕምሮና አካል ላይ መጥፎ ጠባሳ ያሳረፈና መቼም ቢሆን እንዳይደገም የሚፈለግ ነበር፡፡
ይሁንና ይህ የብሩንዲያውያን ስቃይና መከራ ከሶስት ዓመታት በሁዋላ አሁን ሊደገም እየዳደው ይገኛል። ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ መንግስት በቀጣዩ ሃሙስ ህገ መንግስቱን ለማሻሻል ውሳኔ ህዝብ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ መያዙ ነው።
ይህ የመንግስት ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ያጫረ፤ያወዛገበና ብሎም ተቃውሞን የቀሰቀሰ ቢሆንም የቡጁንቡራው መንግስት በአንፃሩ ህገመንግስቱን ለማሻሻል ውሳኔ ህዝብ እንዲያገኝ የሚያስችሉትን ቅስቀሳዎች ከቀናት በፊት በይፋ ጀምሯል። በውሳኔ ህዝቡ ለመሳተፍ ከ5ሚሊየን በላይ ድምፅ ሰጪዎች ተመዝግበዋል። ብሩንዲያውያንም «እደግፋላሁ» ወይም «አልደግፍም» የሚሉ ሁለት አማራጮች ብቻ ተሰጥቷቸዋል።
ከሁሉም በላይ ግን የብሩንዲ መንግስት ህገ መንግስቱን ለማሻሻል ለምን አስፈለገው የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል። እነዚህን ጥያቄዎች ዋቢ በማድረግም መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ተንታኞችም አስተያየታቸውን እያሰፈሩ ይገኛሉ። እነዚህ አካላት እንደሚጋሩት እሳቤም፤ የብሩንዲ መንግስት በዚህ ወቅት ህገ መንግስቱን ማሻሻል የፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ቆይታ ለማራዘም ነው።
በተለይ ይህን እሳቤ በመደገፍ ሰፊ ትንታኔ ያሰፈረው የአልጀዚራ ዘገባ፤ የፐሬዚዳንቱ የሶስተኛ ዓመት የፕሬዚዳንትነት ቆይታ እኤአ በ2020 እንደሚያበቃ በመጠቆም፤ የአገሪቱ መንግስት በአሁኑ ወቅት ህገ መንግስቱን ማሻሻል የፈለገው የፕሬዚዳንቱን መንበረ ስልጣን ለማራዘም እንዲረዳው በማሰብ ነው ሲል አትቷል።
ዘገባው እንዳመለከተው፤ ይህ የህግ መንግስት ማሻሻያ በተለይ በፕሬዚዳንታዊ የስልጣን ዘመን ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። በስራ ላይ ባለው የብሩንዲ ህገመንግስት መሰረት ለአምስት ዓመት በሚዘልቀው ፕሬዚዳንታዊ ስልጣን፣ አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ተከታታይ ጊዜ በላይ መመረጥ አይችልም።
ህገ መንግቱ ተሻሽሎም የአገሪቱ ፐሬዚዳንት ከሁለት ተከታታይ ጊዜ በላይ መመረጥ እንደማይችል ቢያፀናም፤ የስልጣን ቆይታውን ግን ከአምስት ዓመት ወደ ሰባት ዓመት ከፍ ያደርገዋል። ይህ ህገ መንግስት ማሻሻያ የተፈለገው የፕሬዘዳንቱን የስልጣን ቆይታ ለማረዘም ከሆነ ታዲያ የ54 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሁለት ተጨማሪ የሰባት ዓመታት የስልጣን ቆይታ እንዲኖራቸው ያደርጋል ማለት ነው። በሌላ ስሌት ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት አገሪቱን ያገለገሉበት የስልጣን ቆይታ ተረስቶ እስከ 2034 ድረስ በበላይነት መምራት የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው።
በዚህ መልኩ የፖለቲካ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን ህገ መንግስት የማሻሻል ውሳኔው ፕሬዚዳንቱን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው እያሉ ቢሞግቱም፤ የአገሪቱ መንግስት በአንፃሩ ማሻሻያው የፖለቲካ ስነ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋትና ውጤታማ ለማድረግ የታቀደ መሆኑን በማስረዳት ህዝቡ «ማሻሻያውን በመቀበል ድምጹን እንዲሰጥ እየቀሰቀሰ ይገኛል።
ይህን ዋቢ በማድረግ ቪኦኤ እንደዘገበው ደግሞ፤ ፕሬዚዳንቱ ቅስቀሳው በተጀመረበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ ህዝብ ማሻሻያውን ከመቃወም ይልቅ እንዲደግፍ ጥሪ ከማቅረብ ጎን ለጎን ያስገደዱበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡
እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባ፤ፕሬዘዳንቱ 15 አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ህገመንግስቱን የማሻሻል ውጥናቸውን በይፋ የጀመሩት ካለፋው ዓመት አንስቶ ቢሆንም፣የማሻሻል ስራውን ግን ውስጥ ለውስጥ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በዚህ ሂደት በማሻሻያው ላይ ቅሬታ ሊያነሱ የሞከሩም ወገኖች በመንግስት ሐይሎች ለእንግልትና ለእስር ሲዳረጉ ቆይተዋል። የህገ መንግስት ማሻሻያው የጋራ ምክክር ሳይደረግበት በአገሪቱ መንግስት ፍላጎት ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን በመጠቆም ተቃወሞ የሚያሰሙ ወገኖች እየተበራከቱ መጥተዋል።
የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባም እንዲሁ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት የአገሪቱ መንግስት የህገመንግስት ማሻሻያውን ይዘት በሚመለከት በይፋ አላነጋገረንም፤ የሚፈለገውን ያህል በቂ ውይይትና ምክክር ሳይደረገብት የተዘጋጀ ነው፤ ሰነዱ ምን ይዘት እንዳለው በቅጡ አናውቅም፤ በሚል ክፉኛ መቃወማቸውን አስነብቧል።
ህዝቡም ማሻሻያው የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ይልቅ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ቆይታ ለማራዘም የታቀደ ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስንስቷል። ይህ የህዝብ ተቃውሞ ፕሬዚዳንቱ ከሶስት ዓመት በፊት ለሶስተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የተፈጠረው ሞትና ስደት በድጋሚ እንዳይከስት በእጅጉ ተሰግቷል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ፤ የአገሪቱ መንግስት ህዝበ ውሳኔው ከመካሄዱ ቀደም ብሎ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ ጀምሯል። ከእነዚህ ተግባራት መካከልም «የአገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ጥሳችኋል፤ ሙያዊ ስነምግባርን ተከትላችሁ አልሰራችሁም›› በሚል በቢቢሲ፣ቪኦኤ እና በመሳሰሉት የመገናኛ ብዙሃን ላይ የወራት እግድ ማስተላለፉ ለአብነት ይጠቀሳል።
ህዝብ ውሳኔው በአጣብቂኝ ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት አገሪቱን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ያሳለፈው ውሳኔ ብዙዎችን አስግቷል። እንደ ናይጄሪያ ዴይሊ ፖስትዌል ኡኑሲ ዘገባም፤ገዥው ፓርቲ ከቀናት በፊት ፕሬዚዳንቱ «የአለቃዎች ሁሉ አለቃ» ናቸው፤ እሳቸው ያሳለፉት ማንኛውም ውሳኔ ማንም መቃወም አይችልም» ሲል አቋሙን አስታውቋል።
ይህ የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን ፕሬዚዳንቱ ያሰቡትን ለማሳካት አስፈላጊውን እንዲያደርጉ ድፍረቱንና ስልጣኑን እንደሚሰጣቸው በመጥቀስም ተቃዋሚዎቻቸውን ይበልጥ እንዲቆነጥጡ ያስችላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ለሰላም መናጋት ምክንያት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል የሚሉ በርካታ እንዲሆኑ አርጓቸዋል።
በተለይ ውሳኔው በብሩንዲ እኤአ ከ1993 እስከ 2005 ድረስ ለ12 ዓመታት ያህል የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት እንዲደገም ያደርጋል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡ እኤአ 2000 በቀድሞው የፀረ አፓርታይድ ታጋይና የአፍሪካ የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ አሸማጋይነት የእርስ በእርስ ጦርነቱ እንዲቆምና የአሩሻው የሰላምና የእርቅ ስምምነት እንዲጣስ ሰፊ በር ይከፍታል የሚሉ ወገኖችም ተፈጥረዋል፡፡ የአገሪቱ የእምነት አባቶችም ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት ትክክለኛው ጊዜ አለመሆኑን በመወትወት መንግስት ህዝበ ውሳኔውን እንዲያራዘም እየወተወቱ ይገኛሉ።
አሜሪካ ይህ የብሩንዲ ህገ መንግስት የማሻሻል ውሳኔ በእጅጉ አሳስቧታል። እናም የብሩንዲ መንግስት የዜጎችን የመናገር፤ የመሰብሰብና የመደራጃት እንዲሁም የመሳተፍ ዓለምዓቀፍ ህግጋትና ግዴታዎችን በፅኑ እንዲያከብር ጠይቃለች። ቀደም ባሉት ዓመታት የብሩንዲ ህዝብ በሰላም እጦት የከፈለው መስዋእትነት ዛሬ እንዳይደግም ፅኑ ፍላጎቷ መሆኑን በመጥቀስም፣ ይህ እንዳይሆን አስፈላጊን ሁሉ እንደምታደርግም አረጋግጣለች።
መጪውን ሰግተው ከወዲሁ ዓለምዓቀፍ ተቋማት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ የሚጎተጉቱም በርክተዋል። ከእነዚህም አንዱ በደቡብ አፍሪካው ኩዋዛሉ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ፕሮግራም ተመራማሪ ዶክተር ኑቡሲ ክርስቲያን አኒ ኦል ዋነኛው ናቸው።
ፀሃፊው አፍሪካ ዶት ኮም ላይ እንዳሰፈሩት ትንታኔም፤ፕሬዳንቱ በስልጣን ለመቆየት ሲሉ የህገ መንግስት የማሻሻል ተግባር ለመፈጸም እየወሰዱ ያሉት እርምጃ ውጤቱ አደገኛ ነው። በተለይ የአሩሻውን የሰላም ስምምነት የሚጥስ ይሆናል። እናም ይህ ከሆነ የአፍሪካ ልማት፣ ዲሞክራሲና ህዝቦች ድህንነት ያገባኛል የሚለው የአፍሪካ ህብረት በቡሩንዲ ዜጎች ላይ ቀደም ሲል ያረፈባቸው ጥቁር ጠባሳ በድጋሚ እንዳይከሰት የአገሪቱን ውጥረት ለማርገብ ጠንካራ አቋሙን ማሳየት አለበት።
ይሁንና የአፍሪካ ህብረት በራሱ ህገ መንግስት የማሻሻል ሂደትን የሚመለከትበት እይታ ለብዙዎች ግልፅ አይደለም፤ህብረቱ ስልጣንን ለመቆጣጠር መፈንቅለ መንግስት ማካሄድን አጥበቆ የሚከለክለውንና የሚያወግዘውን ያህል፤በስልጣን ለመቆየት ህገመንግስት ለማሻሻል በሚሞክሩት ላይ ጠንካራ አቋም የለውም የሚለው ፀሃፊው፤ኡጋንዳ፤ሩዋንዳ፤ እንዲሁም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የመሳሰሉ አገራት መሪዎች ስልጣን ላይ ለመቆየት ሀገ መንግስታቸውን ሲያሻሽሉና ለማሻሻል ሲዳዱ እያየ እንዳላየ ማለፉን ይጠቅሳል።
ይሁንና እንደ ፀሃፊው እምነት በአፍሪካ ዲሞክራሲን ለማጎልበትና የህዝቦችን ድህንነት ለማረጋጋጥ ከተፈለገ ይህ አይነቱ የህብረቱ እሳቤ መስተካከልና መወገድ አለበት። ይህ ደግሞ ለነገ የሚያድር ተግባር ሳይሆን ዛሬ መጀመር የሚኖርበት ነው።
በእርግጥ በብሩንዲያዊያንም ሆነ በርካታ ወገኖች የትናንቱ አይነት ዘግናኝ የእርስ በእርስ እልቂት ነገም እንዳይከሰት ምኞታቸው ነው። ይህ ክስተት እንዳይፈጸምና ሰላማቸውን ዘላቂ ለማድረግ አስፈላጊውን ለመውጣት ዛሬም ዝግጁ ናቸው። ይሁንና ቀጣዩ ቀን ምን ይዞ እንደሚመጣ ማወቅ ይቸግራቸዋል። እናም ክክፉ ይልቅ ደጉ እንዲመጣ መማፀን ይዘዋል።
አፍሪካና ህዝቦቿም እንደ ታንዛኒያው አሊ ሃሳን ሙዊኒ አይነት ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የስልጣን ቆይታ ጊዜያቸውን በማክበር መንበረ ስልጣኑን ለተተኪ የሚለቁ መሪዎችን እየናፈቁ ነገን ይጠብቃሉ።

ታምራት ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።