ሶሻሊዝም የቬንዝዌላ የውድቀት ምክንያት ይሆን? Featured

11 Jun 2018

ቬንዝዌላ በቅርቡ የፕሬዚዳንት ምርጫ ብታካሂድም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውሶች እስካሁን አለመፈታታቸውን የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡ የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ መሆን፣ የነዳጅ ምርት መቀነስ፣ የወጪ ንግድ መቀነስ፣ በምግብና በመድኃኒት እጥረት ብዙዎች መሰደዳቸው እንዲሁም የአገሪቱ መንግሥት መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ሥልጣን አለመልቀቃቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡
አገሪቱ በነዳጅ ሀብት የበለፀገች ሆና እንዴት እንዲህ ልትሆን ቻለች? ለሚለው ጥያቄ አገሪቱ እየተከተለች ያለው የሶሻሊዝም ሥርዓት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ በርካቶች እንደሚያነሱ ዘገባው ያትታል፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ችግር የሆነው  የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆልና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡  በቅርቡ በአገሪቱ ለተከሰተው የኢኮኖሚ ውደቀት እአአ 2014 ላይ የነበረው የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ቢሆንም በደካማ ፖሊሲ ምክንያት ተመሳሳይ ችግር ከአምስት ዓመት በፊት አጋጥሞ እንደነበር ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለው እጥረት እንዲባባስ የውጭ ምንዛሬ አለመኖር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የችግሩ መንስኤም በአገር ውስጥ ያለውን ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ባለመደረጉ ነው፡፡ በመሠረታዊነት በአገሪቱ ላይ የተከሰተውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት የአገር ውስጥ አምራቾችን ለመጠበቅና የመንግሥት ሠራተኛውን ለማበረታታት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሁጊዮ ቻቬዝ የውጭ ምንዛሬ ላይ ቁጥጥር ዘርግተው እንደነበር ዘገባው ያስታውሳል፡፡ ቀደም ሲል በአገሪቱ ለሚገኙ አቅም የሌላቸው ዜጎች በምግብና በጋዝ ላይ ድጎማ በማድረግ ተጠቃሚ እንደነበሩም ዘገባው ያሳያል፡፡
ነገር ግን የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ቦሊቨር ዋጋ ማጣቱ፣ የአገር ውስጥ ምርቶች ከሌሎች አገር ጋር ያለው ተወዳዳሪነት መቀነሱና የውጭ አገራት ምርቶች ዋጋ መቀነስ የአገር ውስጥ ምርቶች ተፈላጊነት እንዲያጡ ምክንያት መሆኑን ዘገባው ይጠቁማል፡፡ የሚደረገው ድጎማ መነሳት በአገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ንረትና የመገበያያ ገንዘብ መውደቅ አስከትሏል፡፡
አብዛኛው ባለሀብትና ግለሰብ ለቁጥጥርና በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚታየው ችግር መፍትሄ ለማምጣት ከፍተኛ ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ናቸው፡፡ የጥቁር ገበያው እንቅስቃሴ  ዋነኛ የመሠረታዊ ሸቀጦች መግዣ በጀት ከመሆን ባለፈ የምርት ዋጋና አገሪቱ ያስቀመጠችው የመግዣ ዋጋን አጥብቧል፡፡ በዚህም የአገር ውስጥ ምርቶችን ጎድቷል፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶች ከገበያ ውጪ መሆን በአገሪቱ ሙስና እንዲንሰራፋ አድርጓል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚም አሽቆልቁሏል፡፡
በመደበኛው የገንዘብ ምንዛሬና በጥቁር ገበያው መካከል ከፍተኛ የምንዛሬ ልዩነት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ለመንግሥታዊ ቀረጥ ክፍያዎች ጥቁር ገበያው እንዲበረታታ አድርጓል፡፡ በአገሪቱም ሆነ በጎረቤት አገራት ነዳጅና በምግብ ምርት ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት በመኖሩ ምርቶቹን በማገት በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ዋጋዎች በመኖራቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመረቱ ምርቶች እንዳይኖሩ ከማድረጉ በተጨማሪ አገሪቱ በተወሰኑ ምርቶች ብቻ የየዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡
የቀድሞ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ጆርጅ ጎርዳኒ በማዱሮ መንግሥት ላይ በተቀሰቀሰው ሁከት ምክንያት እንዲለቁ ያደረጋቸው ከእአአ 2003 እስከ 2012 ድረስ ሦስት መቶ ቢሊዮን ዶላር በመጥፋቱ ምክንያት ነው፡፡  በአጭር ጊዜ ውስጥ ቻቬዝ ችግሩን ለመፍታት ምንም ዓይነት ጥረት ያላደረጉ ሲሆን የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ከመውደቁ በተጨማሪ የጥቁር ገበያው ሁኔታ በእጥፍ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን በረጅም ጊዜ እቅድ የማህበራዊ ኢኮኖሚው ሁኔታን ለማስተካከልና ለውጥ እንዲመጣበት ለማድረግና አምራች ድርጅቶች በተለይ ህብረት ሥራ ማህበራትንና የግል ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግና የነቃ ዜጋ መፍጠር ላይ ለማተኮር ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚመሩት በአገር በቀል ድርጅቶች ነው፡፡ የህብረት ሥራ ማህበራትም እየቀነሱ ይገኛል፡፡ በተግባር ሲታይ ህብረት ሥራ ማህበራቱ በቂ ካለመሆናቸው በላይ በአሁኑ ወቅት ያሉት ሙሰኞች በመሆናቸው የግል ባለሀብቱ ቁጥር እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ቻቬዝ የመረጡትና የለውጣቸው አካል ያደረጉት 21ኛው ክፍለ ዘመን ሶሻሊዝምን ነው፡፡ ነገር ግን የቬንዝዌላ ኢኮኖሚ የሚፈልገው ገበያ ተኮር የሆነና የግል ባለሀብቱ በብዛት የሚሳተፍበት መሆን እንዳለበት በሥልጣን ቆይታው አረጋግጧል፡፡ የማህበራዊና ኢኮኖሚው እንዲሁም የግል ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ የግል ዘርፉ አገሪቱን በበላይነት እንዲቆጣጠር ይፈለጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ኩባ የምትከተለውን ፖሊሲ ማየት ለቬንዙዌላ ጥቅም የለውም፡፡
ሁለተኛው የአገሪቱ ችግር የሆነው በነዳጅ ሽያጭ የበለፀገች እንደመሆኗና የሶሻሊዝም ርዕዮት ዓለም መገለጫዋ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከሶሻሊዝም መውጣት ካልቻለች አገሪቱ ለከፍተኛ ውድቀት ትዳረጋለች፡፡ የነዳጅ ሽያጭ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን ማዱሮም ይህን በማወቅ ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ በአልጀዚራ ዜና ማሰራጫ በቬንዝዌላ ጉዳይ በታየው ጥናታዊ ፊልም ላይ እንደታየው ለቬንዝዌላና ለሕዝቦቿ የነዳጅ ሽያጭ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የፖለቲካ ሁኔታውም በነዳጅ እንደሚወሰን ነው፡፡
እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ሙግዌል ቲንከር ገለፃ፤ ቻቬዝ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ሁለት ቬንዝዌላ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው ቬንዝዌላ ከነዳጅ ሀብቱ የሚጠቀመው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በነዳጅ ሽያጭ ጥላ ስር የነበረ ነው፡፡   የቬንዝዌላ ተቃዋሚዎች ባቀረቡት ጥያቄ ቻቬዝ የነዳጅ ሽያጩ እኩል ለአገሪቱ ጥቅም ላይ እንደሚውል ቃል ገብተው ነበር፡፡ ነገር ግን ቻቬዝ የአገሪቱን ታሪክ እንደ አዲስ ከሀብታም ሰዎች፣ ከሌላ አገር ዜጎች፣ ከተማሩ እንዲሁም ከምዕራባውያን ውጪ መፃፍ ፈለጉ፡፡
የቬንዝዌላ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ቦሊቫር በማዱሮ አስተዳደር ወቅት ነበር ዋጋ እያጣ የመጣው፡፡ በዚህም በአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ መነሳት ጀመረ፡፡ በተመሳሳይም በአገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች ተፈላጊነት እንዲቀንስና የጥቁር ገበያው የልውውጥ መጠን እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ድርጅቶችና ሀብታም ግለሰቦች በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረጉ ሲሆን የሚያወጡት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ቬንዝዌላን ለአስርት ዓመታት ቀውስ ውስጥ ከቷት ነበር፡፡  
በነዳጅ ላይ የተጣበቀው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጠቀመው የተወሰኑ ቡድኖችን ብቻ ነው፡፡ የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም የተመሰረተው የነዳጅ ሀብት ላይ እንደመሆኑ መንግሥት የነዳጅ ሀብቱን በመጠቀም የኅብረተሰቡን ሕይወት መለወጥ አለበት፡፡ በአገሪቱ ማህበራዊ ትስስሮች የላሉ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ መስራት የማይታሰብ ጉዳይ ነው፡፡
ፖለቲከኞች ለአገሪቱ መከፋፈል ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ቻቬዝ በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር መንስኤ  እራሱን፣ ወታደራዊ ኃይሉንና ሶሻሊዝምን አስቀምጠው ነበር፡፡ ቻቬዝ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን ኢንስቲትዩሽንና የገንዘብ ምንጮችን ወደ ራሱ በማምጣት እንደ አዲስ እንዲደራጁ ሲያደርግ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልገጠመውም፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ደግሞ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መስራት ሲጠበቅባቸው በተቃራኒው በአገሪቱ የፋይናንስና እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው ሶሻሊዝም ሥልጣን አሳታፊ በሆነ ዴሞክራሲና በሶሻል ኢኮኖሚ በመታገዝ አገሪቱን ከነዳጅ ጥገኝነት ማውጣት ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ የተቀመጡት ነገሮች አገሪቱን ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርገዋታል፡፡ የሥልጣን ሽግግሩን ባህላዊ ከሆነ አሠራር በማውጣት ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ተጠያቂነት የሰፈነበት በማድረግ አገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ካፒታሊዝም በራሱ ለሙስና በር የሚከፍት አይደለም፡፡ ቻቬዝ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሶሻሊዝም ለአገሪቱ  ውድቀት መንስኤ አልነበረም፡፡ በማዱሮ ዘመን ግን ሶሻሊዝም የአስተዳደሩ ውድቀት ማሳያ ሆኗል።

መርድ ክፍሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።