የአውሮፓውያኑ ህብረት ህልውና Featured

12 Jun 2018

የአውሮፓ ህብረት እ ኤ አ በ 2008 ከተከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ወዲህና ከአረቡ ዓለም ነውጥ በኋላ በአሁኑ ወቅት በስደተኞችና በብሪታኒያ የፍቺ ጥያቄ እጅጉን እየተፈተነ ይገኛል። ለመሰል ቀወሶቹ መፍትሄ ለማኖር ደፋ ቀና እያለ ባለበት ሂደትም ከሰሞኑ ሌላ የራስ ምታት ተጨምሮበታል። መርሁን በተለይ ስደተኞችን የሚመለከተውን ፖሊሲ የሚነቅፉ እንዲሁም የአብዛኞቹን አባል አገራት የጋራ መገበያያ ዩሮን ለመጠቀም ዳተኛ የሆኑ ፓርቲዎች ከወደ ሮም ብቅ ብለውበታል።
ፀረ የአውሮፓ ህብረት አቋም ያላችው ብሔረተኛ ፓርቲዎች ቀስ በቀስ በቀጠናው መስፋፋታቸውና በተለይም በዩሮ ገንዘብ ተጠቃሚ የሆኑ አገሮች የሚከሰተው የበጀት ጉድለትና የእዳ ጫና ቀውስ ህብረቱን እጅግ አስመርሮታል። ቀውሶቹን ተከትሎም ምናልባት ከህብረቱ የወጣችውን የብሪታንያን ፈለግ ለመከተል የሚያስቡ ከዩሮ ተጠቃሚ አባል ሀገራት ማህበር ወይም ደግሞ ከሌሎች ስምምነቶች የሚያፈነግጡ አገራት ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች መንፀባረቅ ጀምረዋል።
በተለይ የፖለቲካ ምሁራን የህግ አርቃቂዎችና የመገናኛ ብዙኃን በህብረቱ ቀጣይ ህልውና ላይ ጥያቄን የሚያስነሱ ሐተታና ገለፃዎችን ማንፀባረቅ ጀምረዋል። አንዳንዶቹ ወቅታዊ ቀውስ ለመነሳቱ ጀርመንን የመሳሰሉ የህብረቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ባለቤቶችና ዘዋሪዎች ከጋራ ውሳኔ ይልቅ የራሳቸው አቋምና አቅምም ለማንፀባረቅ የመፈለጋቸው ውጤት ነው ይላሉ። ሌሎች በአንፃሩ የህብረቱ አገራት የፖለቲካ አንድነት መርህን አለመረዳታቸውና የየራሳቸው የታሪክ የባህልና ሌሎችም መገለጫዎች ለአንድ አውሮፓ ለመስጠት ዳተኛ መሆናቸው እንደሆነም ያሰም ሩበታል።
የኢኮኖሚ ምሁራኑ በበኩላቸው «ወቅታዊው የህብረቱ ቀውስ ሌላ ሳይሆን ህግን በአግባቡ የመተግበርና ያለመተግበር ድምር ውጤት ነው» ይላሉ። እንደ ኢኮኖሚስቶቹ ገለፃም የህብረቱ አባል አገራት የምጣኔ ሀብት ውህደታቸውን ጠንካራና የተሳካ ለማድረግ እ.ኤ.አ 1997 ያፀደቁትና 2005 በጀርመንና በፈረንሳይ ጠያቂነት ማሻሻያ ቀርቦበት ተሻሽሎ የቀረበው የምጣኔ ሀብት ህግ የልዩነትና ወቅታዊው ቀውስ መነሾ ነው።
ይህ ህግ አባል አገራት በዓመት ውስጥ ከሚኖራ ቸው በጀት፤ የሚኖረው ጉድለት በዓመት ከሚያመ ርቱት ጠቅላላ ምርት 3 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ይደነግጋል። የአባል አገራቱ ጠቅላላ ብሔራዊ የመንግሥት ዕዳም በዓመት ከሚያመርቱት ጠቅላላ ምርት ከ60 በመቶ በላይ መሆን እንደሌለበት ያስጠነቅቃል።
«ይሁንና ይህን ህግ ተግባራዊ የሚያደርጉ አገራት ጥቂቶች ናቸው፤ ለዚህም ምክንያቱ አብዛኞቹ በዕዳ ጫና ቀውስ ውስጥ መዘፈቃቸው ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ዓመታትን አልፎ ዛሬ ላይ ከህብረቱ ጋር እንዲፋጠጡ አድርጓቸዋል ይላሉ።
ሲ ኤን ኤን ቲም ሊስተርም፤ በእርግጥም ህብረቱ አባል አገራት ዳግም በኢኮኖሚው ውስጥ ስለ መግባታቸው ያትታል። ከስድስት ዓመታት በፊት ፖርቹጋል፣ አየርላንድ፣ ግሪክ እና ስፔን በተከሰተው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ዛሬም መደገሙም የሚያስ ታውሰው ዘገባው፤ በአሁን ወቅት ፖላንድ ሃንጋሪ፤ ኢጣሊያን ግሪክና ስፔን የቀውሱ ተጠቂዎች መሆናቸውን ያስቀምጣል። የህብረቱ የወቅቱ ቀውስ ቀደም ሲል እንደነበረው ኢኮኖሚያዊ ብቻም ሳይሆን ፖለቲካዊ የሆኑ የፖሊሲ ጥያቄዎች ማስከተሉ የህብረቱና አባል አገራቱን ህልውና አሳሳቢ ያደርገዋል» ይላል።
ፖል ጉድማንን የመሳሰሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሃፍት በአንፃሩ፤ ወቅታዊው ችግር በህብረቱ ውስጥ ዴሞክራሲ ያለመኖሩንና በርካታ የቀጣናው እቅድና ፍላጎቶች በህብረቱ ፓርላማ አልያም ከቀጣናው ህዝብ ሳይሆን በብሄራዊ መንግሥቱ ፍላጎት የሚወሰኑ የመሆናቸው ውጤት መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ ፀሃፊው ገለፃ፤ ህብረቱ ጠንካራ አመራር ብቃት ያላቸው ፖለቲከኞች ቢኖሩትም ከእነሱ ይልቅ ለግል እቅድና ፍላጎታቸው የቆሙና የቀጣናውን ጉዳዮች ሳይቀር በራሳቸው የሚወስኑ ናቸው። አንዳንዶች በአንፃሩ ህብረቱ እንዲዳከም ከጀርባ ሴራ የሚያሴሩ ሲሆን፤ ይህን በመቀመር ቀዳሚ ተወንጃይ የሆነችው ደግሞ ሩሲያ ናት። የኦስትሪያ ብሮድካስት ኦርድ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሰሞኑ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ይህን ጥያቄ ለሞስኮው አለቃ ፕላድሚር ፑቲን ያቀረበ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱም ሩሲያ ውንጀላውን ፈፅሞ እንደማትቀበለውና ህብረቱን ለመከፋፈል አንድም ተግባር አለመፈፀሟን፤ ህብረቱ የአገሪቱ ዋነኛ የንግድና የኢኮኖሚ አጋር መሆኑን መናገራቸውን አመላክቷል።
የተለያዩ የፖለቲካና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔ በመሥራት የሚታወቀው የአሜሪካው የፖለቲካ ካምፓኒ ፀሃፊ ማቲው ካሚኒስኪ በአንፃሩ ከሴራ ይልቅ የአገራት ጫና መኖሩን ይገልፃል። ይሁንና የቀውሱ ዋነኛ ምክንያት ህብረቱ በራሱ መከወን የነበረበትን ተግባር ያለመከወኑ መሆኑን ያስረዳል።
እንደ ፀሃፊው ገለፃ፤ በተለይ እንግሊዝ ከሁለት ዓመት በፊት ከህብረቱ ራሷን ለማፋታት ከወሰነች ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ውጥረት ታፍኗል። በእርግጥም አውሮፓውያኑ ከብሪታኒያ የፍቺ ጥያቄ በኋላ ለህብረ ታቸው በጋራ ለመቆምና ፍቅር እንዳላቸው ለማሳመን ሲዳዱ ተስተውለዋል። ይሁንና የአሜሪካው
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍቅራቸውን ውሃ ቸልሰውበታል። ፕሬዚዳንቱ በተለይም ህብረቱም ሆነ አውሮፓውያን እጅጉን ከሚያፈቅሩት የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት በተጨማሪ በዲፕሎማሲው መስክ ከሚኮሩባቸው ተግባራት አንዱ ከሆነው የኢራን የኒውከሌር ስምምነት አገራቸውን ማስውጣ ታቸውና የአባል አገራትን ህብረት ሸርሽሮታል።
ከዚህ በተጓዳኝ «አውሮፓውያኑ ከእንግሊዝ የፍቺ ጥያቄ በኋላ ህብረትና ስነልቦናቸውን ለማጠናከር መሥራትና የተበላሸውንም በአፋጣኝ ለመጠገን መትጋት ነበረባቸው፤ ይሁንና ይህን ለማድረግ ምንም አልሠሩም የሚለው ፀሃፊው፤ በተለይ ባለፈው ዓመት በፈረንሳይ በተካሄደው ምርጫ የኢማኑኤል ማክሮን አሸናፊ ሆኖ ወደ ሥልጣን መምጣት ለህብረቱ ዳግም ውህደትና ኃያልነት መልካሙን ዜና ቢያበስርም ውጤቱ ግን ዛሬ ላይ በአደባባይ አይታይም።
የአሶሽየትድ ፕሬስ የቢዝነስ ጉዳዮች ተንታኙ ዴቪስ ሙህዝ በበኩሉ፤ ከሰሞኑ ከአውሮጳ ህብረት እንዲሁም ከዩሮ መስራች ሀገሮች አንዷ በሆነችው ኢጣሊያ ባለፈው መጋቢት ወር በተደረገ ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የፖለቲካ ሥልጣኑን በይፋ የተቀላቀሉት ፓርቲዎች የአውሮፓውያኑንና የህብረ ታቸውን ቀውስ ይበልጥ አጡዞታል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በብረትና በአሉሙኒየም ምርቶች ላይ የንግድ ቀረጥ ማሻሻያን በህብረቱ ላይ መጣላቸውንና የብሪታኒያ ፍቺ መቃረብ ደግሞ የቀጣናውን ቀውስ ይበልጥ አጋግሎታል» ነው ያለው
ዶክተር አንጀሎ ክሪስግሎስ የመሳሰሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ፀሃፍትም ብሔረተኛ ፓርቲዎች አውሮፓን እያጥለቀለቁና አውሮፓውያንም ወደ አዲሱ የፖለቲካ ምህዳር እየተጓዙ ስለመሆናቸው ያትታሉ። የብሄርተኛ ፓርቲዎች እያደር ማደግ ደግሞ የፖሊሲ መውድቅ የህዝብ ስጋት ግልፅ ውጤት መሆኑን የሚገልፁት ዶክተሩ፤ ይህንም የህብረቱ አመራሮች ችላ ሊሉት የማይገባ አብይ ስጋት መሆኑን ያሰምሩበታል። በመፍትሄነትም ጠንካራና ፈጣን የለውጥ እቅድ መተግበር የግድ እንደሚል ያመላክታሉ።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ማኑኤል ማክሮንን ከሰሞኑ በአውሮፓው ፓርላማ መድረክ ቆመው የለውጥ እቅዳቸውን ባብራሩበት መድረክ፤ መሰል ከህብረቱ ልዩነት እርምጃ ከእርስ በርስ ጦርነት ጋር አመሳስ ለውታል። ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን እያሳሰበን ነው፤ ይህ ደግሞ እጅጉን የተሳሳተ ምርጫ ነው» ሲሉም ተደምጠዋል።
የጀርመኑ የውጭ ግንኙነት ካውንስል ዳይሬከተር ዳንኤል ሽዋርዘር በአንፃሩ፤ ጀርመንና ፈረንሳይ አፋጣኝ የሚባል የጋራ ፖለቲካዊ ጥምረት መፍጠር እንዳለባቸው ይወተውታሉ። በተለይም ለህብረቱ ወቅታዊ ቀውስ እልባት መስጠትና የቀደመ የአባል አገራቱን አንድነት በመመለስ ረገድ የሁለቱ አገራት መሪዎች የመሪነት ሚናን መጫወት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
የሁለቱ አገራት መሪዎችም ቢሆኑ ህብረቱ የውስጥ ቀውሶቹን መፍታት ከቻለ የውጭ ቀውሶቹ እጅ እንደማያሰጡት ይተማመናሉ። በተለይ ማርኮን የዩሮ ዞን ለውጥ ይረዳል ያሉት እቅድ ለማምጣት መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። የጀርመኗ አቻቸው አንጌላ ሜርከልም ቢሆኑ የማክሮንን እቅድ ዘግይተውም ቢሆን ለመቀበል የተገደዱ መስለዋል። እናም አጋርነታቸውን የሚያመለክት አቋም አሳይተዋል። አውሮፓውያኑም በጋራ በመቆም እጣ ፈንታቸውን በጥንካሬቸው እንዲወስኑ መሟገት ጀምረዋል።
ህብረቱም ህልውናው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን በመረዳት በተለይ የውስጥ ችግሮቹን በሚመለከት በምጣኔ ሀብት ቀውስ ለሚውተረተሩ የዩሮ ዞን ተጠቃሚ የሆኑ አባሎቹ መፍትሄና የፋይናንስ ዘርፉ ለማረጋጋት ዝግጁነቱን አሳይቷል።
በዚህም በምጣኔ ሀብት ቀውስ ለሚውተረተሩ አገራት ኢንቨስትመንት ለማጎልበትና ለመደገፍ 55 ቢሊዮን ዮሮ መድቧል። በዚህ እቅድ መሰረት 27 አባል አገራት 25 ቢሊዮን ዩሮ 2021-2027 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚቋደሱ ሲሆን ከአገራቱ መካከል 19ኙ የአንድ መገበያያ ገንዘብ ተጠቃሚዎች ናቸው፤ እነዚህ ሀገሮች የበለጠውን ገንዘብ የሚያገኙ ይሆናል።
ይህን ለማግኘት ግን አገራት ተቋማዊ ለውጦችን ከመተግበር ጀምሮ የጡረታና ሌሎች ፖሊሲያቸውን ዳግም መፈተሽና ለብራስልሱ አስተዳደር ታዛዥና ታማኝ መሆን እንዳለባቸው አስጠንቅቋል። ቀሪው 30 ቢሊዮን ዮሮ ደግሞ፤ በብድር መልክ የሚቀርብና ወለድ የማይታሰብበት ይሆናል። ፈተና መሆናቸው እየቀረ ነው። ፌዴራላዊ የአውሮፓ ህብረትን የሚናፍቁት የማርኮን እቅድም አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ብዙዎች ተማምነዋል። በዚህ ወር በሚካሄድ ስብሰባም የዩሮ ዞን ክለሳ እቅድ ፓኬጅና ሌሎች እቅዶች ይቀርባሉ ተበሎ ይጠበቃል። ከስብሰባው በፊት ግን ገና ከወዲሁ አገራት በስደተኞች ጉዳይ ይበልጥ የተለያየ አቋም እንዳላቸው የሚያንፀባርቅ አቋም ታይቶባቸዋል።
በርካታ ወገኖች ግን ወቅታዊ ቀውሶችን በመቃኘት የህብረቱ ህልውና አደጋ ላይ ስለመቆሙ ተስማም ተዋል። አንዳንዶች በአንፃሩ በዚህ ሃሳብ ከመስማማት በፊት የህብረቱን ህልውና የሚጠቁ መውን ጠቅላላ ስብሰባ በጉጉት መጠባበቅን ምርጫቸው አድርገዋል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።