የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ድል Featured

13 Jun 2018

ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረውን የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ውይይት ለማዘጋጀት ሲንጋፖር ሰሞኑን ሽር ጉድ ስትል ሰንብታለች፡፡ ከብዙ እሰጥ አገባ በኋላ ትናንት ፕሬዚዳንት ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሲንጋፖር ተገናኝተዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙም በሞቀ ሁኔታ ሰላምታ ተለዋውጠዋል፡፡
በሲንጋፖር በተካሄደው የሁለቱ አገራት ውይይት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጥቅል ስምምነት ተፈራርመው ማጠናቀቃቸው ይፋ ሆኗል። ሁለቱ መሪዎችም በሲንጋፖር ደሴት በሚገኘው ቅንጡ ሆቴል 45 ደቂቃ የቆየ ውይይት አድርገዋል፡፡ ለ70 ዓመታት በባላንጣነት ሲተያዩ የነበሩት አገራት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው መወያየታቸው ወደ ወዳጅነት የሚያመራ ጎዳና ላይ እንደሚገኙ ያመለክታል ሲል ኒውዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡
አሜሪካና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች በሲንጋፖር ያደረጉት የፊት ለፊት ግንኙነት በሁለቱ አገራት አዲስ ታሪክ ያስመዘገበ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ለ70 ዓመታት በጥርጣሬና በስጋት ከመታያየት በኋላ መሪዎቹ የፊት ለፊት ግንኙነት ማድረጋቸው ያልተጠበቀ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ያመለክታሉ፡፡
ከመገናኘታቸው በፊት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጣም ጥልቅ ስሜት እንደተሰማቸውና ጥሩ ውይይት ይሆናል ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም ይህንኑ ስሜታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፥ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ያደረኩት ውይይት ከተጠበቀው በላይ ስኬታማ ነው ብለዋል።
በሲንጋፖር የተካሄደው ውይይት በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰፍኖ የቆየውን ውዝግብ የሚያረግብ ነው ተብሎለታል፡፡ በተለይ አካባቢውን ከኑክሌር ስጋት የሚያላቅቅ እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጋዜጣዊ መግለጫቸው የሰጡት ፍንጭ ይህን ያመለክታል፡፡ አካባቢው ከኑክሌር ነፃ የማድረግ እንቅስቃሴው በፍጥነት መጀመር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ማብለያዎቿን ስትዘጋ አሜሪካ የደህንነት ማስተማመኛ ትሰጣታለች፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም አገራቸው የሚሳይል ማስወንጨፊያዎችን እንደምታስወግድ ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡ ማዕቀቡ ግን ይህ እስኪረጋገጥ ድረስ እንደሚቆይ ነው ያስታወሱት፡፡ በተመሳሳይ አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በቅንጅት የምታካሂደውን የጦር ልምምድ ታቆማለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ የሰሜን ኮሪያው መሪ የዲፕሎማ ሰው፣ አስተዋይና ሰላምን በጸኑ ፈላጊ ሰው ናቸው ሲሉ አድንቀዋቸዋል፡፡ ኪም አገራቸውን ከኑክሌር ነፃ በማድረግ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያጠናከራሉ ሲሉ ተስፋ እንደጣሉባቸው ጠቁመዋል፡፡ ውይይቱ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን የምታቋርጥበት ሂደት መጀመሪያ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በበኩላቸው ያለፈውን በአሉታ የመተያየት አባዜ ለመተው መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ «ጥሩ ግንኙነት እንደሚኖረን አምናለሁ፡፡ ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ የቆየው ፍረጃና ጥሩ ያልሆነ ልምዳችን ለግንኙነታችን እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ሁሉንም ችግር አልፈነዋል» ሲሉ ውይይቱ ፍሬያማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ያደረጉት ውይይት ታሪካዊ መሆኑን አንስተው፤ ዓለም በቅርቡ ለውጦችን ማየት እንደምትጀምር ፍንጭ ሰጥተዋል።
ውይይቱን ተከትሎም የፖለቲካ ተንታኞች ከተጨባጭ ድምዳሜ ይልቅ አመላካች ውጤቶች የተገኙበት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ በዋሽንግተን መከላከያ ማዕከል ምሁር የሆኑት አንቶኒ ሩጊሮ «የሁለቱ አገራት መሪዎች የፈረሙበት ሰነድ ስለ ማዕቀብም ሆነ የሰላም ስምምነት ስለመደረሱ የሚገልጸው ነገር የለም፡፡ በውይይቱ ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦች ብዙም ግልጽ አይደሉም፡፡ ግን ለተጨማሪ ውይይት የሚጋብዙ ናቸው፡፡ በጥቅሉ ሁለቱ አገራት ከውዝግብ ወጥተው ወደ ጥሩ ግንኙነት ሊያመሩ ይችላሉ» ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች በስብሰባቸው ማጠናቀቂያ ከስምምነት ደርሰውብታል የተባለ ሰነድ ላይ ቢፈራረሙም ይዘቱ ግልጽነትና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚጠየቅ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ ቢሆንም ስምምነቱ ሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ትጥቋን የምትፈታበትን አካሄድ የሚያሳይ ጭምር እንደሆነ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቁሟል፡፡
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ውይይቱን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተጠቅመውበታል እያሉ የሚተቹ የፖለቲካ ተንታኞች የመኖራቸውን ያህል ለሰላም ፈር የቀደደ መድረክ ሲሉ የሚገልጹም ጥቂት አይደሉም፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች በሲንጋፖር ፈር ቀዳጅ ውይይት ማድረጋቸውም በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን የኑክሌር ስጋት ዘላቂ መፍትሄ ይሰጠዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣን እንገለጹት «እስካሁን የመጣንበት መንገድ ቀላል አይደለም፡፡ የተሸፈነውን ዓይናችንን ገልጠን፣ አባጣ ጎርባጣውን መንገድ አልፈን እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡ መጪው ጊዜም የወዳጅነታችን ገመድ ማጥበቂያ ይሆናል» ሲሉ ውይይቱ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መሠረት የተጣለበት ተስፋ ሰጪ መሆኑን መግለጻቸውን ዋሽግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
የኪም እና ትራምፕ ታሪካዊ ውይይት በሰሜን ኮሪያ እና አሜሪካ መካከል ለረጅም ጊዜ ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት ይፈታዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እ.አ.አ. ከ1950-1953 ሁለቱ ኮሪያዎች ያደረጉትን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የሻከረ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስታውሳሉ፡፡
በተለይ ሰሜን ኮሪያ የምታደርገው የጦር መሣሪያ ባለቤት የመሆን ሩጫ ተከትሎ አሜሪካ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎች አገራት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተከታታይ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡ ይህም የሰሜን ኮሪያን ኢኮኖሚ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ጋር የቆየውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በግትር አቋማቸው ጸንተው ቆይተዋል፡፡ ይህም አገሪቱ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድትገለልና ኢኮኖሚያዊ ጫናም እንዲበረታባት አድርጎ የቆየ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋርም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከስድብ እስከ ዛቻ አዘል ንግግሮች ድረስ ተለዋውጠዋል፡፡ ይሁንና ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው የደረሰባትን ኢኮኖሚያዊ ጫና እና ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መገለል በመረዳት ይመስላል ከደቡብ ኮሪያ ጋር የነበራቸውን የሻከረ ግንኙነት እንደገና ለማደስ እየሞከሩ ነው፡፡
የሰሜን ኮሪያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ይፋ እንዳደረገው አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር አዲስ የስምምነት ምዕራፍ ለመክፈት ፍላጎት እንዳላት እና ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተስፋ መኖሩን ጠቁሟል፡፡
የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ፍላጎት ለየቅል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የተዳከመው ኢኮኖሚዋን እንዲያንሰራራ ለማድረግ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱላት እና የኑክሌር ባለቤትነቷ እንዲከበር ፍላጎት አላት፡፡ አሜሪካ በበኩሏ ቀዳሚ አጀንዳዋ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን ሙሉ በሙሉ እንድታቋርጥ መሆኑን ተንታኞች አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ስምምነት ላይ ለመድረስ ቀጣይ እና ተከታታይ ውይይቶች ሊደረጉ እንደሚችሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እአአ በ2018 መጀመሪያ ላይ ሰሜን ኮሪያ ያካሄደችውን የሚሳይል ሙከራ ተከትሎ በኮሪያ ልሳነ ምድር ጦርነት ይቀሳቀሳል ተብሎ ተሰግቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእዚህም የተነሳ በአሜሪካና በሰሜን ኮሪያ የቃላት ጦርነት ተጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም እሰጥ አገባውን ወደ ጎን በመተው ሁለቱ አገራት ችግሩን በውይይት ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡ በተለይ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ደቡብ ኮሪያና ቻይና የተጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ያወሳሉ፡፡

ጌትነት ምህረቴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።