አገልግሎት ያልጀመረው ጤና ጣቢያ የፈጠረው ቅሬታ Featured

የጤና ጣቢያው ከፊል ገጽታ እና ጉዳት የደረሰባቸው ንብረቶች፤

በየካ ክፍለከተማ የሚገኘው የየካ አባዶ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት አሥራ ሦስት ጤና ጣቢያ ህንፃ ግንባታ ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት ሆኖታል። ከውጭ ሲታይ የጤና ጣቢያው ህንፃ ጥራቱን ጠብቆ መሰራቱን  ገፅታው ይመሰክራል። ወደ ህንፃው ውስጥ ሲገባ ግን በውጭ ከሚታየው  ተቃራኒ ነገር ያጋጥማል። ህንፃው ውስጥ የሚገኙ በሮች ተሰባብረው፣ እጀታቸው ተነቃቅሏል። መስታወቶቹና የመፀዳጃ ቤት ዕቃዎችም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

ወጣት ብሌን ገብረስላሴ በየካ አባዶ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፕሮጀክት አሥራ ሦስት ውስጥ መኖር ከጀመረች አጭር ጊዜ ሆኗታል። የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው እግሩ ላይ መስታወት ወድቆ ደም በከፍተኛ ደረጃ እየፈሰሰው ህክምና ቦታ ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር ታስታውሳለች። አደጋ የደረሰበት ሰው የህክምና ተቋም ለማግኘት ራቅ ያለ ቦታ መሄድ ስለነበረበት ከፍተኛ ደም ፈሶት ራሱን ስቶ እንደደረሰ ትገልፃለች። «ጤና ጣቢያው አገልግሎት ቢሰጥ አንቸገርም ነበር» በማለት በቁጭት ትናገራለች፡፡

ወይዘሮ አቦነሽ ዳባ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም  ጀምሮ በስፍራው መኖር እንደጀመሩና  ልጆቻችንን ለማስከተብ፣ ሲታመሙ ለማሳከም ሌላ አካባቢ መሄድ አለብን፤ ለተጨማሪ ወጪና ለእንግልት ተዳርገናል ይላሉ። ነፍሰ ጡር በነበሩበት ወቅትም የህክምና ክትትል ለማድረግ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ እንደተገደዱ ይናገራሉ። ሁለተኛ ልጃቸውን ሲወልዱም  ከፍተኛ ወጪ እንዳወጡና ህክምና  ለማግኘት እንደተንገላቱ ያመለክታሉ። እርሳቸውም «እዚሁ ግቢ ያለው ጤና ጣቢያ አገልግሎት ቢሰጥ ያለ ብዙ ወጪ መገላገል እችል ነበር» ይላሉ፡፡

ሌላው ነዋሪ  አቶ ኤልያስ ይፋቶ  እንደሚናገሩት፤  የነዋሪዎቹን አቤቱታ በመያዝ በተደጋጋሚ ለክፍለ ከተማው ጤና ቢሮና ሥራ አስፈፃሚው ቢሮ ደጅ ቢጠኑም ለአንድ ዓመት ያህል መፍትሄ ማግኘት አልቻሉም። ወደሚመለከታቸው ኃላፊዎች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ «በቅርቡ ይሰራል፣ ሥራ ይጀምራል ሌሎች ችግሮችንም ለመፍታት እየሰራን ነው» በማለት ጥሩ ምላሽ ይሰጣቸዋል። ይሁንና እስካሁን መፍትሄ  አላገኙም፡፡

ነዋሪዎቹ እንደሚናገሩት ጤና ጣቢያው እስከ ሐምሌ 2008 ዓ.ም ድረስ ጥበቃ አልነበረውም። ይህ ስላሳሰባቸው ጥበቃ እንዲቀጠር በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው ቢቀጠርም ዘግይቶ የጤና ጣቢያው ንብረት በተለያየ ምክንያት ከወደመ በኋላ ነው። በሌላ በኩል እንደ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማት በአቅራቢያው አለመገንባቱ ችግር መፍጠሩን እንዲሁም የጎርፍ ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህንን ችግራቸውን አቤት የሚሉበት የወረዳ  አስተዳደር በአቅራቢያቸው አለመኖሩ ደግሞ ችግራቸውን አባብሶታል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ሙሉ ተካ ጤና ጣቢያው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ይናገራሉ። ‹‹የነዋሪዎቹን ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢቀርብም የህንፃው ግንባታ በጊዜው አላለቀም ነበር። አምና ተከስቶ የነበረውን የአተት በሽታ  መቆጣጠር  ላይ ነበር ትኩረታችን›› ይላሉ፡፡ በጤና ጣቢያው ህንፃ ላይ የደረሰው ውድመት ህንፃውን ከተረከቡ በኋላ እንደሆነ ግን ያምናሉ፡፡ የደመወዝ ክፍያው አነስተኛ በመሆኑ  በወቅቱ ጥበቃ ለመቅጠር አለማስቻሉን  ይናገራሉ።

ጤና ጣቢያው ተገንብቶ ካለቀ በኋላ ለምን አገልግሎት እንዳልጀመረ ሲጠየቁም ‹‹ጤና ጣቢያው የመብራትና የውሃ አገልግሎት አልተዘረጋለትም። የመብራት ዝርጋታ ችግሩ ትራንስፎርመር አገር ውስጥ ያለመኖር ችግር ነው። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተወሰኑ እቃዎችን የማሟላት ሥራ ተሰርቷል›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጤና ጣቢያው እስካሁን ሥራ መቼ እንደሚጀምር ሲመልሱም ‹‹እየሰራን ነው፣ ወደ 13 የህክምና ባለሙያ ቀጥረን በሌላ ጤና ጣቢያ እየሰሩ ይገኛሉ፣ በቅርቡ ትራንስፎርመር ወደ አገር ይገባል፣ ወንበርና ጠረጴዛ የመሳሰሉትን ገዝተናል፣ እነዚህን የሚከታተል አካል ተመድቦ እየሰራ ነው›› ብለዋል፡፡ አክለውም የጤና ጣቢያው ህንጻ በየካቲት ወር መጨረሻ  ተጠግኖ ያልቃል የሚል ተስፋ ሰጥተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ኃላፊዋ እንደተናገሩት፤ ነዋሪው በቅርብ ጤና ጣቢያ ተገንብቶ እያለ ወደ ሌላ ቦታ ለምን እንሄዳለን በሚል ካልሆነ በስተቀር ብዙም ርቀት የሌለው የጤና ተቋም ስላለ በእዚያ  መጠቀም ይችላል፡፡

የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር  ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ መንገሻ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ነዋሪዎች የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው። ተገንብቶ ያለቀው ጤና ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ነበረበት። በቅርቡ ከተጠባባቂ በጀት ለጤና ጣቢያው ዕድሳት እንዲደረግ ተወስኗል። የተረከቡት ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ ህንጻ ነው። ከከፍታ ቦታ የሚመጣው ጎርፍ የነዋሪዎቹ ቤት እየገባ መቸገራቸውን ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት እንዲስተካከል ተሞክሯል። ይሁንና  በቂ አይደለም።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ጉዳያቸውን አቤት የሚሉበት የቅርብ የወረዳ አስተዳደር ባለመኖሩ በቀጥታ ወደ ክፍለ ከተማ ለመሄድ መገደዳቸውን በተመለከተም «የወረዳ አስተዳደር መኖር እንዳለበት ብናውቅም ችግሩን ክፍለ ከተማው ሊፈታው አይችልም። በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ጉድለቶችና ችግሮች የሚያስፈፅማቸው አካል የተለያየ በመሆኑ ነው ለመፍታት ያስቸገረው›› ብለዋል።

ዜና ሐተታ

ሰላማዊት ንጉሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።