«ጽሕፈት ቤቱ በማንኛውም የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ውስጥ ጣልቃ አይገባም»- ዶክተር ነገሪ ሌንጮ Featured

በአገሪቱ በተለያዩ አካላት የሚሠሩ ወንጀሎችን በማጋለጥ መልካም አስተዳደር ለማስፈን በሚሠሩ ማንኛውም የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ላይ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንዳማይኖረው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር አስታወቁ። በአገሪቱ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ተግባራዊ ለማድረግ ህዝብ በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

    የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ የምርመራ ጋዜጠኝነት በአገሪቱ በተለያዩ አካላት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለህዝብ ይፋ የሚያደርግና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚረዳ በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ በማንኛውም የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ውስጥ  ጣልቃ አይገባም። ከዚህ በፊት በተለያየ መልኩ ጣልቃ ገብነቱ የሚስተዋል ሲሆን፤ ከአሁን በኋላ ሚዲያው ካለማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት የሚሠራበት ሁኔታ ይመቻቻል።

የምርመራ ጋዜጠኝነት በእቅድ እንደመሠራቱ በእቅዱ ዙሪያ የተቋሙ ኃላፊና የሚሠራው አካል ተስማምተው እስከሠሩ ድረስ ማንም የውጭ አካል ማስቆም እንደማይችልና ለማስቆም ህግም እንደማይፈቅድ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ መርሆዎችን በመከተል እስከተሠራ ድረስ የምርመራ ሥራው ለህዝብ ይፋ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

«የግለሰቦችንም ሆነ የተቋምን ስም ይጎዳል በሚል ምክንያት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አንድን የምርመራ ሥራ ሊያስቆም አይችልም» ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ የሚደረግ ከሆነ የሀብት ብክነት ከማስከተሉ ባሻገር ፍትሐዊነት እንዳይሰፍን ያደርጋል።  በመሆኑም እውነት እንዲደበቅ፣ ህዝብ በመንግሥት ላይ  እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ በመሆኑ ሥራው ተሠርቶ ጉዳዩ በህግ ሊዳኝ ይገባል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የምርመራ ጋዜጠኝነትን በአገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ ራሱን የቻለ፣  የተሟላ የሰው ኃይልና አቅርቦት ያለው፣ በየጊዜው ባለሙያዎች ብቃታቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉበት ስርዓት የተዘረጋበት፣ የመረጃ ምንጮች የተጠናከሩበትና የግንኙነት ሥነምህዳሩ የሠፋ ማዕከል ስለሚያስፈልግ ይህን ለማሟላት ጽሕፈት ቤቱ ይሠራል። በተጨማሪም የምርመራ ጋዜጠኝነት ከህዝብ ጋር የሚሠራ ሥራ በመሆኑ ህዝብ ተሳታፊ ሊሆንና የምርመራ ጋዜጠኝነቱን የሚሠራው ጋዜጠኛ ዝግጁ ሊሆን፣ክህሎቱን ሊያሳድግና የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን መቋቋም ያስፈልጋል።

የአገሪቱ ሚዲያ ፍርሐት የነገሠበት፣ በጋዜጠኛውና በአመራሩ መካከል ሠፊ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ጥቂት ሥራዎች ተሠርተው ገዝፈው የሚዘገቡበት፣ ችግሮች እንዳሉ እየታወቀ ለግለሰቦች ወይም ለድርጅቶች ስም በማሰብ ተቀባብተው የሚታለፉበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ይህን ለማስተካከል ከፌዴራል እስከ ክልል የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ለውጥ(ሪፎርም) ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንና ጋዜጠኛው በነፃነት  እውነታዎችን ለህዝብ የሚያወጣበት፣ የተጠያቂነት ስርዓትን የሚዘረጋበትና ለህዝብ ጥብቅና የሚቆምበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየተደረገ ነው ብለዋል። 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።