የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማነት መቼ ይረጋገጥ ይሆን?

በአገሪቱ ወጥ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርትና አዘገጃጀት መኖር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆኑ ተቋማትን ለመደገፍ፣ ድርጅቶችን ከውድቀት ስጋት ለመከላከል እንዲሁም አሉታዊ የኢኮኖሚ ውጤቶችን ለመቀነስ የፋይናንስ ስርዓቱ አለም ዓቀፍ ደረጃን የተከተለና የዘመነ ሊሆን እንደሚገባ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ሆኖም በአገሪቱ ጠንካራ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ በሚገባው ደረጃ አለመዳበሩ ህዝብና መንግስት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ካለማግኘታቸው ባሻገር አሰራሩ ወጥነት እንዲጎድለውና በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን ማድረጉ የዘርፉ ምሁራን አስተያየት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጋሼ የማነ እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ በሚገባው ደረጃ አለመዳበሩ ህዝብና መንግስት ማግኘት ያለበትን ጥቅም አላገኙም፡፡ ምክንያቱም የፋይናንስ ሪፖርቶች እንዲሰሩ አስገዳጅ ህግ ያልነበረ በመሆኑና ከዚህ ቀደም የሚሰሩ የፋይናንስ ሪፖርቶች የተዘበራረቁ፣ ወጥነት የጎደላቸውና ለተጠያቂነት ግልጽ አለመሆናቸው፣ በአገሪቱ ሙያው ባለቤት አልባ ስለነበርና ድርጅቶች ሪፖርት ሲያዘጋጁ ሊከተሉት የሚገባ አለም አቀፍ የፋይናንስ ህግ አለመስፈኑና የትኛው ድርጅት ምን አይነት የፋይናንስ ስርዓት መከተል እንዳለበትም ግልጽ አሰራር አለመኖሩ የመሳሰሉት ችግሮች ተዳምረው ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያልሰፈነበት እንዲሆን አድርገዋል፡፡

በአገሪቱ ወጥ የፋይናንስ ሪፖርትና አዘገጃጀት አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ  አዋጅ ቁጥር 847/2006 ተደንግጎ፤ የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ማቋቋሚያና አሰራሩን መወሰኛ ደንብ ቁጥር 332/2007 ወጥቶ፤ ከሀምሌ  01 ቀን 2009ዓ.ም. ጀምሮ በግልና በመንግስት ዘርፍ ባሉ ድርጅቶች ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ ጋሼ የማነ፤ አዋጁ በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ሂሳባቸውን እንዴት መመዝገብ፣፣ መያዝና ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው እንዲሁም አለም ዓቀፍ የሂሳብ ሪፖርት ደረጃዎች የሚከተሉትን አሰራር በመያዙ የፋይናንስ ስርዓቱ ወጥ እንዲሆን ያደርጋል ይላሉ፡፡

አቶ ጋሼ የማነ እንደሚሉት፤የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰሩትን ህዝብ በግልጽ እንዲገነዘብ የሚያደርግና ኦዲተሮች ስራቸውን በትክክል መስራት እንዲሁም አለመስራታቸውን በቀላሉ ለመረዳት ስለሚያስችል ሃላፊነታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል፡፡ በመሆኑም አስተማማኝና ጥራት ያለው የሂሳብ ሪፖርት  ለማስፈን ሰፊ እገዛ ይኖረዋል፡፡ 

‹‹የጀመረችውን እድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሀብት አስፈላጊ ነው፤ የሀብት ምንጭ የሆነውን የአገር ውስጥ የግብር ስርዓት ለማስፋት ደግሞ የፋይናንስ መረጃዎች እውነተኛ፣ አስተማማኝና በቀላሉ የሚታወቁ ሊሆኑ ይገባል›› የሚሉት አቶ ጋሼ የማነ፤ ይህን ለማስፈን የፋይናንስ ስርዓቱ አለም ዓቀፋዊ አሰራርን መከተል እንዳለበትና ይህም የሂሳብ መግለጫዎችን(ፋይናንሻል ስቴትመንት) ግልጽ ስለሚያደርግ ሙዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ባለሃብቶች እርግጠኛ ሆነው እንዲገቡ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ያሳድጋል፤ መንግስት ሊሰራ የሚችልባቸውን በቀላሉ እንዲለይና የመክፈል አቅሙን ባገናዘበ ሁኔታ እንዲበደርም ያስገድዳል ይላሉ፡፡

 ጠንካራ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት በአካውንቲንግና ኦዲቲንግ ተገቢ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ስለሚያስፈልጉ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል   የሚሉት አቶ ጋሼ የማነ እስካሁን ባለው አሰራር በሂሳብ አያያዝ ላይ በድርጅቶች ከሚስተዋሉ ክፍተቶች መካከል ድርጅቶች ያላቸውን የሀብትና የዕዳ መጠን በትክክል ካለመገንዘብ ዕዳውን በሀብት፤ ሀብቱን በዕዳ ሂሳብ መዝግበው ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም ረጅም አመት ያገለገለ ህንጻ ወይም ተሸከርካሪ ያለው ድርጅት የሀብት መጠኑን ሲመዘገብ ለአሮጌዎቹ ዋጋ አይሰጣቸውም፡፡ ይህ መሆን እንደሌለበትና ዋጋው ሊወጣ የሚገባው ከወቅቱ ገበያ አኳያ እንደሆነ አዲሱ አሰራር ይደነግጋል፡፡

በተመሳሳይ አገልግሎት የማይሰጥ፣ ቀኑ ያለፈበት መድሃኒት፣ ማዳበሪያ፣ ኬሚካል ወዘተ... የማስወገጃ ወጭ የሚያስወጣ በመሆኑ በዕዳ መልኩ መመዝገብ ሲገባው እንደ ሀብት ተመዝግቦ የሚቀመጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ የፋይናንስና ኦዲት ስርዓቱ ካለመዘመኑ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ታደሰ ናቸው፡፡

ተቋማቱ ያላቸውን ሀብትና ዕዳ በትክክል በማወቅ የሚወገደውን በአግባቡ በማስወገድ፤ ጥቅም ላይ መዋል የሚገባውንም ለማዋል የሚረዳ እንዲሁም የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች አለም ዓቀፍ ደረጃዎችን ተከትለው እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ቀደም ሲል በዘልማድ ይሰራባቸው የነበሩ የሂሳብ አያያዝና የሪፖርት አቀራረብ ስርዓቶች አለም ዓቀፍ ደረጃና ወጥነት ባለው መልኩ እንዲቀርቡ የሚያስገድድ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡

አቶ አክሊሉ እንደሚናገሩት፤ የመንግስትና የግል ድርጅቶች በተለያየ ሁኔታ ወደ ተግባር የሚገቡ ሲሆን፤ ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣  የገንዘብ ተቋማት፣ ኩባንያዎች፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ከፍተኛ የሰራተኛ ይዞታ ያላቸው ተቋማት ከሀምሌ 2009ዓ.ም ጀምሮ ሪፖርታቸውን በመዝጋት በ2010 አለም ዓቀፍ የሂሳብ ሪፖርት ደረጃዎችን መሰረት አድርገው በአዲሱ አሰራር እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ ውጤቱ እየተለካ አነስተኛና መካከለኛ የሚባሉ ድርጅቶችም እስከ 2012ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሀብት አመራር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍለ ወልደማርያም እንደሚሉት ደግሞ፤ አዲሱ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሪፖርት አሰራር የተቋሞች የሂሳብ መግለጫ(ፋይናንሺያል ስቴትመንት) በተገቢውና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ስለሚያደርግ ተገቢ ውሳኔ ለመወሰን ያስችላል፡፡ ከአለም ዓቀፍ አቻ ተቋማት ጋር ግልጽ በሆነ መልኩ ለመወዳደርም ይረዳል፡፡ በዚህ ረገድ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በፍጥነት ወደዚህ አሰራር ለመግባት ለባለሙያዎች፣ ለኦዲትና ፋይናንስ ሥራ ሃላፊዎች በአዋጁና በትግበራ ፍኖተ ካርታ ስልጠና እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን፤ የማስፈጸሚያ እቅድ በማዘጋጀት ተወያይቶ አጠናቋል፡፡ በቀጣይ ባለሙያዎች ቴክኒካል የሆኑ ዝርዝር ስልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል፡፡

 ዜና ሐተታ

ዑመር እንድሪስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።