«እጅ የሚወጣው በምክንያት ነው!» - የተከበሩ ሽታዬ ምናለ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እጅ ከማውጣት ያለፈ ምን ይሰራሉ ብለው የሚተቹ አንዳንድ ሰዎች የምክር ቤቱን ሥልጣንና ኃላፊነት ያልተገነዘቡ መሆናቸውን የምክርቤቱ ምክትል አፈጉባዔ አስታወቁ፡፡

ምክትል አፈጉባዔ የተከበሩ ሽታዬ ምናለ በምክር ቤቱ አሰራር ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ «ምክር ቤቱ ጥርስ የሌላው አንበሳ ነው! አባላቱ እጅ ከማውጣት ያለፈ ስልጣን የላቸውም!» ተብሎ ከአንዳንድ ሰዎች ለሚቀርበው ትችት «እጅ ማውጣትም ቀላል ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ያመንበትን ነው እጅ አውጥተን ውሳኔ የምናሳልፈው» በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

«ትችት ሲቀርብ በአግባቡ መሆን አለበት፤  የተቋሙንም ሥራ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል»ያሉት የተከበሩ ሽታዬ ሦስት የመንግሥት አካላት ተነጣጥለው  በህገ-መንግሥቱ መደራጀታቸውንና እነርሱም ህግ አውጭ፣ ህግ ተርጓሚና አስፈጻሚ መሆናቸውን ገልፀው ፤ ምክርቤቱም አስፈጻሚው የሚያመነጨው ህግ ህዝብን የሚጠቅም መሆኑን፣በህጉ ውስጥ የሴቶችና የወንዶች እኩል ተጠቃሚነት መኖሩን በዝርዝር መርምሮ እንደሚያፀድቅ አመልክተዋል፡፡

የተከበሩ ሽታዬ ከአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የሚቀርቡ ህጎች ሁሉ በቀጥታ እንደማይፀድቁና  ህጎች ከመጽደቃቸው በፊት በቂ ውይይትና ክርክር እንደሚያካሂድ አስረድተዋል፡፡

ምክርቤቱን ሥራ የሌለው ተቋም አድርገው የሚያዩ ሰዎች በግላቸውም እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት የተከበሩ ሽታዬ ምክርቤቱ የሀገር ጉዳይ እንደሚያይና  ባደራጃቸው18 ቃሚ  ኮሚቴ አማካኝነት እስከሃያ የሚደርሱ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን እንደሚከታተል አስታውቀዋል፡፡ የእያንዳንዱን አስፈጻሚ መስሪያቤት ዕቅድ ገምግሞ መከታተል ከባድ ኃላፊነት  እንደሆነ አስረድተው፤ ትችቱ ከግንዛቤ እጥረት የመነጨ እንደሚሆንና ይህ መታረም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

«ምክር ቤቱ የአስፈጻሚውን ሥራ መከታተል እንጂ ወርዶ መንገድ ወይም ጤና ጣቢያ አይሰራም» ያሉት የተከበሩ ሽታዬ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመወጣት በኩል ግን አሁን  በበለጠ መስራት እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል፡፡

በምክርቤቱ የፀደቁ ረቂቅ አዋጆች ተፈፃሚነታቸው ላይ ችግር ሲያጋጥም በመጀመሪያ ማስተማርና መደገፍ  ጥፋት ከተገኘም በሥራው ላይ ያሉ ኃላፊዎችን ከቦታው እስከማንሳት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አፈ ጉባዔዋ አመልክተዋል፡፡

ከመሰረተ ልማትና ከቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተሄደውን ርቀት ለአብነት የጠቀሱት አፈ ጉባዔዋ ፤ሥራዎች በዚህ መልኩ ቢሰሩም የወጡ አዋጆች በሙሉ ተፈፃሚ አለመሆናቸውንና ችግሩ በአቅም ውስንነትና ቁርጠኛ ካለመሆን እንደሚመነጭና  የአፈጻጸሞቹ ጉድለቶች በሂደት የሚወገዱ መሆናቸውን እንዲሁም የማህበረሰብ ለውጥ አዝጋሚ መሆኑን በመረዳት ለውጥ ለማምጣት ሁሉም በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።