ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባሻገር ለወጣቶች ተስፋን የሰነቀ የተፋሰስ ልማት

የተፋሰስ ልማት ተፈጥሮን ባለበት በማቆየት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባታ መሰረት የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ነው፡፡ አፈር በጎርፍና በነፋስ ተጠርጎ እንዳይሄድ በሥነ-ሕይወታዊ ዘዴ በመታገዝ የአፈርን ለምነትና የስነ-ምህዳርን ሚዛን የመጠበቅም ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ተራራማ የሆኑና ለእርሻ አመቺ ያልሆኑ ቦታዎችን ወደ ገቢ ምንጭነት በመቀየር ‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ› እንዲሉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ እንድብር ከተማ ግራር ቀበሌ በጎታም ንዑስ ተፋሰስ የሚገኙ ወጣቶች ለዘመናት ለምንም አገልግሎት ይውል ያልነበረንና የጎርፍ፣ አፈር መሸርሸርና የመሬት መናድ ያጋጠመውን 150 ሄክታር ተዳፋት መሬት ለተከታታይ አምስት ዓመታት የተፋሰስ ሥራ በመስራት የተራቆተውን አካባቢ መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በቸሃ ወረዳ እንድብር ከተማ ግራር ቀበሌ ንብ በማነብ ሥራ ከተደራጁ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ሚፍታህ ሁሴን እንደሚለው፤ አካባቢው ለበርካታ ዓመታት ከብት ይውልበት የነበረ በመሆኑ መሬቱ የተጎዳ፣ ምንም ዓይነት የዕጽዋት ዘር የማይታይበት፣ የመሬት አቀማመጡም ተዳፋት በመሆኑ አፈሩ በጎርፍ እየተሸረሸረ የሚገኝ ነበር፡፡ ሆኖም የአካባቢውን መጎዳት ተከትሎ የጉራጌ ዞን ከቸሃ ወረዳ ጋር በመተባበርና ህብረተሰቡን በማስተባበር የተፋሰስ ልማት እንዲሰራና አካባቢው እንዲጠበቅ በማድረጉ በአሁኑ ወቅት ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባሻገር 13 የቀበሌዋ ወጣቶች በንብ ማነብ ሥራ ተደራጅተን እንድንሰራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ተራራማ የሆኑ ቦታዎች ለግብርና ምቹ ባለመሆናቸውና ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለን ባለማሰባችን 150 ሄክታር የሚሸፍነው ቦታ ለበርካታ ዓመታት አፈሩ ሲሸረሸር፣ አካባቢው ወደ  ገደልነት ሲቀየርና ተፈጥሯዊ ውበቱን አጥቶ ምድረ በዳ ሲሆን ተመልክተናል የሚለው ወጣት ሚፍታህ፤ የተሰሩ የተፋሰስ ሥራዎች ለአካባቢው ወጣት ተስፋ የሚያደርግበት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ሌሎች ቦታዎችንም እንዲያማትር አመላክቷል ይላል፡፡    

መሬቱ ከጉዳት አገግሞ ወደነበረበት እንዲመለስ ለአምስት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ሥራ መሰራቱንና አካባቢውን በአጥር በመከለል እንዲጠበቅ መደረጉን የሚገልጸው ወጣት ሚፍታህ፤ ለንብ ማነብ ሊጠቅሙ የሚችሉ አበባዎችን፣ የተለያዩ ዕጽዋቶችንና አፈሩን ቆንጥጠው ሊይዙ የሚችሉ ዛፎችን በማልማት መሬቱን ወደነበረበት መመለስ እንደተቻለ ያስረዳል፡፡ በተለይም ወጣቶቹ ተደራጅተን በሰቀልናቸው 23 ዘመናዊ እና 13 ባህላዊ የንብ ቀፎዎች በተሰቀሉ በሳምንት ውስጥ በ16ቱ ቀፎዎች ንብ ሊገባባቸው ችሏል፡፡ ይህም አካባቢው ነፋሻማ ከመሆኑ ባሻገር ለንብ ማነብ ሥራ አመቺ መሆኑንና ከወራት በኋላ ምርት የማግኘት ተስፋ እንዳለው አመላካች ነው ሲል ይገልፃል፡፡

በካንጋሮ ጫማ ፋብሪካ በቅጥር፣ መርካቶ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሁም በግል ሥራ ተሰማርቶ በድምሩ ለ18 ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ መስራቱንና ይጀመራቸው ሥራዎች በሙሉ ሊያዋጡት  ባለመቻላቸው ወደ ገጠር ተመልሶ የግብርና ሥራ ሲሰራ ያገኘነው ወጣት መውለድደግ ወልደገብርኤል፤ ህይወቴን ለመቀየር አካባቢዬን ለቅቄ ከሄድኩበት ጊዜ ጀምሮ ለ18 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ከቅጥር ጀምሮ እስከ ግል ንግድ ብንቀሳቀስም የከተማ ሕይወት ‹ሞላች ጎደለች› በመሆኑ ራሴን መቀየር አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ወደ ገጠር ተመልሼ በግብርና ሥራ የተሰማራሁ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ድንችና የጓሮ አትክልት በስፋት እያመረትኩ ነው፡፡ በተጨማሪም በተፋሰስ ልማት ሥራ ወደ ጥቅም በተቀየረው በጎታም ንዑስ ተፋሰስ ግራር ቀበሌ ከአካባቢዬ ልጆች ጋር በመደራጀት የንብ ማነብ ሥራም እየሰራሁ ነው፡፡ ሥራው ጅማሬ ላይ ቢሆንም ወደፊት አዋጭ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ይላል፡፡

በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብትና አነስተኛ መስኖ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሺከታ ገብረሰንበት፤ አካባቢው በተፋሰስ ልማት ወደነበረበት ከመመለሱ በፊት በጣም የተጎዳና ከጥቅም ውጪ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በመሬቱ ምንም ዓይነት ዕጽዋት ያልነበረበትና አፈሩ እየተሸረሸረ የሚሄድበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ወረዳው ከዞን ጋር በመሆንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመሰራቱ መሬቱን ወደነበረበት ከመመለስ ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል በማለት ያብራራሉ፡፡

ከአርሶ አደሩ ጋር በተሰራው ሰፊ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንዲተከልበት በማድረግና ከብት እንዳይገባ በማጠር ወደነበረበት መመለስ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው መቶ በመቶ በዕጽዋት እንዲሸፈን የተደረገ ሲሆን፤ ከአገር በቀል የዕጽዋት ዝርያዎች ዝግባ፣ የአበሻ ጥድ፣ ጥቁር እንጨት፣ ኮሶ ተተክለው ማደጋቸውንና ከውጭ ከመጡት ደግሞ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት ሳይኖረው ከሌሎች ጋር አብሮ መብቀል የሚችል ግራቪሊያ የተባለ ዛፍና ሌሎች አበባዎች እንደሚገኙ አቶ ሺከታ ይገልጻሉ፡፡

አርሶ አደሩ የተፋሰስን ሥራ ጠቀሜታ በተገቢው ሁኔታ በመረዳቱ የተጎዱ ቦታዎችን እየመረጠና እየሰራ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩንና በተሰሩ ልማቶች ላይ የጋራ ህግ በማውጣት እየጠበቃቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሺከታ፤ ከብቶች ግጦሽ ፍለጋ በየአቅጣጫው ሲንቀሳቀሱ ጉልበታቸውን ከመጨረስ ጀምሮ፣ ክብደታቸውን በመቀነስ የወተት ምርት ሊሰጡ እንደማይችሉ በመገንዘብና ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት በማመዛዘን ከብቶቹን አስሮ በመቀለብ እያረባ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ወጣቶቹ የተፋሰስ ልማት ሥራን ጠቀሜታ በመረዳት ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን እየፈለጉ ወደ ገቢ ምንጭነት እየቀየሩ ሲሆን፤ ወረዳው የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው የሚሉት፡፡

በመጥረቃት ንዑስ ተፋሰስ ጆካ ቀበሌ ሲሰራ ያገኘሁት ወጣት አርሶ አደር ዘርጋ ቴኒ፤ ለአምስት ጊዜ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በርካታ ቦታዎች መልማት የቻሉ ሲሆን፤ ወደ ገቢ ምንጭነት ለመቀየር የከብት ግጦሽ፣ የድንች ብዜትና ንብ የማነብ ሥራዎችን ወጣቱ በመደራጀት እየሰራ ነው፡፡ ይህም አገልግሎት አይሰጡም የተባሉ መሬቶች ወደ ልማት እንዲገቡ አድርጓል ይላል፡፡  

በጉራጌ  ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አለምነሽ ባዴ፤ በዞኑ የሚሰሩ የተፋሰስ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት 869 ተፋሰሶች የለሙ ቢሆኑም ሙሉ በሙሉ ወጣቱ እየተጠቀመባቸው አይደለም በማለት ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ አለምነሽ እንደ ግራርና ጆካ ቀበሌ ወጣቶች ዓይነት ጅምር ሥራዎች ለመስራትና አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲሁም በገጠር የሚኖረውን ወጣት ተጠቃሚ ለማድረግ በተፋሰስ የሚለሙና ለእርሻ አመች ያልሆኑትን የእንስሳት መኖ እንዲመረትባቸው፣ ነፋሻማ ቦታዎችን አስፈላጊ ግብዓት በማሟላት የንብ ማነብ ሥራ እንዲሰራባቸው እንደሚደረግና በበጀት ዓመቱ እንደ ዞን 120 ሺ 677 ሄክታር መሬት የተፋሰስ ልማት ለመሥራት መታቀዱን፣ ይህን ሊያሳካ የሚችል 502 ሺ 274 አርሶ አደር መመረጣቸውን፣ ከዚህ ውስጥም 68 ሺ 814 ወጣት አርሶ አደሮች መሆናቸውን፣ የተፋሰስ ልማት ሥራውን በተገቢው ሁኔታ ለማከናወንም ከሰው ኃይል፣ ከቦታ መረጣና ከግብዓት አቅርቦት አኳያ አጠቃላይ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ ስራው በ13ቱ ወረዳ በ412 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፤ እስካሁንም 25 በመቶ ሥራው ተሰርቷል ብለዋል፡፡ 

ዜና ሐተታ

ዑመር እንድሪስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።