«የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ ያደርጓታል» - ከንቲባ ድሪባ ኩማ

በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎች ሲጠናቀቁ መዲናዋ ፅዱና አረንጓዴ እንደምትሆን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እየተከናወኑ ከሚገኙ ዘመናዊ የፍሳሽ መሰረተ ልማት ሥራዎች በተለይም የመካኒሳ ቆጣሪና የቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያና  የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች የግንባታ  ፕሮጀክቶች ትናንት ተጎብኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ መዲናዋን ፅዱ እና አረንጓዴ እንደሚያደርጓትና የከተማዋ ዘመናዊነት የሚረጋገጠው በዘመናዊ የፍሳሽ አገልግሎት በመሆኑ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በከተማዋ 70 በመቶ የሚሆነውን ነዋሪ ሙሉ በሙሉ በቀጥታ ከዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ጋር በማገናኘት በመኪና የሚሰጠውን አገልግሎት ያስቀራል ያሉት ከንቲባው «ከተማዋን ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ጋር ከማስተሳሰር ባሻገር አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ግንባር ቀደም እንድትሆንም የሚያግዛት ነው» ብለዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለማርያም በበኩላቸው «ከዚህ ቀደም የነበረው የፍሳሽ ማንሳት አገልግሎት ከከተማዋ ዕድገትና አቅም አንፃር እንደማይመጥን ጠቅሰው፣ በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ግን ከተማዋ የተሻለ የመስመር ፍሳሽ የማንሳት አቅም እንደሚኖር ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በትልልቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የህብረተሰቡን የፍሳሽ ማንሳት ጥያቄ በማስተናገድና ተጣርቶ የሚወጣው ውሃ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል ይደረጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በቀጣይም በከተማዋ ኃይቆች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለከተማዋ መናፈሻና ውበት እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም «ፕሮጀክቱ በቴክኖሎጂ ደረጃው በአገሪቱና በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በመስመርም ሆነ በተሽከርካሪ የሚሰበሰበው ፍሳሽ በጥቅሉ 18 ሺ ሜትር ኪዩብ  የሚሆነው በሰባት ማጣሪያ ጣቢያዎች እየተጣራና እየተወገደ ይገኛል።

ግንባታው 54 በመቶ የደረሰው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያና የፍሳሽ መስመር በቀን 100 ሺ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም ሲኖረው ፕሮጀክቱም በ2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል። ለፕሮጀክቱ የተመደበው አጠቃላይ በጀትም 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ነው።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚከናወነው ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታም በቀን 27 ሺ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ይኖረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመንግሥት የተመደበ ሲሆን፣ ግንባታው በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት ደግሞ በቀን 33 ሺ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን በመገንባት ላይ የሚገኙ ከ50 ሺ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ተጠቃሚ ያደርጋል።         

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።