በጎውን ጅምር ጥላሸት የሚቀባ ድርጊት Featured

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት በምሳሌነት ትጠቅሳለች፡፡ እ..አ እስከ 2030 እንደአገር የሚኖረውን የከባቢ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በ64 በመቶ ለመቀነስ ቃል በመግባትም ከታዳጊ አገራት በቀዳሚነት ተቀምጣለች፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ2008 .ም በአገሪቱ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 708416 ናቸው፡፡ ይህ አሃዝ በየዓመቱ በ17 በመቶ ይጨምራል፡፡ በአብዛኛው የሚገቡ ተሽከርካሪዎችም ያገለገሉ መሆናቸው የከባቢ ሙቀት አማቂ ጋዝ የመቀነስ እቅዱን አይገዳደረውም? ችግሩን ለመከላከልስ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ማስረሻ ይፍሩ በባዮሎጂና በፕላኒንግ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፣ በኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንትም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ በአዲስ አበባ አካባቢ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ጥናትና ምርምር ቲም ያስተባብራሉ፡፡ እርሳቸው በሚያስተባብሩት ቲም የተሰራው ጥናት ያመለከተውም አሮጌ ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጭስ እንደሚለቁ ነው።

እንደ አቶ ማስረሻ ማብራሪያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት ጋር ልቀቱ ሲነጻጸርም በ10 በመቶ ይበልጣል። በከተማው ውስጥ የሚገኙት 50 በመቶ የሚደርሱት ተሽከርካሪዎች ከ20 ዓመት በላይ ያገለገሉ ናቸው። ይህም የጭስ ልቀቱን በማባባስ የአየር ጥራት ችግር እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ የሚወጣው የጭስ ልቀት ከፍተኛ የአየር ብክለት ከማስከተሉም በላይ በሰው ላይ የጤና ችግር ያደርሳል፡፡ የተሽከርካሪውን የሞተር አቅም ያዳክማል።

ከከተማው ከአምስት ዘርፎች የሚለቀቀው ሙቀት አማቂ ጋዝ ምን ያክል እንደሆነ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ በ2012 ..አ የልቀቱ መጠን አራት ነጥብ 89 ሚሊዮን ቶን ካርበን ዳይኦክሳይድ መሆኑም ታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥም 47 በመቶው የሚሆነውን የሚሸፍነው የትራንስፖርት ዘርፍ ነው፡፡ የካርበን ልቀቱ በዚሁ ከቀጠለ ለሙቀት መጨመርም ሆነ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፣ አካባቢን ያገናዘበ የልማት ዕቅድ በማውጣት ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚን መገንባት አዳጋች ያደርገዋል።

አቶ ነጋሽ ተክሉ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መንግሥትን በመወከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሥነ ህዝብ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አገሪቱ የገባችውን ቃል ጥላሸት የሚቀባ፣ በጎ ጅምሩን የሚጎዳ ነው፡፡ ኃይለኛ ጭስ የሚያወጡ ተሽከርካሪዎች ከውጭ አገር እየገቡ ነው፡፡ ቀደም ሲልም የገቡ ተሽከርካሪዎችም ከፍተኛ ጭስ እየለቀቁ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ።

ከተማው በሰፈው በአረንጓዴ ተክል ባልተሸፈነበት ሁኔታ የተሽከርካሪዎቹ በካይ ጭስ አሳሳቢ ነው፡፡ አካሄዱ በዚህ ከቀጠለ አዲስ አበባን ከሻንጋይ ሞስኮና የመሳሰሉ አደገኛ ከተሞች ዝርዝር ውስጥም ያስገባል፡፡ ውጤቱም የነዋሪውን ጤንነት ይጎዳል፣ አገሪቱ የምትከተለውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አካሄድን ያስታል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ሊያሳስብ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ፈጣን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡

ዶክተር አደፍርስ ወርቁ፤ በኢትዮጵያ አካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ሳይንስ ምርምር ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ የአረንጓዴ ልማት ስልቱ መተግበር ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ሙቀት አማቂ ጋዞች የመቀነስ አዝማሚያ አይታይም፡፡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ብዙ ነዳጅ ስለሚጠቀሙ የሚለቁትም ጭስ መጠን ይበዛል፡፡ በከተማው የተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ መጠን በካይ ጋዝ የሚለቁትን ከአገልግሎት የማውጣት አሰራር ዘርግቶ መተግበር ይገባል፡፡

የሙቀት አማቂ ጋዞች በከባቢ አየር ውስጥ መበራከት ሙቀቱን ከፍ ስለሚያደርገው በአንዳንድ ዕጽዋት ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ሰዎችን ኢኮኖሚም ያናጋል፡፡ የዕጽዋትና የእንስሳት የበሽታ ዓይነቶች ሊበዙ ይችላሉ፣ ግብርናን የሚጎዱ መጤ አረሞች አድገው ምርታማነትን ይጎዳሉ፣ በሰው ጤንነትም ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ በሽታዎች ሊበራከቱ ይችላሉ ሲሉ የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለውን ቀውስ ይናገራሉ፡፡ ለውጡ ድርቅ እንዲደጋገምና ሰደድ እሳት በስፋት እንዲነሳ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሙቀት አማቂ ጋዝን ወደ አየር በመልቀቅ የተለመደው አካሄድ ከቀጠለ የሙቀቱ መጠን እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል፡፡ አገሪቱም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመግባት ያዳግታታል፣ ወንዞችና አካባቢዎች ይበከላሉ፣ ልማቱን ማስቀጠልም ያዳግታል፣ በካይ ጋዝን በ64 በመቶ ለመቀነስ የተገባውን ቃል ማሳካት ያስቸግራል ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ዳንኤል ሰይፉ፤ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂና በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትራንስፖርት ባለስልጣን የተሽከርካሪና የተቋማት ስታንዳርድ ዝግጅት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ አገር ውስጥ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ ያገለገሉ በመሆናቸው በጤናና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል ይላሉ፡፡

ከሚገባው መጠን በላይ በካይ ጭስ የሚያወጡ ተሽከርካሪዎች ከመንገድ መወገድ አለባቸው የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ ከቅርብ ዓመታት ይልቅ የሩቅ ዓመታት ስሪት ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት የቀረጥ ሥርዓቱ ቅናሽ ይሰጣል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አስመጪዎች ለማስገባት የሚመርጡት የሩቅ ዓመታት ምርቶችን ነው፡፡ መኪናዎቹ ከገቡ በኋላ ለዕድሳት ከፍተኛ ገንዘብ በማስወጣት የኢኮኖሚ ኪሳራን እንደሚያስከትሉም ይናገራሉ፡፡ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ የጭስ ለቀትን ለመቀነስ የተዘረጋ አሰራር እንዳለ ጠቅሰው፣ ይህ ግን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ባለመጀመሩ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እየተተገበረ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፣ ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ማስረሻ መፍትሄ ብለው የሚያቀርቡት ሃሳብ አላቸው፤ ይህንን ለመታደግ ከሚመ ለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን አውጥቶ ልቀቱን መቀነስ ይገባል፡፡ ለትግበራውም ባለስልጣኑ እንደጀመረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቅንጅት አሰራሩን ማጠናከር ይኖርበታል፣ ባለድርሻዎች የካርበን ልቀቱን ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጡ ቢከሰት ተጋላጭነትን ለመቀነስ በትኩረት መሥራት ይገባቸዋል፡፡

አዳዲስ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ የቀረጥ ሥርዓቱን ማስተካከል ይገባል፡፡ አካባቢን ያገናዘበ የኢኮኖሚ ልማት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ የታቀዱትን ግቦች ለማሳካት እንደሚያስቸግር በማስገንዘብ፣ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንደሚገባም አቶ ማስረሻ ያስገነዝባሉ፡፡

አቶ ነጋሽም፣ ታዳሽ ኃይልን መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በመቀነስ በኤሌክትሪክ ኃይል በሚሰሩ መተካት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በተለመደው አካሄድ ከቀጠለ ግን አገሪቱ የምትከተለውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የልማት አካሄድን ያኮላሻል፣ ኢኮኖሚውን ይጎዳል፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የመሰለፍ ግብን ያሳጣል፣ ከተሞቿም ለኑሮ ተስማሚነታቸው ይቀራል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከፍተኛ ጭስ የሚለቁ ተሽከርካሪዎችንም ከመንገድ የሚያስወጣ አሰራር መቀየስ፣ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያበረታታ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡

አቶ ዳንኤል ለችግሩ መፍትሄ ነው የሚሉት፣ ተሽከርካሪዎች ዘመኑ ከሚፈቅደው ቴክኖሎጂ ጋር ለማጣጣም የተሰራውን ጥናት ነው፡፡ ከውጭ አገር የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ዕድሜ ለመገደብ ጥናቱ ተጠናቅቆ መመሪያ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም፣ ትግበራው ውጤት ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ታክሎበት ችግሮቹን ይፈቱታል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡

ኬንያ ከ8 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን እንዳይገቡ አግዳለች፣ ግብጽ፣ ባንግላዴሽና ህንድ ወደ አገራቸው እንዲገቡ የሚፈቅዱት እስከ ሦስት ዓመታት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ብቻ ነው፡፡ ቻይና ግን ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገሯ እንዲገቡ አትፈቅድም፡፡ ከአገራቱ ተሞክሮ በመውሰድ ኢትዮጵያም አገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ዕድሜ ለመገደብ እየተሰራ ነው፡፡ በእዚህም ለአየር ንብረት ተጋላጭነትን ለመቋቋም የሚከናወነውን በጎ ጅምር ጥላሸት የሚቀባውን አካሄድ መቀልበስ ይቻላል።

 

ዘላለም ግዛውና በሪሁ ብርሃነ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0004896931
TodayToday8395
YesterdayYesterday8828
This_WeekThis_Week55179
This_MonthThis_Month100001
All_DaysAll_Days4896931

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።