‹‹ይሄ የእኛ ቀጣና አይደለም» ለፖሊስ አባላት አይሠራም

ዜና ሐተታ

ቦታው ሸዋ ዳቦ ወረድ ብሎ ያለው ሜጋ አካባቢ ነው፡፡ ወቅቱ ማታ ከዛም በላይ ብርዳማ በመሆኑ አለፍ አለፍ ብለው በቆሎ በመጥበስ የሚሸጡ ሴቶች መንገደኛው ብርዱን ያስታግስለት ዘንድ የተጠበሰና የተቀቀለ በቆሎ እየሸጡ ይታያሉ፡፡በዚህ መሀል አንድ በግምት ዕድሜው 20ዎቹ ውስጥ የሚሆን ጎረምሳ ከአንድ እናት ላይ በቆሎ በመሸጥ ያጠራቀመችውን ብር ይነጥቃታል፡፡

እሷም እልህ በተናነቀው ድምፀት እንዲመልስላት ስትለምነው ገፍትሯት መንገዱን ቀጠለ፡፡ ይሄን ጊዜ በአካባቢው የደንብ ልብስ የለበሱ ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እያለፉ ነበር፡፡ የግለሰቧን ገንዘብ እንዲያስመልሱ ቢጠየቁም ከእነርሱ የተሰጠው ምላሽ ‹‹ይሄ የእኛ ቀጣና አይደለም» የሚል ሆነ።

በሌላ ቀን ተመሳሳይ ተግባር፤ ኢሚግሬሽን አካባቢ የተከሰተን ጾታዊ ትንኮሳ በአካባቢው ለሚገኝ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ቢጠቆምም በክፍሉ የነበረው ፖሊስ ግን ‹‹ይሄ የእኛ ክልል አይደለም›› ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው ከሃያ ሜትር ባልበለጠ ርቀት ውስጥ ነበር፡፡ ፖሊሱ ግን ወደ አራዳ ክፍለከተማ ወደሚገኝ ፖሊስ መምሪያ በመሄድ ጥቆማውን መስጠት እንደሚቻል ተናገረ፡፡ ወደተጠቀሰው ፖሊስ ጣቢያ ተሂዶ ችግሩ እልባት አገኘ።

ወይዘሮ ሚለን አማኑኤል መኖሪያቸው ቦሌ ክፍለ ከተማ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ወይዘሮዋ እንደሚሉት «ከሰሞኑ መገናኛ አካባቢ በግምት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ እያቆራረጠ የሁለት ብር ከ70 ሳንቲሙን ታሪፍ ሰባት ብር በሚያስከፍል ረዳትና በተሳፋሪ መካከል ውረድ አትውረድ አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ተሳፋሪው መብቱን በመጠየቁ እያቆራረጡ መሄድና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል መብታቸው እንዳልሆነ በመናገሩ ፀብ ተፈጠረ፡፡ በአካባቢው የነበሩ ተራ አስከባሪዎች ሳይቀሩ ተሳፋሪው ላይ ተረባረቡ፡፡ ጉዳዩም እየተጋጋለ በመምጣቱ ከተሳፋሪዎቹ መካከል የተወሰኑት ከአስፓልቱ ዳር ወዳሉት ሶስት ፖሊሶች በማምራት የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ ይጠይቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፖሊሶቹ የእነሱ ክልል እንዳልሆነ በመግለፅ ወደ ቦሌ ክፍለከተማ እንዲሄዱ ነገሯቸው» የሚሉት ወይዘሮ ሚለን፤ በወቅቱ ፖሊሶቹ በያዙት መገናኛ ራዲዮ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ መልዕክት እንዲ ያስተላልፉላቸው ቢጠየቁ እንኳ፤ የቦሌን ፖሊስ ጣቢያ አድራሻ እንደማያውቁት ምላሽ መስጠታቸውን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹በአካባቢው የተገኙት ፖሊሶች በወቅቱ ማብረድ የሚቻለውን ቀላል ተግባር በእንጭጩ መቅጨት እየቻሉ ዝም ማለታቸው ህገወጥ ድርጊት ነው›› ይላሉ ወይዘሮ ሚለን፡፡ አያይዘውም ችግሩ እየተፈጠረ ያለው የገቡትን ቃል ለመተግበር የቅንነት ጉድለትና የስራ ኃላፊነትን ጠንቅቆ ካለማወቅ የመነጨ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ሲዘጋጁ ፖሊሶች ላይ በስፋት የሚነሱትን ቅሬታዎች ከመድረክ ግብዓትነት ባለፈ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን እየመረመሩ መፍትሄ ሊሰጡት ይገባል የሚል እምነት አንዳላቸው ይገልፃሉ።

ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል እንደሚናገሩት፤«ፖሊሶች ከተመደቡበት ቀጣና ውጪ በትብብር ካልሆነ በቀር ሌላ ክልል ላይ የተፈጠረን ህገ-ወጥ ተግባር የመከላከል ግዴታ የለባቸውም። ይህም ሊሆን የቻለው ፖሊሶች እየሰሩ ያሉት በባህላዊ መንገድ ስለሆነ እንጂ ከህግ አንፃር ማንኛውም የፖሊስ አባል ወንጀል ሲፈፀም ክልሉም ባይሆን በዕለት ውሎ መዝገቡ ይዞ ተበደልኩ የሚለውን አካል፣ በደል ፈፅመሃል በሚል ክስ የቀረበበትን እንዲሁም ምስክሮችን ከመዝገቡ ጋር አያይዞ መላክ እንደሚኖርበት ይታመናል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት መሰል ችግሮች የሚከሰቱት በቸልተኝነት፣ ለመተባበር አለመፈለግና ቅንነት አለመኖር እንዲሁም ቀጣናው ባለመሆኑ አያስጠይቀኝም ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው» በማለት የተመደብኩበት ክልል አይደለም የሚል ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ይህንን «ክልሌ አይደለም» የሚለውን የፖሊሶች ምላሽ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ አንዲሰጥበት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ኮማንደር ፋሲካው ፋንታን አነጋገርን። ወንጀልን መከላከል እንኳን የፖሊስ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ግዴታ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ህዝቡን በታማኝነትና በቅንነት አገለግላለሁ ብሎ ግንባር ቀደም የሆነው የፖሊስ ሀይል ድርብ ኃላፊነት ቢሆንም አልፎ አልፎ ይሄን አስተሳሰብ የሚቃረኑ ተግባራት ሲከሰቱ እንደሚስተዋሉ ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ማንኛውም የፖሊስ አባል የደንብ ልብስ ባይለብስም በየትኛውም ስፍራ ችግሮችን የማረጋጋት ስራ መስራት እንደ ሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡ በቅርብ በቂርቆስ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አዋሳኝ ላይ አለመግባባት ቢፈጠርም በቦታው የነበሩ የፖሊስ አባላት ግን ‹‹እኛ አይመለከተንም›› በሚል መገፋፋቶች ተፈጥረው እንደነበር ተሰምቷል፡፡ በተለያዩ ወቅቶች መሰል ችግሮችም ከህብረተሰቡ እንደሚነሱ አረጋግጠዋል፡፡

ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር አሰራርን ማዘመን በመሆኑ ስራውን በተቀላጠፈ መልኩ ማስኬድ የሚቻልበት መንገድ ተቀይሷል፡፡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች የገቡ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም አዲስ ነፃ የስልክ መስመር 911 ተዘርግቶ ሙከራ ስርጭት ጀምሯል፡፡ ለእዚህ ስራ የሚሰማሩም ከሶስት መቶ በላይ የፖሊስ አባላት ስልጠና ወስደው ባለፈው ሳምንት ተመርቀዋል፡፡ ይህም በማንኛውም ቦታ ጥቆማ ተደውሎ ከተሰጠ የደዋዩን ሙሉ መረጃ በመያዝ የተባለበት ስፍራ በመገኘት ለችግሩ እልባት የመስጠት ስራ ይሰራሉ። በመሆኑም ቀድሞ የነበረውን ክልሌ ነው አይደለም የሚለውን ችግር ያቃልላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮማንደር ፋሲካው ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ወንጀል ሲፈፀም እያዩ ዝም ማለት እንደ ወንጀል ተባባሪነት የሚቆጠር በመሆኑ፤ ሁሉም ፖሊሶች በየትኛውም አካባቢዎች ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 

ፍዮሪ ተወልደ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።