«ቅሬታ የበዛበት» የቀን ገቢ ግምት Featured

ተግባራዊ እየተደረገ  ያለው አማካኝ የቀን ገቢ ግምት በርካታ ቅሬታዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ችግሩ ሊፈጠር የቻለው የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ባግባቡ ባለመሰራቱ መሆኑ በአንድ በኩል ሲነገር፤ በሌላ በኩል  ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ መሆኑም እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡ ቅሬታ የበዛበት የቀን ገቢ ግምት ትክክለኛ  ምክንያቱ ምን ይሆን?

በኮከብና መልካሙ የኦዲት ሽርክና ማህበር የሂሳብ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ አበበ፤ ግብር አስገቢው ባለስልጣን ለደረጃ ‹‹ሐ›› ነጋዴዎች በቅርበት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይገባው እንደነበር አስታውሰው፤  ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ባግባቡ እንዳልተከናወነም ይናገራሉ፡፡ የቀን ገቢ ግምት የሚሰራው ወጪዎች ተቀንሰው ነው፤ አሰራሩ እንኳን ለነጋዴው ማህበረሰብ ለባለሙያም ቢሆን ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉት። ለተፈጠረው ቅሬታ ምክንያቱ ስለ ስሌቱ ለነጋዴው ህብረተሰብ ባግባቡ የማስረዳት እጥረት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ዮሐንስ እንደሚያብራሩት፤ ወደ ግመታ ከመገባቱ አስቀድሞ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ባግባቡ ባለመሰራቱ አንዳንድ ነጋዴዎች ከሱቆቻቸው እቃዎችን ሲቀንሱ ታይቷል፡፡ በቀን የሚያስገቡትን የገቢ መጠን የመደበቅ ዝንባሌም ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ በለጠ ዘውዴ፤ ሰሞኑን በመርካቶ ገበያ አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቅ ዘግተው ማየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ሂደቱ ተገቢ እንዳልነበረም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ተቀባይነት አናገኝም›› የሚል የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ ቅሬታ ማቅረብ የማይፈልጉ አንዳንድ ነጋዴዎች እንደገጠማቸውም ይናገራሉ፡፡   

በግብር ሰብሳቢው ባለስልጣንም ለነጋዴው ህብረተሰብ በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዳልተሰራ አስታውሰው፤ ነጋዴዎች የቀን ገቢ ግምቱን በዓመታዊ ሽያጭ አባዝቶ ተከፋይ ድምርን የማስቀመጥ ሁኔታ እንዳለ መታዘባቸውን ይጠቁማሉ። በመሆኑም ሥራው ራሱን የቻለ ስሌት እንዳለውና ነጋዴው የሚደርስበት ተከፋይ ግብር ምን ያህል እንደሆነ የማስረዳት እጥረት የፈጠረው መሆኑን ይገልፃሉ።           

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ ግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ፕሮግራም ልማትና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ፈቃደ፤ የንግዱን ማህበረሰብ በተለያየ መንገድ ስለአሰራሩና ሊደረግ ስለታሰበው ነገር ግንዛቤ ለመፍጠር መሰራቱን፣ የተለያዩ አደረጃጀቶችንና ህብረተሰቡን የማወያየት ሥራ በስፋት መሰራቱን ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ግንዛቤ በመፍጠር በኩል የትግበራው መጠን በቂ አልነበረም፡፡ ሥራው ተደጋጋሚ መሆን ይገባው እንደነበርና አሰራሩ ክፍተት እንደነበረበትም ያምናሉ፡፡

የግንዛቤ እጥረቱ ሰፊ ክፍተት መፍጠሩን በመጠቆም፤ ነጋዴው በትክክል የሚከፍለውን የግብር መጠን ባለማወቁ ለችግሩ መንስኤ ሆኗል ይላሉ፡፡ አንዳንዶች የቀን ገቢ ግምቱን በዓመት አባዝቶ ያንን እንዳለ የተጣራ ግብር እንደሚጣል አድርጎ ማሰብ በስፋት የታየ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ (አንድ መቶ አስር ብር )  110 ብር አማካኝ የቀን ገቢ ግምት  ተገምቶላቸውም ጭምር ቅሬታ ይዘው የሚመጡ ነጋዴዎች ማጋጠሙን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በንግድ አሰራሩ መሰረት ግምቱ ነጋዴዎቹን ከግብር ነጻ እንደሚያደርጋቸውም አለማወቃቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት የመዘርጋት ሂደቱ ጊዜ እንደሚጠይቅ የሚጠቁሙት አቶ ያሬድ፤ በተለይ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ነጋዴዎች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸውና ግብራቸውንም በሂሳብ መዝገባቸው መሰረት መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ይጠቁማሉ፡፡

እንደአቶ ያሬድ ማብራሪያ፤ የደረጃ ‹‹ሐ›› ነጋዴዎችም የሂሳብ መዝገብ ቢይዙ ይበረታታል፡፡ ግን ህጉ የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ አያስገድዳቸውም፡፡ በተለይ ግለሰብ ነጋዴዎች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ባህላቸው ደካማ ነው፡፡ ደረሰኝ ላይ መሰረት ያደረገ ግብይት መፈጸምም አልተለመደም። አብዛኞቹም ከባህላዊ አሰራር አልወጡም፡፡ ወደ ዘመናዊ የአሰራር ሂደት የመሻገሩ ሂደትም ዘገምተኛ ነው፡፡

አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው በተለይም በደረጃ ‹‹ሐ›› ያሉት አብዛኞቹ ነጋዴዎች ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት የሚከተሉ አይደሉም፡፡ በመሆኑም እነዚህን ነጋዴዎች ወደ ዘመናዊ አሰራር እንዲሻገሩ ተከታታይነት  ባለው መልኩ የማስገንዘብ ሥራ በመገናኛ ብዙሃን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ተመኑ በዝቷል የሚሉ ጥያቄዎችንም ባግባቡ መመልከትእንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ፡፡

አቶ በለጠ፤ ግምቱ ራሱን የቻለ ስሌት አለው፡፡ ግብር ሰብሳቢው ባለስልጣን ግልጽነት እንዲፈጠር መስራት አለበት፡፡ የሚጣል ተከፋይ ግብር ምን ያህል እንደሆነ ነጋዴው ጠይቆ እንዲረዳና መረጃ እንዲያገኝ የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቶ ሰፊ ሥራ መስራት ይኖርበታል ይላሉ፡፡

አቶ ዮሐንስ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ድርጊት ከግልጽነት እጥረት የመነጨ ነው፡፡ይህ አካሄድ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ተገቢ ያልሆኑ ህገ ወጥ የኃይል ድርጊቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፣ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ከዘጉ ሸማቹንም ይጎዳሉ የሚል ስጋት አላቸው፡፡    

የተረጋጋ የንግድ ሥርዓት ካልሰፈነ በሂደቱ ሸማቹ ህብረተሰብ ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይም ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል  ነው የአቶ በለጠ ስጋት፡፡       

ነጋዴው ወደ ዘመናዊ አሰራር እንዲገባ የማስተማርና ግንዛቤ ለመፍጠር ሰፊ ሥራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ደረጃ ሲለካ ተገቢ ሥራ አልተሰራም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አማካኝ የቀን ገቢ ግምት አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ለመሻገር እንዲቻል ጥናት እየተሰራ ሲሆን፤ ከአማካኝ የቀን ገቢ ግምት የተሻሉ አማራጮችን ለመተግበር ያስችላል የሚል ተስፋ አላቸው አቶ ያሬድ ፡፡

ዜና ትንታኔ

ዘላለም ግዛው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።