አዲስ አሽከርካሪዎች እስከ ሁለት ዓመት በጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ እንዲያሽከረክሩ ይገደዳሉ Featured

አቶ ታደሰ ተፈራ

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የፖሊሲና ህግ ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሥራ ላይ የነበረው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተሻሽሎ ሥራ ላይ እንደሚውል ተገለጸ፡፡

በ2000ዓ.ም የወጣው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ ብቃት ያለው አሽከርካሪ ለማፍራት ታስቦ እንደነበር የሚታወስ ነው:: ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተከትሎ ከፍተኛ የመኪና ቁጥር መጨመር እና የህዝቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ከማደግ ጋር ተያይዞ የመኪና አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ በመምጣቱ ቀድሞ ይሠራበት የነበረውን አዋጅ ማሻሻል የግድ እንዳደረገው በትራንስፖርት ሚኒስቴር የፖሊሲና ህግ ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ተፈራ ገልጸዋል::

አሁን ያለው አጠቃላይ የትራንስፖርትና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ከአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ጋር አብሮ እንዲያድግ ይህን ደንብ ማሻሻልም ተገቢና አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የትራፊክ አደጋን በመቀነስ እና አስተማማኝ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ ለትራፊክ ፖሊስም ሆነ ሌሎች ሕግ አስከባሪዎችን በተሻለ ለመቆጣጠር እንደሚያስችላቸው  ይታመናል::

በአገራችን አሁን ላለው የትራፊክ አደጋ እንደ ዋና ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ፣ የመንገድ ችግር፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ብቃት ችግር በዋናነት የሚጠቀሱ  ናቸው:: ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ለአሽከርካሪዎች የተሰጡ የመንጃ ፈቃዶች ሁኔታ እንደሚያሳየው ከ80 በመቶ በላይ አደጋ የተመዘገበው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በተሰጡ የመንጃ ፈቃዶች እንደሆነ በ2007 ዓ.ም ከፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳይ አቶ ታደሰ ነግረውናል፡፡ ከዚህ በመነሳት በመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ ላይ ችግር እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡ መንግሥትም ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ እንደሆነ እና በቀጣይ ደረጃውን የጠበቀ የአሽከርካሪን ብቃት የሚያሳድጉና ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡

«አንድ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ የሚለካው በስልጠናው አሰጣጥ፣ በሚሰጠው ፈተና፣ ተማሪውን በአግባቡና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ይለካል ወይም ይፈተናል ወይ የሚሉትን ቁምነገሮችን እና የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ይሆናል»

ከእነዚህ መስፈርቶች በመነሳት አሁን ያሉትን በማሻሻል ችግሩን በቀጣይነት ለመቅረፍ እንደሚሠራ እና ለዚህም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ተገልጿል::

ከእነዚህ ተግባራት ጎን ለጎን የሌሎችን አገሮች ተሞክሮም ለመቅሰም ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት አንድ አሽከርካሪ ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ ዋናውን የመንጃ ፈቃድ ወዲያው እንዲያገኝ አይደረግም፡፡ ይህ ከመደረጉ በፊት ልምድ ካላቸው አሽከርካሪዎች ጋር እስከ ሁለት ዓመት አብሮ እንዲነዳ በማድረግ ብቃቱንና የራስ መተማመኑን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥፋት አለመፈፀሙ ከተጣራ በኋላ ዋናው መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ግን እንደገና ስልጠናውን እንዲወስድ ይገደዳል፡፡ እኛ አሁን ያወጣነው አዋጅ ይህን ስርዓት የሚከተል ሲሆን፤ አንድ ሰልጣኝ ስልጠናውን ሲያበቃ የሚሰጠው የመንጃ ፈቃድ ዋናውን የመንጃ ፈቃድ ሳይሆን ለሁለት ዓመት የሚያገለግል ጊዜያዊ የመንጃ ፈቃድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊው ክትትል ተደርጎ አንድ አሽከርካሪ ጥፋት ካልፈፀመ ዋናው መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተወሰነ የአሠራር ችግር ሊገጥም እንደሚችል የሚገመት ሲሆን፤ በሂደት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የሚቀረፍ እንደሆነ በመጠቆም ይህ አዋጅ መሻሻሉ በችሎታና ሥነ-ምግባር የዳበረ አሽከርካሪ እንዲኖረን የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።