ተጨባጭ መረጃ ከተገኘ ሚኒስትሮችም ቢሆኑ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገለጸ

ሙስና የፈፀመ ማንኛውም ሰው ተጨባጭ መረጃ ከተገኘበት ተጠያቂ እንደሚሆን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አስታወቁ፡፡  

      ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተር እንደገለፁት፤ አመራሩን ጨምሮ አጠቃላይ ሕዝቡ ሙስና የፈፀመ በሙሉ ተጠያቂ እንደሚሆን መገንዘብ አለበት፡፡ መንግሥት በሚሰራው ሥራ የሕዝብን አመኔታ የሚፈልግ በመሆኑ ማንንም ከማንም ሳያበላልጥ ያጠፋ ሁሉ እንዲጠየቅ ያደርጋል፡፡

«እየተወሰደ ያለው እርምጃም ለሕዝብ ጥርጣሬዎች በሙሉ ምላሽ ተሰጥቷል የሚያስብል አይደለም። በአንድ ጊዜ ሁሉም ጥያቄ ይመልሳል ተብሎም አይታመንም» ያሉት ሚኒስትሩ፤ እየተወሰደ ያለው እርምጃ መረጃ ያልተገኘባቸውንም ለመለየት መነሻ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ 

      በአንድ ቀን 31 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና እነርሱን እንደምንጭ በመጠቀም በሚደረግ ምርመራ ንክኪ ያላቸው ብዙዎችን ማግኘት እንደሚያስችል ጠቁመው፤ የሚከሰሱት ሰዎች የሚሰጡት መረጃ  ወደ ብዙ ሚኒስትሮች ሊያደርስ ይችላል ብለዋል፡፡ በመሆኑም መረጃ ከተገኘ ሚኒስትሮችም ቢሆኑ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ  እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

     የበታች ኃላፊዎችም ሆኑ ፈፃሚዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ሲጠየቁ፤ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የበላይ ኃላፊዎች በድርጊቱ ላይ ባይሳተፉም ድርጊቱን እያወቁ ማለፋቸው ከተረጋገጠ ተጠያቂ የማይሆኑበት ምክንያት አለመኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ 

ማንም ከማንም ተለይቶ የተለየ ከለላ የሚሰጥበትና ከተጠያቂነት እንዲሸሸግ የሚደረግበት ሁኔታ የለም። በወንጀል ውስጥ የገባውና ያንን መከታተል ያለበት ኃላፊ እኩል ተጠያቂ ባይሆኑም፤ ሁሉም በየደረጃው እንደሚጠየቅ  ገልጸዋል፡፡

ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።