የድንበር ግጭት ባለባቸው ክልሎች ‹‹ልዩ ቆጠራ›› ይካሄዳል

  - ለቆጠራው 3 ቢሊዮን ብር ተበጅቷል

አገሪቱ በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ በ2010 ዓ.ም ለምታካሂደው አገር አቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በድንበር ይገባኛል ግጭት በሚስተዋልባቸው ክልሎች አስቀድሞ መፍትሄ ካልተሰጣቸው ልዩ ቆጠራ እንደሚካሄድ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡አገር አቀፍ ቆጠራውን ለማካሄድ 3 ቢሊዮን ብር ተበጅቷል፡፡

     የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በድንበር ይገባኛል ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በፍጥነት እልባት ካልተበጀ  በ2010 ዓ.ም መጀመሪያው ሩብ ዓመት እንደሚካሄድ ለሚጠበቀው፤ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኤጀንሲው  ‹‹ልዩ ቆጠራ›› ለማካሄድ አማራጭ ይዟል፡፡

አቶ ሳፊ፤ በድንበር አካባቢ ግጭቶች በአማራ እና ትግራይ እንዲሁም በኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መካከል የተከሰተ ቢሆንም፣  በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ እልባት እየተሰጣቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የየክልሉ መንግሥታትም መሰል ችግሮችን በፍጥነት እንዲፈቱና ለቆጠራው ስኬታማነት  ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ ምናልባት በእነዚህ አካባቢዎች መፍትሄ ያልተበጀላቸው ከሆነ የህዝብና ቤት ቆጠራው ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔሃብታዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ትንቢያ እና ትርጉም የጎላ አንድምታ ስላለው ‹‹ልዩ ቆጠራ›› ይካሄዳል፡፡ ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች የሚቆጠረው ህዝብ በአገሪቱ ህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት ላይ የሚደመር እንጂ ወደ ማናቸውም ክልል እንደማይጠቃለሉ ተናግረዋል፡፡ በሌላው ዓለም መሰል ችግሮች ሲከሰቱ ‹‹ልዩ ቆጠራ›› ተግባራዊ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡

በተያያዘም ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ 3 ቢሊዮን ብር ተበጅቷል፡፡ ቆጠራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ ሲሆን፤ ለዚህም የሚያግዙ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተገዙና ጂ.ፒ.ኤስ የተገጠመላቸው 180ሺ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ በቆጠራው ተቆጣጣሪዎች፣ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ 190ሺ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ቆጠራው በአሥር ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ባለሙያዎችን መምረጥ የክልሎች ኃላፊነት እንደሚሆንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ 1976 ዓ.ም፣ 1987 ዓ.ም እና 1999 ዓ.ም አገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ ያካሄደች መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ1987 ዓ.ም በፀደቀው የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀፅ 103 መሰረት ደግሞ በየአሥር ዓመቱ  የህዝብና ቤት ቆጠራ እንደሚካሄድ ይደነግጋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።