በአንዱ ክልል ውሃ ሙላት፤ በሌሎቹ ውሃ ጥማት ትምህርት ሲያስተጓጉል Featured

የአፋር ክልል ውሃ ጥማት ፤

በቀደሙት ዓመታት ትምህርት ለማቋረጥ አያሌ ምክንያቶች ይጠቀሱ ነበር። ለአብነትም ልጆች ወላጆችን ሥራ ለማገዝ፣ ለትምህርት የጎለበተ አመለካከት ያለው ማህበረሰብ አለመበራከት እንዲሁም ኋላ ቀር የኑሮ ዘይቤ መከተል አንኳር ችግሮች ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በታዳጊ ክልሎች ወደ ትምህርትቤት የሚመጡ ተማሪዎች ቁጥር ዕድገት ቢያሳይም የሚያቋርጡትም በርካቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ ከተለመደው ችግር ባለፈ ትምህርት ለማቋረጥ የሚያስገድዱ ተፈጥሯዊ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው።

የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኦሞድ ከፋላ እንደሚሉት፤ በክልሉ የውሃ ሙላት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ  እያስተጓጎለ ነው። በተለይ በኑዌርና አኝዋክ ዞኖች አንዳንድ ሥፍራዎች፣ኢታንግ፣ ሌራ የሚሰኙ ወረዳዎች፣ በአኮቦ ወረዳ ውስጥ ያሉ ትምህርትቤቶች እንዲሁም ከክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ ራቅ ብለው የሚገኙ ወረዳዎች የውሃ ሙላት ክፉኛ እያስቸገራቸው ነው። ተማሪዎች እጅግ ዘግይተው ትምህርት የሚጀምሩ ሲሆን፤ የትምህርት ማጠናቀቂያ ወቅት ሳይደርስም በውሃ ሙላት የተነሳ ለማቋረጥ ይገደዳሉ።

አቶ ኦቦንግ እንደሚሉት፤ ለመፍትሄ ከተቀመጡት መካከል ሕብረተሰቡ ቀደም ብሎ ውሃ ሙላት ከመከሰቱ በፊት የመምህራን ቁሳቁስ በማጓጓዝ ችግሩን ለመቋቋም ጥረት ሲደረግ ነበር። ወንዞቹን አቋርጦ የሚያልፉ ጠንካራ ድልድዮችን መገንባት ደግሞ ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆን በእቅድ ተቀምጧል። ነገር ግን ከክልሉ መንግሥት አቅም አኳያ ሁሉንም ትልልቅ ድልድዮችን እና መሸጋገሪያዎችን መገንባት አስቸጋሪ ስለሆነ የፌዴራል መንግሥት እገዛ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አቶ መሐመድ አህመድ ኑር የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ፤ የውሃ ጥማት ልጆችን ከትምህርት እያራቃቸው እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ በዚህ ዓመት በኤልኒኖ ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ  በርካታ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል። ቀብሪድሃር፣ ዶሎ እና ጀር፤ የሚባሉ ዞኖች ደግሞ በርካታ ተማሪዎች የተጎዱበት ስፍራ ነው። በዚህ ዓመት በተከሰተው ድርቅ  የ229 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በድርቅ ተጎድተዋል። ይሁንና ከፌዴራል መንግሥትና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለማቃለል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በ37 ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምገባ ተጀምሯል። ከዚህም ባሻገር ለታዳጊ ክልሎች በሚደረገው ልዩ ድጋፍም ችግሮችን በዘላቂነት  ለማቃለል ጥረት በመደረግ ላይ ነው።

የክልሉ መንግሥትም ውሃ አቅርቦት ማሳደግ፣ በትምህርት እና በተፋሰስ ማስፋፋት ላይ በአፅንኦት እየሠራ ሲሆን፤ ድርቅ የሚበረታባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች በተፋሰስ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ እየተደረገ ነው።  በክልሉ የሚገኘው የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እገዛው ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓሊ ሁሴን በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ካሉ ደጋ እና ወይናደጋ አካባቢዎች አኳያ በክልሉ ሞቃትና  ዝቅተኛ ዝናብ የሚስተዋልበት በመሆኑ ድርቅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው። ተማሪዎችም በውሃ ጥማት ከትምህርት ገበታቸው እየራቁ ነው። ክልሉ አብዛኛው የበረሃማነት ባህሪ ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ በአንድ አካባቢ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በተለይም ለእንስሳት ሲባል ውሃ ባለበት ስለሚንቀሳቀሱ  በአንድ ስፍራ ተረጋግቶ ከመማር አኳያ አሉታዊ ጫና መፍጠሩን ይናገራሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ መንግሥት አርብቶአደሮቹ በሄዱበት አካባቢ እየተንቀሳቀሱ የሚያስተምሩ መምህራንን ቢያሰማራም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን በሙሉ ማስተማር አልተቻለም። በተለይ በዚህ ዓመት የተከሰተው ድርቅ የከፋ ችግሮችን አስከትሏል። ችግሮቹ በዚህ ከቀጠሉ የተማረ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንዳያቀዛቅዘው ይሰጋሉ።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የውሃ ጥማት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ ቢያደርግም ችግሮቹን ለማቃለል የሚደረገው ጥረት የተጠናከረ  ነው። በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግሮችን ሊያቃልሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የመፍትሄ አካል እየሆኑ ነው። ለዚህም  የአፋር ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው፤ ተማሪዎች በመሠል ችግሮች ከትምህርት እንደሚቀሩ መረጃው አለኝ ይላሉ። ድርቅና ውሃ ሙላት ተፈጥሮ አንዳንዴ ከምታስከትላቸው ችግሮች ናቸው። በችግሮቹ ሳቢያ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ለጊዜው በውሃ ሙላት ለሚቸገሩ አካባቢዎች እንደ መፍትሄ የተቀመጠው ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ለመማር ማስተማር የሚያግዙ ግብዓቶችን ቀድሞ ማጓጓዝ፣ ችግሮችን ቀድሞ መረዳትና መዘጋጀት ዋንኞቹ ናቸው። የክልሉ መንግሥት እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ እገዛ ማድረግ እንዳለበትና በማድረግም ላይ መሆኑን ያብራራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎች በድርቅና ሌሎች ተፈጥሯዊ ክስተቶች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ቀድሞ ይደረግ ከነበረው ድጋፍ እና ክትትል በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ክፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ችግሮችን መከላከልና መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ይናገራሉ። በሂደትም ችግሮች ይቀንሳሉ ባይ ናቸው።

ዜና ሐተታ

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።