ፕሮጀክቱ ህጋዊ የውጭ አገራት ሥራ ሥምሪት እንዲስፋፋ ያግዛል ተባለ

የዓለም የሥራ ድርጅት በኢትዮጵያ ህገወጥ  ስደትን ለመከላከል እና ህጋዊ የውጭ ሥራ ስምሪት እንዲኖር የሚያግዝ ፕሮጀክትን  ይፋ አደረገ፡፡ 

ፕሮጅክቱ ሰሞኑን ይፋ በሆነበት ወቅት  በሥራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገራት  ስምሪት  ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ እንደተናገሩት፤ የፕሮጀክቱ  ዋና ዓላማ የውጭ አገራት ሥራ ሥምሪት ህገወጥ መንገድን በተከተለ መልኩ ሳይሆን ህጋዊ በሆነ መልኩ  እንዲካሄድ ማስቻል ነው፡፡ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል አንደኛው መንገድ ህጋዊ ስምሪቱን ማጠናከር በመሆኑ፤ ፕሮጀክቱ የዜጎችን አቅም  በመገንባት እና ለህብረተሰቡ ስለ ስደት አስከፊነት በማስተማር ግንዛቤ መፈጠር ላይ ይሠራል፡፡ በተጨማሪም ዜጎች በአገራቸው  ሠርተው መለወጥ እንዲችሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት መካከል በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ መሆኗን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአንጻሩ ከአገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ የስደተኞች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን አስታውሰው፤ከአገር የሚወጡት ዜጎች ለአደጋና ለህልፈት ሕይወት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ድህነት እና ስለስደት ያለው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ፕሮጅክቱ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ስለስደት አስከፊነት በማስተማር በአገር ውስጥ ሠርተው እንዲለወጡ  ይሠራል ብለዋል፡፡

ከእዚህም ባሻገር አንድ ውጭ አገር የምትሄድ ሴት ከመሄዷ አስቀድማ  በምትሠራው ሥራ ላይ ስልጠና ለመስጠት ይረዳል፡፡ በተጨማሪ ከስደት ተመላሾች እንዴት ገንዘብ መያዝ እንዳለባቸው ስልጠና ለመስጠት ፕሮጀክቱ ያግዛል ብለዋል፡፡

  የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት  ቢሮ ዳይሬክተርና የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይ ሚስተር ጆርጅ  ኡኩቶ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ህገወጥ ሥምሪትን ለመግታት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ይሠራል፡፡

  ፕሮጀክቱም ከእንግሊዝ የልማት ድርጅት ዲ.ኤፍ.አይ.ዲ  በተገኘ 3 ሚሊዮን ዩሮ የሚፈፀም ሲሆን፤  እ.አ.አ ከ2017 እስከ 2020 የሚቆይ ይሆናል፡፡

ሰብስቤ ኃይሉ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።