ክልሉ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ 26 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መያዙን አስታወቀ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለወጣቶች የፌዴራል መንግሥት ከመደበው በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል 26 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አቶ አሻድሊ ሐሰን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በክልሉ ሰፊ ለም መሬት፤ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ኃይል በመኖሩ ያለውን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም  የተለያዩ ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ሴቶችና ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ጥረት በርካቶችን ወደ ሰብል ምርትና እንስሳት እርባታ ማስገባት ተችሏል፡፡

‹‹አሁንም በተካሄደው ጥናት በክልሉ 16ሺ280 ሥራ አጥ ወጣቶች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት በልዩ ሁኔታ ከሚመድበው የወጣቶች በጀት በተጨማሪ የክልሉ መንግሥት 26 ሚሊዮን ብር መድቧል›› ብለዋል፡፡

እንደርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ፤ የክልሉ መንግሥት ቱሪስቶችን ለማቆየት ታሪካዊ ቦታዎችንም የማሳደስ ሥራ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም ወጣቶች እያደረጉ ባለው ተሳትፎ የሥራ ዕድል እያገኙ ሲሆን፤ በቀጣይም የክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ለወጣቶቹ ሥራ ፈጠራ ከፍተኛ ዕድል ይኖረዋል፡፡  በተለይም በክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ቱሪዝም ሰፊ የሥራ አማራጭ እንደሚኖር በመታሰቡ  ወጣቱ የተሻሉ የሥራ ዕድሎችን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በክልሉ ከዚህ በፊት ሴት ወጣቶች ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ግን የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር በማደራጀት ሥራፈጥረው ሃብት የሚያፈሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ የመንደር ማሰባሰብ የቴክኒክ ኮሚቴ  መሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊው  አቶ ሙለታ ወንበር እንደገለፁት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወጣቶች እርሻ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ሰፊ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ የቴክኖሎጂና የዘር አቅርቦት ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ወጣቶች እያመረቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ወጣቶቹ ሙዝ፣ ዘይቱን  ሰሊጥ፣ አኩሪአተር እና በቆሎ በብዛት እያመረቱ ነው፡፡ በእነዚህ ምርቶች ካፒታላቸው ማደግ በመጀመሩ በበሬ ከማረስ አልፈው፤ ትራክተር እየጠየቁ ነው፡፡ እንደየማሳቸው መጠን ታይቶ ብድር  በመመቻቸት ትራክተር የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

በክልሉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ 500 ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ማደራጀት ተችሏል፡፡ መንግሥት 13 ትራክተሮችን በመግዛት በብድር የሰጠ ሲሆን፤ በተጨማሪነት በዚህ ዓመትም ሰባት ትራክተሮች ተጨምሮላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት 20 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን 10 ተጨማሪ ትራክተሮችን በመግዛት  ስልጠና ተሰጥቶ ትራክተሮቹ እንዲከፋፈሉ የሚደረግ  መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

«ወጣቶችን በግብርና ላይ በማሰማራት ተተኪ አርሶአደርና ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ እየተሰራ ነው» ያሉት አቶ ሙለታ፤ በእንስሳት ማድለብ ላይ በርካታ ወጣቶች እየሰሩ ነው፡፡ እስከ አሁን የተሰራው መነሻ እንጂ በቂ ነው ተብሎ የሚወሰድ ባይሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለወጣቶች ልዩ ትኩረት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የመስኖ ቦታዎችን በመለየት ለወጣቶች ለመስጠት እና የዶሮ ዕርባታ ላይ በስፋት ለማሳተፍ  መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ 

ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።